
የሕዝብን ማንነት በማጥፋት የህልውና አደጋ የሆነውን ሽብርተኛ ቡድን ለመደምሰስ በሚደረገው ዘመቻ ሁሉም እንዲሳተፍ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 10/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ሃይማኖት፣ ባህል፣ ታሪክ፣ እምነት፣ ወግና ልማድ አንድ ማኅበረሰብ ማንነቱን የገነባባቸው መሰረቶች ናቸው፡፡ ሩህሩህነቱ፣ ይቅር ባይነቱ፣ ጀግንነቱ፣ ለሀገሩ ያለው ፍቅር ማንነቱን ያዋቀረባቸው እስቴች እንደሆኑ ግልጽ ነው። ህልውና የሚባለውም እነዚህ ሁሉ ተደምረው እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ። የአማራ ሕዝብም እንደ ሕዝብ በእነዚህ ዕሴቶች የሚገለፅ ማንነት ያለው ነው። የአንድ ሕዝብ ህልውና አደጋ ላይ ነው ሲባልም እነዚህ የማንነት መሰረቶቹን ሊነጠቅ ነው ማለት ነው፡፡ ሽብርተኛው ትህነግ አማራን እንደ ሕዝብ በጠላትነት ፈርጆ ሲነሳ የማንነቱ መሰረቶች የሆኑትን መዋቅሮች በማጠልሸት እና በማንቋሸሽ ነበር የጀመረው።
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያነጋገራቸው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኀላፊ እና መምህር ባምላክ ይደግ (ዶ.ር) ሽብርተኛው ትህነግ ከምስረታው ጀምሮ የአማራን ብሎም የኢትዮጵያዊነት እሴትን ለማጥፋት የሄደበትን ርቀት ገልጸዋል፡፡ በዚህም የአማራ ሕዝብ ሃይማኖተኛ መሆኑን እንደ ኋላቀርነት፣ ይቅር ባይነቱን እንደ ሞኝነት፣ ለፍቅር ሟች መሆኑን እንደ ደካማነት፣ ሰብዓዊነቱን እንደ ሽንፈት፣ ለተጎዱ መታገሉን እንደ ፅንፈኝነት እየቆጠረ አማራ የራሱ የሆኑ ማንነቶቹን እንዲተዋቸው ለማድረግ ሲሠራ ኖሯል ብለዋል።
ዶክተር ባምላክ አሁን ከወራሪው እና ሽብርተኛው ትህነግ ጋር እየተደረገ ያለው ተጋድሎ እነዚህን ማንነቶች ለማዳን መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል ብለዋል። ሽብርተኛው ትህነግ የአማራ ሕዝብ ለራሱ የሚሰጠውን የእችላለሁ መንፈስ እንደ ትምክህት፣ ሀገሩን ከወራሪ ለማዳን ያደረገውን ተጋድሎ ደግሞ እንደ ነፍጠኝነት /አሉታዊ ትርጓሜ እየሰጠ/ ጥላሸት ሲቀባ መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡
ይህም ማንነቱን የጣለ እና ሽብርተኛ ቡድኑ ራሱ እንደፈለገው የሚጠመዝዘው ሕዝብ ለማድረግ አስቦ እንደነበር ዶክተር ባምላክ አስረድተዋል። ሽብርተኛው እና ወራሪው ትህነግ አማራ በሀገር ግንባታ ውስጥ ያበረከተውን ጉልህ አስተዋፅኦ ሲነጥቀውና ሲክደው መኖሩንም ምሁሩ አንስተዋል። ሽብርተኛው ትህነግ እንደ ሀገር አማራ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በመሆን የሚጋራቸውን ደማቅ ታሪኮች በማናናቅ እርስ በርስ የተከፋፈለ እና የተቃቃረ ሕዝብ ለመፍጠር ያልፈነቀለው ድንጋይ እንደሌለም ዶክተር ባምላክ ጠቅሰዋል።
እናም ይላሉ ዶክተር ባምላክ “͑͑በህልውናችን የመጣ ነው’ ሲባል እምነታችንን ያንቋሸሸ፣ ታሪካችንን ያጎደፈ፣ ባህላችንን የተጠየፈ፣ ለሀገር ያለንን ፍቅር እንደ ሞኝነት የቆጠረ መሆኑን በመረዳት ይህንን አሸባሪ ቡድን ለመደምሰስ ሁሉም በንቃት የህልውና ዘመቻው ላይ ተሳታፊ መሆን ይኖርበታል” ሲሉ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፡- ፈረደ ሽታ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ