
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 10/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎንደር ዞን ሕዝብ ለመከላከያ ሰራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኀይል፣ ለሚሊሻ፣ ለፋኖ እና የክተት ጥሪውን ተቀብለው በማይጠብሪ ግንባር ሽብርተኛውን የህወሃት ቡድን በመፋለም ለሚገኙ ኀይሎች ድጋፍ አደረጉ።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በግንባር ተገኝተው ድጋፉን ካስረከቡ በኋላ እንደተናገሩት፣ ህዝቡ ከ83 ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ በሁሉም ግንባሮች ለተሰለፈው ኀይል ድጋፍ አድርጓል ።
በማይጠምሪ ግንባር ለተሰለፈው ኀይልም ለአሁኑ የሚሆን 78 የእርድ ከብቶችን፣ 18 ፍየልና በግ ማስረከባቸውንና በቀጣይነትም የህልውና ዘመቻው እስከሚጠናቀቅ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
የመከላከያ ተቋምን ለማጠናከር የሚደረገውን ርብርብ ለመደገፍ በዞኑ የሚገኙ ወጣቶችን በመመልመል ወደማሰልጠኛ መላካቸውን የተናገሩት አስተዳዳሪው አቶ ደሳለኝ ጣሰው፣ ዞኑ ሀገራችንን ከሱዳን ጋር የሚያዋስን እንደመሆኑ አሁን ላይ ካሉ የፀጥታ ስጋቶች አንፃር መላው የዞኑ ህዝብ ኢትዮጵያን ለማዳን ከተሰለፉ ኀይሎች ጋር በፅናት በመቆም ማንኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የምዕራብ ዕዝ ዕደላ ኀላፊ ሌ/ኮ አሸብር ሽፈራው በበኩላቸው፣ በግንባር የተሰለፈው ኀይል ህዝቡ እያደረገለት ባለው ድጋፍ ተነሳስቶና በግዳጁ ተግቶ የጁንታውን ግብዓተ-መሬት በማፋጠን ላይ መሆኑን ተናግረዋል ።
ባለፉት ጊዜያት ከኦሮሚያና ከሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች የተላኩትን ድጋፎች ሰራዊቱ በተገቢው እንደተጠቀመ ሁሉ፣ የምዕራብ ጎንደር ዞን ህዝብም ላደረገው አለኝታነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ምንጭ: የመከላከያ ሠራዊት
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ