
በተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ኩባ ላደረገችው ድጋፍ ከኢትዮጵያ ምሥጋና ተቸራት፡፡
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 11/2013 ዓ.ም (አሚኮ) እኤአ ሐምሌ 13/2021 በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ኩባ ለነበራት ኢትዮጵያን የሚደግፍ አቋም በኩባ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ምሥጋና አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የምክር ቤቱ ውሳኔ በሰብዓዊ መብቶች ተቋም እና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እየተካሄዱ ያሉትን ምርመራዎች ግምት ውስጥ ያላስገባ መሆኑን አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ኩባ የኢትዮጵያን እውነት የሚደግፍ አቋም ማንጸባረቋ ነው የተገለጸው፡፡ ይህም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የሚመጥን መሆኑ ነው አምባሳደሩ ያነሱት፡፡
በ1970 ዎቹ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ኩባ የነበራትን አስተዋጽዖ በመጥቀስ የሀገራቱ ግንኙነት ታሪካዊ ፣ በደም ጭምር የተሳሰረ እና ጽኑ መሠረት ያለው መሆኑን አምባደር ሽብሩ ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በጤና ፣ በትምህርት ፣ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና መሰል በርካታ መስኮች ላይ የትብብር መርኃግብሮችን በማስፈፀም የሁለትዮሽ ግንኙነቱ እንዲጠናከር መደረጉንም አንስተዋል።
አሸባሪው የትህነግ ቡድን በአማራ እና በአፋር ክልሎች ወረራ በመፈጸም ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጭፍጨፋ እና ዘረፋ መፈጸሙን ያነሱት አምባሳደሩ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ የሕግ ማስከበር ሥራ እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሽብርተኛው ትህነግ ሕጻናትን ጭምር ወደ ጦርነት እያሰለፈ መሆኑን እና ልጆቻቸውን ወደ ጦርነት ለመላክ ፈቃደኛ ያልሆኑ የትግራይ ቤተሰቦች የዕርዳታ ምግብ እስከመከልከል መድረሱንም አንስተዋል፡፡
አምባሳደር ሽብሩ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውኃ ሙሌት በተፋሰሱ ሀገራት ላይ ጉዳት ተጽእኖ ሳያደርስ መሞላቱን አስገንዝበዋል፡፡
በዚህ ረገድ ያለው ድርድርም በአፍሪካ ኅብረት እንዲካሄድ የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም መሆኑን ግልጽ ማድረጉን አምባሳደር ሽብሩ ገልጸዋል፡፡
በየማነብርሃን ጌታቸው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ