
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 11/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከሰማህ ምከረው፣ በዘመድ በአዝማድ አስመክረው፣ ለፍቅር ስትል ቻለው፣ ልብ ይሰጠው እንደሆነ ታገሰው፣ ቀን ስጠው፣ እምቢ ካለ ግን ውገረው፣ ተፈጥሮን ተመክሮ አያድነውምና ክንድህን አያሳዬው። ጀግንነትክን ሲፈታተን፣ የትዕግስትህን ወሰን ሲጥስ፣ መንደርህን ሲያረክስ አይሆንም በለው። የጀግና ልጅ ጀግና ነህና መንደርህን አርክሶ፣ የትዕግስት ወሰንህን ጥሶ የሚመጣውን ክንድህን አበርታበት፣ አፈሙዝህን አዙርበት፣ ምላጭህን ሳብበት፣ ፊትክን አጥቁርበት፣ ክንድህን ጣልበት።
አንተ ቴዎድሮስ ለክብርና ለሀገር ፍቅር፣ ለአንድነት፣ ለኢትዮጵያዊነት፣ ከምንም በላይ ለኩራት ሞቶ ያሳየህ፣ ገብርዬ እስከ ሞት ድረስ ታምኖ መታመንን ያረጋገጠልህ፣ ፅናትን የሰጠህ፣ የጦር ስልትን የነደፈልህ፣ ምኒልክና ጣይቱ ዓድዋ ላይ ዘምተው አዘምተው ያሸነፉልህ፣ ታሪክህን በወርቅ ቀለም ያፃፉልህ፣ ክብርህን ከማማው የሰቀሉልህ፣ እነ ሚካኤል ለሀገር ፍቅር የተዋደቁልህ፣ በጀግንነታቸው ታሪክ የሠሩልህ፣ እነ በላይ፣ እነ ቢትወደድ አዳነ፣ እነ አሞራው ውበነህ እልፍ አዕላፍ ጀግኖች ጠላትን መትተው፣ በደማቻውና በአጥንታቸው ድንቅ ሀገር ያቆዩልህ፣ ከጀግኖች የተወለድክ፣ በጀግንነት ያደክ፣ በጀግንነት የኖርክ፣ ለጀግንነትህ የተፈጠርክ ነህ።
የሞከረህ ጠላት ሁሉ ሞቷል፣ የነካካህ ሁሉ በየደረሰበት ቀርቷል፣ አንገትህን ሊያስደፋህ የከጀለው ሁሉ አንገቱን ደፍቷል፣ ለወሬ ነጋሪ፣ ዜና አብሳሪ ከጠላቶችህ የተመለሰ አልነበረም። ሳንጃህ ወጋቸው፣ አፈሙዝህ በላቸው፣ መውጨው ጠፋባቸው፣ የሀገርህ አፈር አዋሃዳቸው፣ ምስጥ አነኮታቸው። እንኳን አባቶችህና እናቶችህ የኖርክባቸው፣ እግርህ የረገጠባቸው፣ ተራራዎች፣ ሸንተረሮችና ሜዳዎች ሁሉ ለጠላት አይመቹም፣ አስረው ያስቀራሉ፣ በየደረሱበት እየተመቱ ይቀብራሉ። ጠላትን አያላውሱም፣ አያንቀሳቅሱም። ለዚያም ነው “ሀገራችን ጎንደር፣ ሀገራችን ጎጃም፣ ሀገራችን ሸዋ ሀገራችን ወሎ ያ ግድም ያግድም፣ አንጋዳው ክፉ ነው አያረማምድም” ተብሎ የተገጠመለት።

ማንስ ያሸንፈሃል፣ ማንስ ችሎ ይጋፋሃል፣ ለአንተ የተፈጠረ ማሸነፍ ብቻ ነውና። እንደ አባትህ ጠላትህን መልስ፣ ወደፊት ገስግስ። አንተም በዘመንህ ለገናና ታሪክ ተነስ። ጠላቶች እንደ አሸን ይበዛሉ፣ ድንቋን ሀገር፣ ኩሩውን ሕዝብ እንዴት አድርገን እንበትነው ብለው ይመክራሉ፣ ጀንበር በጠባች ቁጥር ይዶልታሉ። ለእቅዳቸው መሳካት ይሆናል ያሉትን ሁሉ ይፈፅማሉ። ታዲያ እቅዳቸውና ምኞታቸው ከኢትዮጵያዊያን፣ እሴት፣ ሃይማኖት፣ ፅናት፣ ጀግንነት እና አይበገሬነት በታች ነው።
በጀግኖች ብልሃት ምኞታቸው ቅዠት ይሆናል፣ እቅዳቸው ይከሽፋል። የጀግኖችን ሡሪ የሚያስፈታ፣ አንበሶችን የሚረታ ጠላት በየዘመናቱ አልተፈጠረም። አይፈጠርም። በታተናቸው ሲሉ የሚሰባሰቡ፣ ለያየናቸው ሲሉ የሚተባበሩ፣ በደም ማፅናት፣ በአጥንት መሥራት የሚችሉ ድንቅ ጀግኖች። የምትወዳት ሀገርክን፣ የተወለድክባት፣ እትብትህ የተቀበረባት፣ ተቀማጥለህ ያደክባት፣ አድገህ ወግ ማዕረግ ያየህባት ርስትህን፣ የምትሳሳላትን ልጅህን፣ የአካል ክፋይ የሆነችውን ሚስትህ ሊደፍር፣ ሊያዋርድ ሲመጣ በእርስት፣ በነፃነት፣ በማንነት፣ በሚስትና በኢትዮጵያዊነት ድርድር የለም በለው።
አንቺም ቢሆን ክብርሽን ሊያዋርድ፣ ልጅሽና ባልሽን ሊገድል የመጣውን አሻፈረኝ በይበት። ለክብር የሞተ አባትና እና እናት እንጂ ክብሩን የሰጠ የላችሁምና። ጠላት የበዛብህ፣ መሰናክሉ የጠናብህ ከጠላትህ የተሻልክ፣ ቀድመህ የሄድክ፣ በሁሉም ነገር የበለጥክ ስለሆንክ ነው። በየዘመናቱ የቀጠቀጥካቸው ጠላቶችህ የዘሩት፣ አድርግ ብለው የላኩት፣ በታሪክህ ግዝፈት ልቡ የሚያር ጠላት ዛሬ ላይ ተነስቶብሃል። መክረኸው፣ አስመክረኸው፣ ታግሰኸው፣ ያልሰማህ፣ በዘመናቱ በክፋቱ ልብህን ያደማህ ነው ጠላትህ።
እንደ ውቅያኖስ የሰፋውን ትዕግስትህን፣ እንደ ተራራ የገዘፈው ጀግንነትክን፣ እንደ አለት የፀናው አቋምህን ያላወቀው ክፉ ጠላት በየዙሪያህ ከቦሃል። ከተቻለው ሊያጠፋህ፣ አንገትህ ሊያስደፋህ ተነስቷል። አንተም ጠላትህን እየቀጣህ በመጣህበት ስልትህ፣ በሚያስደነግጠው ግርማህ ግረፈው፣ አሳደው፣ አንገቱን አስደፋው። በየዘመናቱ ሀገርህን ደፍረው፣ ወሰኑን አልፈው፣ ወንዙን ተሻግረው የመጡትን ሁሉ ለወሬ ነጋሪ ሳታስቀር በዱር በገደሉ እንዳስቀረሃቸው ሁሉ ዛሬም እንደዚያው አድርግ። መንገዳቸውን አጨልምባቸው፣ ዘመናቸውን ቋጭላቸው፣ ከአፈሩ ጋር ደባልቃቸው። ጠላትን መቅጣት፣ ሀገርን ማፅናት፣ ወገንን ማኩራት መገለጫህ ነውና።
ኢትዮጵያ ለአማራ የሚናገርባት ቋንቋው፣ የሚያጌጥባት ካባው፣ ከአባት የተቀበላት ለልጅ የሚያስረክባት አደራው፣ ከምንም በላይ መመኪያው፣ ከዘመን ዘመን መኩሪያው፣ የሚኖርላት ቃሉ፣ የማይከዳት ውሉ ናት። ደም በማፍሰስ፣ አጥንት በመከስከስ ሀገር ማኖርን እንጂ ሀገር መሸጥን፣ ያበላ እጅ ያጠባን ጡት መንከስን አልተማረም አማራ። አማራ ገጥሞ ያላሸነፈበት፣ ገድሎ ያልፎከረበት፣ ጥይት እንደ አሸዋ ያልዘራበት፣ ጠላት እንደ አውሬ ያላባረረበት፣ ምሽግ ያልሠበረበት ግንባር የለም። ሲገጥሙት ይማታል፣ ሌላውን ለማኖር ይሞታል፣ ሞቶ ማኖርን፣ ኮርቶ መክበርን፣ ጀብዱ ሠርቶ በታሪክ መዘከርን ያውቅበታል።
በውሸት የኖረ፣ ለውሸት የዘመረ፣ በስርቆት የከበረ ዘራፊ ጠላት ደጅህ ድረስ መጥቷልና በውሸት ኖሯል የእውነት ቅበረው። እድሜው ይበቀዋል። ከዚህ በላይ እድሜ አትስጠው፣ ምክርም፣ ፍቅርም፣ ክብርም አያስፈልገውም ሙትን ይዞ እንዳይሞት ወደ ሞት ገፋ ማድረግ ነው።
“ተመክሮ ተመክሮ ጠላት ልብ ካጣ
ንገረው ለአማራው አስተካክሎት ይምጣ” አዎን ለአማራው ንገረው ያበጠውን አፈንድቶት፣ የጎበጠውን አቃንቶት፣ የተበላሸውን አስተካክሎት ይምጣ። ንገረው ለእርሱ ልኩን ያሳየዋል፣ ንገረው ለዚያ ጀግና በየደረሰበት ወደ ማይቀረው ይሸኘዋል። ለዓመታት የጠላህ፣ ያስጠላህ፣ የበደለህ፣ ያንገላታህ፣ አሁንም ከበደሉ ያላረፈልህ ጠላትህ መዳፍህ ውስጥ ገብቷል። ውሳኔው በአንተ ላይ ሆኗል።
አማራ በቀለበት ውስጥ የገባውን ጠላቱን አደብ የሚያስይዝበት ጊዜው ደርሶለታል። አሁን ላይ በየዋሻው እየተሹለከለከ ሊያሸብር ይጥራል፣ በምታውቃቸው ሥፈራዎች እየቃኘህ ጠላትህን ቅጣ፣ በገባበት እንዳይወጣ አድርገው። አንተ እንኳን በውሸት በሞቀ ጦርነት የማትደናገጥ ልበ ደንዳና ሕዝብ ነህ። የጠላቶችህ ወዳጆች በሚያስወሩት ወሬ ሳትሸበር ፣ በጦር ሜዳ ሳትበገር፣ ጠላትህን ለመጨረሻ ጊዜ ቅበር፣ ድልህንም ከማማው በላይ ከፍ አድርገህ አክብር።
ብዙ ፈተናዎች ሊገጥሙህ ይችላሉ፣ ፈተናዎቹ ግን ከአንተ ጀግንነት፣ ብልሃት፣ አንድነትና ቆራጥነት ሁሉ በታች ናቸው። በአባቶችህ ወኔ ተነሳስተህ፣ የአባቶችህን ቃል ኪዳን ጠብቀህ፣ አደራቸውን አክብረህ ሀገርን አስከብር፣ ወገንን ከሞትና ስቃይ አድን። ከቤትህ ስትነሳ እንደምታሸንፍ አረጋግጥ፣ ከአንተ ጋር እውነት፣ ጀግንነት፣ አንድነት፣ የፀና እምነት፣ የማይናወጥ ኢትዮጵያዊነት አለና።
የመጨረሻውን የድል ጥግ የምታጣጥመው፣ ከጠላት መቃብር ላይ ቆመህ በጋራ የምትዘምረው፣ የድልህን ችቦ ከፍ አድርገህ የምታበራው፣ ስለ ጀብዱ የምትነግረው የምትዘክረው አንተ ነህና። የጥንቸል መንጋ ለአንበሳ ስጋት አይሆንም። አንተ እንደ አንበሳ የጀገንክ፣ እንደ ነብር የፈጠንክ ታላቅ ሕዝብ ነህና ክንድህን አንሳ። አካባቢህን በደንብ አስስ፣ ወደ ፊት ገስግስ። የተላከው አይደለም የላከውን ቀጥተህ መልሰሃልና፣ ተላላኪው ጠላትህ ከአንተ በታች ነው። ታዲያ የጠላትህ እድሜ እንዳይረዝም በኅብረት ዝመት፣ በአንድነት ክተት። የጠላትህን እስትንፋስ ለዘላለም አቋርጥበት። ወጣም ወረደም ሁሉም ነገር በአንተ አሸናፊነት ይጠናቀቃል። በዚህ ጥርጥር አይገባህ።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ