
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 11/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሽብርተኛውን ህወሓት ቡድን ጥፋት ለማስፈጸም ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሲገቡ የነበሩ 32 የጥፋት ተላላኪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አብልአዚም መሃመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በቁጥጥር ስር የዋሉት በሽብርተኛው ህወሓት አስተባባሪነት ከሀገር ውጭ ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱ ናቸው።
ግለሰቦቹ በክልሉ ጠረፍ አካባቢ አሶሳ፣ ኩርሙክ ወረዳዎች በኩል ድንበር አቋርጠው ባለፉት ሶስት ተከታታይ ቀናት ወደ ክልሉ ሲገቡ መቆጣጠር መቻሉን አስታውቀዋል።
በቁጥጥር ስር ከዋሉት አብዛኞቹ ወጣቶች ሲሆኑ በሽብርተኛው ቡድን “የፌዴራል መንግሥት ተዳክሟል” በሚል የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ተታልለው ወደ ጥፋት መንገድ የገቡ ናቸው ብለዋል።
እንዲሁም በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ሲሳተፍ የነበረው የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ (ቤህነን) ምክትል አመራር እና ፓርቲውን ወክለው በምርጫ የተሳተፉ እጩዎች፣ አሶሳ ከተማ ተቀምጦ ጥፋቱን ሲያስተባብር የነበረ የአሸባሪው አባል እንደሚገኙበት አብራርተዋል።
የጥፋት ቡድኑ ተላላኪዎች የያዙት የጦር መሣሪያ፣ ቢላዋ፣ ገጅራ፣ ላፕቶፕ ካምፒዩተር፣ የባንክ ደብተር እና ሌሎችም ቁሳቁሶች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ግለሰቦቹን መቆጣጠር የተቻለው በአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ሀገር መከላከያ እና ክልሉ ልዩ ኀይል እንዲሁም ሚኒሻ አባላት ጋር ባረጉት የተቀናጀ ጥረት መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደም አሸባሪው ህወሓት በክልሉ ያለምንም ካፒታል በግብርና ኢንቨስትመንት ስም ተሰማርቶ ከፍተኛ ገንዘብ ከልማት ባንክ ዘርፏል ያሉት ኮሚሽሩ በተለይ የክልሉን ወርቅ ሃብት በህገ-ወጥ መንገድ ማጋበሱን አስታውሰዋል።
ከለውጡ በኋላ የክልሉ ህዝቦች በተለይም ወጣቱ በስፋት ተደራጅቶ የተፈጥሮ ማዕድኑን በማልማት ኑሮውን መቀየር መጀመሩን ጠቁመው ይህ ለአሸባሪው ህወሓት እንዳልተመቸው አስረድተዋል።
በሽብር ቡድኑ የጥፋት ሴራ በተለይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በህዳሴ ግድብ ጉዳይ በሚመጣበት ማንኛውም ጫና እንደማይደራደር የገለጹት ኮሚሽሩ የክልሉ ሕዝብ የጥፋት ተላላኪዎችን አሳልፎ የሰጠው ይህንኑ አቋም በመያዝ እንደሆነ አመላክተዋል።
ክልሉ ከፌደራል የጸጥታ ኅይሎች በመቀናጀት የጥፋት ቡድኑ ሀገር የማፍረስ እቅድ አስቀድሞ ማክሸፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ኮሚሽነር አብዱልአዚም አስታውቀዋል፤ ህብረተሰቡም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m