
ኢትዮጵያ አትደፈርም!!
እነሆ ዛሬ ነሐሴ 12/2013 የሦስት ህያው ጀግኖቻችን የልደት ቀን ነው። የዓድዋው ጀግና፣ የጥቁር ሕዝቦች የድል ሐውልት ምልክት የዳግማዊ አጤ ምኒልክም 177ኛ፣ የጦር ሜዳ ባለሟሏ እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘ-ኢትዮጵያ እና የጦሩ ገበሬ ፊታውራሪ ገበየሁ ገቦ 181ኛ የልደት ቀን ነው። እነዚህ ህያው ጀግኖቻችን የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ጉልህ አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡ በተለይም የውጭን ጠላት አንበርክከው፣ ለኢትዮጵያ ሀገራችን ሉዓላዊነት፣ ለዛሬው ትውልድ ኩራት ብቻ ሳይሆን ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የድል ምልክት የሆነ ደማቅ ታሪክ ሠርተው አልፈዋል።
አባቶቻችንና እናቶቻችን ከውጭ ወራሪ ጋር ተፋልመው፣ ባንዳውንም ልክ አስገብተው ሀገር አቆይተውልናል። ድልን በደማቅ ቀለም የፃፉ ህያው ጀግኖቻችንን የልደት ቀን በምናከብርበት በዚህ ዕለት የውጭ ቅጥረኛ ባንዳዎች ወረራ ፈፅመውብናል።
ትህነግ በግብር አሸባሪና ወራሪ ሲሆን፤ በተልዕኮ ደረጃ ደግሞ የኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች ቅጥረኛ ነው፡፡ ቅጥረኝነቱ ኢትዮጵያን ከማዳከም እስከ መበታተን የደረሰ ነው፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያችን በቀደመ እውነቷ እንደምትድን አንጠራጠርም፡፡ የትኛውንም ቅጥረኛ ባንዳ በመቅበር ኢትዮጵያ ታሸንፋለች፡፡ ለዚህም የታሪክ ውርሳችን ትልቅ አቅም ይሆነናል፡፡
ህያው ጀግኖቻችንን ስናከብርም ሆነ ስንዘክር የእነሱን ዓላማ የወረስን መሆኑን በተግባር እያስመሰከርን ሊሆን ይገባል።
ጀግኖቻችን በዘመናቸው ከእነሱ የላቀ የጦር መሳርያ ይዞ የመጣውን ጠላት፣ በጥቅም የተገዛውን ቅጥረኛ ባንዳ አንበርክከው በመስዋእትነታቸው ኢትዮጵያን እንዳቆዩት ሁሉ እኛም በዘመናችን የገጠመንን ደመኛ ጠላት አንበርክከን የትውልድ አደራችንን እንወጣለን።
እንደ እምዬ ምኒልክ ለክብር፣ ለነጻነትና ለፍትሕ መቆምን፤ እንደ እቴጌ ጣይቱ ጦር አዝምተንና ግንባር መርተን፣ ጠላት ማርበድበድን፤ እንደ ፊታውራሪ ገበየሁ “ስሸሽ ከኋላዬ ከተመታሁት፣ ሬሳዬን ምድር አትቀበለው፣ የሎስ አሞራ ይብላው” ብለን የአባቶቻችን ጀግንነት ወራሾች መሆናችንን የምናስመሰክርበት ጊዜው አሁን ነው።
የአባቶቻችንና የእናቶቻችን ድል አድራጊነት ስንዘክር እንደኖርነው፣ የትውልድ ግዴታችን ተወጥተን ባለድሎች እንሆናለን።
የዘመናችንን ደመኛ ጠላት አሸንፈን እንደ ትውልድ፣ በድል እንደገና ተወልደን የጀግኖቻችን ክብርን እናስጠብቃለን።
የጀግኖቻችንን ልደት የምናከብረው ጠላትን በታትነን፣ ወራሪነት ውድ ዋጋ እንደሚያስከፍል አሳይተን፣ የሕዝባችንን ሕልውና እና የኢትዮጵያን አንድነት አረጋግጠን እንጂ ኬክ ቆርሰን ብቻ አይሆንም።
አባቶቻችን እና እናቶቻችን በዓድዋ ዘመቻ እንዳደረጉት፣ በያዝነው የህልውና ትግል የፖለቲካ ልዩነታችንን ወደጎን ትተን፣ በአንድ ልብ፣ በአንድ የትግል ዓላማ መስመር እና ግንባር ተሰልፈን በደመኛ ጠላታችን ላይ ድል ተቀዳጅተን ለቀጣዩ ትውልድ የአሸናፊነትና ነጻ ሕዝብ ታሪክ ባለቤትነታችንን እናስቀጥላለን።
በዛሬው ዕለት የህያው ጀግኖቻችንን የልደት ቀን በማስመልከት ❝እንኳን ተወለዳችሁ❞ የምንላቸው እንደወትሮው በአዳራሽ ተሰብስበን ሳይሆን በግንባር ተሰልፈን ነው፡፡ በተለይም ወጣቶች ለወገን ጦር አስተማማኝ ደጀን ከመሆን አልፈን፣ የወረረንን ደመኛ ጠላት በዱር በገደሉ እየተፋለምን፣ መግቢያ መውጫውን አሳጥተን በማንበርከክ ነው ❝እንኳንም ተወለዳችሁ❞ የምንላቸው፡፡
ለህያው ጀግኖቻችን የምናቀርበው የልደት ስጦታ የታሪክ ውርሳችንን ለማስጠበቅ በህልውና ትግሉ ላይ ጀብዱ በመፈጸም ነው፡፡ የትውልድ አደራቸውን እንደተቀበልን የምናስመሰክረው በቅጥረኛ ባንዳዎች መቃብር ላይ በመቆም ነው።
የህያው ጀግኖቻችንን የታሪክ ውርስ፤ ቅጠረኛ ባንዳን ድል አድርገን፣ እንደ ትውልድ በአዲስ ድል ተወልደን፣ ክብራችሁን እናስጠብቃለን!
ኢትዮጵያችንም አትደፈርም!!