
ለአሻጥረኞች እኩይ ሴራ መሳሪያ እንዳንሆን እንጠንቀቅ፡፡
የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግሥትና ሕዝብ ሀገራችን ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ ከገጠማት ፈተና ለመታደግ ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት ርብርብ በማድረግ ላይ ነው፡፡
በአንድነት ከቆምንና ተደምረን ከተጋን ይህን ፈተና አሸንፈን፣ ችግሩን ወደ ዕድል፣ ዕድሉንም ወደ ታላቅ ድል ለውጠን፣ ሀገራችንን ወደ የሰላምና የብልጽግና ከፍታ ማማ ላይ እንደምናደርሳት ለአፍታም አንጠራጠርም፤ ኢትዮጵያ ሀገራችን ሁሌም ምጥና ጣር ቢበዛባትም እንደብረት እየጠነከረች በፈጣሪዋና በሕዝቦቿ ጥረት ከሚገጥሟት ፈተናዎች በማይታመን ሁኔታ ትንሣኤዋ እየደመቀ የምትሄድ ሀገር ናት፡፡ ከለውጡ ወዲህ ያጋጠሟትም ፈተናዎችና ያለፈችባቸው መንገዶች ይህን ሐሳብ የሚያጠናክሩ ናቸው፡፡
የክልላችን ሕዝብ የሀገሩን ሉዓላዊነትና አንድነት ለማስከበር ከዳር እስከ ዳር በተንቀሳቀሰበት በዚህ ወሳኝ ወቅት አሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ ከኢትዮጵያና ከሕዝቦቿ በተጻራሪ በመቆም የያዙትን የጥፋት ተልእኮ በግልጽ መናዘዝ ጀምረዋል፡፡ እነዚህ ሁለት ያበቃላቸው የሽብር ኃይሎች በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ቢዶልቱም ኢትዮጵያን የሚነቀንቅ ድፍረትም፤ጉልበትም ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ለዚህም ነው የክልላችን ሕዝብ ‹‹ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ፤ የትም፣ መቼም በምንም›› በሚል መሪ ቃል እየተመራ የህልውና ዘመቻ ላይ የሚገኘው።
ይህን ቁርጠኝነቱን ከዚህ በፊት ባልታየ መልኩ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ በማውለብለብና በመልበስ ጭምር በየከተሞቹ ባካሄዷቸው ደማቅ ሰላማዊ ሰልፎች፣ ስብሰባዎች እያረጋገጠ ነው።
የሕዝቡ የደጀንነት ማረጋገጫ ቃል በመግባት ብቻ የተገታ አይደለም በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች መከላከያን እየተቀላቀሉ ቃልን በተግባር ማሳየት ጀምረዋል። የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ሠራዊቱን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ።
ሕዝቡ መከላከያን በገንዘብም በአይነትም እየደገፈ ነው። እናቶች ልጆቻቸውን ስመው ወደ ግንባር ሸኝተዋል። በዚህ ብቻ ሳያበቁ ፤ የሚችሉትን ያህል የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ በተጓዳኝ ወገባቸውን አስረው ለሠራዊቱ የሚውል ስንቅ እያዘጋጁ ናቸው።
ባለሀብቶች የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በመተባበር ሰንጋዎችን፣ በጎችን፣ ፍየሎችንና ገንዘብ ሠራተኞችም የወር ደመወዛቸውን እየሰጡ ናቸው።
ይህ የሕዝቡ አጋርነት ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ትልቅ ስንቅና ደጀን ነው።
ይሁን እንጂ ሕዝባችን ለዘመናት ከተጣበቀው ድህነትና ከዚህ ከሚመነጨው ጉስቁልና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ከፍሎ ለመሻገር በተነቃቃ ማንነትና እልህ ውስጥ ቢገኝም ለግል ጥቅም ሲሉ ሀገራቸውን ክደው ከጥፋት ሀይል ጎን የሚያሰልፋቸውን ተግባር የሚሸርቡና የሚጎነጉኑ ብለውም የሚሳተፉ ጥቂት የሚባሉ የእናት ጡት ነካሾች አልታጡም፡፡ ይህ በራስ ወዳድነት ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብና ከዚህ የሚመነጨው ክፋት የሚፈጥረው ሰብአዊ ቀውስ እና ሀገር ማፍረስ የቱን ያህል ንጹሐንን ዋጋ እያስከፈለ እንደሆነ ለመረዳት ከሞቀ ቀዬአቸው ወጥተው በጊዜያዊ መጠለያ ላይ ያሉ ዜጎችን መመልከት በቂ ነው።
በሀገር ጠላትነት ከውስጥም የተሰለፈ ይሁን ከውጭ ዓላማው ሕዝብን ማጥፋት ማውደም እና ማዋረድ ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እንደ ሀገርና እንደ ህዝብ በዝምታ የሚታይ አይሆንም፡፡ ይህ የሕዝቡ ትብብርና ጀግንነት ያስደነገጣቸው የውስጥና የውጪ የጥፋት ኀይሎች ባወጁት ይፋዊ ጦርነትና በጀመሩት የሽብር ተግባር መዝለቅ ሲያቅታቸው እና ማጣፊያው ሲያጥራቸው እንደ አበደ ውሻ ሁሉንም መልከፍና መንከስ ቀጥለውበታል፡፡ ተባባሪዎቻቸው የሆኑ የወቅቱ ሁኔታ መልካም አጋጣሚ የፈጠረላቸው መስሏቸው የማይገባቸውን ሀብት ለማካበት እና በሕዝብ ላይ የኑሮ ጫና እንዲፈጠር ለማድረግ የሚሯሯጡ ጥቂት ስግብግብ ነጋዴዎች እንዳሉ እየታዩ ነው፡፡ እነኚህ ራስ ወዳድና ለሕዝብና ለሀገር ወገናዊነት የሌላቸው ግለሰቦች በኢትዮጲያ ላይ ይፋዊ ጦርነት ከከፈተው ከአሸባሪው የሕወሓት ጁንታ የሚለዩ አይደሉም፡፡ ስለዚህ ያለ ዕውቀት ሀብት ለማካበት ብቻ በዚህ የሀገርና ሕዝብ ክህደት ተግባር ውስጥ የተሳተፋችሁ ነጋዴዎች ለአሻጥረኞች እኩይ ሴራ መሳሪያ እንዳትሆኑ እጃችሁን በፍጥነት እንድትሰበስቡ መንግሥት ያሳስባል፡፡ በአመለካከትና በድርጊት የባንዳነትና የተላላኪነት ተግባር ለመወጣት የንግዱን ሥርዓት ለማዛባት በሕዝብ ላይ ኑሮውን ለማክበድ በዘመታችሁ ቡድኖች ላይ ግን መንግሥት አስተማሪና የማያዳግም እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ያስታውቃል፡፡
ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን መሰረት ያደረገ የዋጋ ንረት እንደተጠበቀ ሆኖ በጥቂት ስግብግብ ግለሰቦች ራስ ወዳድነት የሚፈጠረው የዋጋ ጭማሪ ግን ሕዝብ ከመንግሥት ጎን በመሆን ሕገወጥ የምርት ክምችት እና የግብይት ሥርዓቱን ለማዛባት የሚደረገውን አሻጥር በማጋለጥ እንዲተባበር ጥሪ እናደርጋለን፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ከሕዝብ እና ከመንግሥት የተሰጠውን ኀላፊነት ችላ በማለት የሕዝቡን መብትና ጥቅም በሚጎዳ ሀገርን በሚያፈርስ ተግባር ውስጥ ሲሳተፍ በተገኘ የመንግሥት የሥራ ኀላፊም ሆነ ባለሙያ ላይ መንግሥት ጥብቅ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ለማሳሰብ እንወዳለን።
ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ፤የትም፤መችም፤ በምንም!
የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግሥት
ነሐሴ 11/2013