ትውልዱ የአደራ ቃሉን በድል ይወጣል!

250
“ይገድሉኛል። ከገደሉኝ ትግሌን አደራ። በተለይ የእኔ ትውልድ ትግሌን አደራ”
ሰማዕቱ ሳሙኤል አወቀ
ሳሙኤል አወቀ ገና በለጋ ዕድሜው የሰላማዊ ትግሉን ተቀላቅሎ የሚያምንበትን የሠራ የራሱን አሻራ ያሳረፈ የትግል ሰማዕት ነው፡፡ ሳሙኤል ለትግል ዓላማው ሳይታክት፣ ጠላቶቹን ሳይፈራ እስከመጨረሻው ለቃሉ የታመነ የትውልዱ ጀግና ነው። ከትግል ወደኋላ ማፈግፈግን፣ መስዋእት እሆናለሁ ብሎ መሸሽን የተጸየፈ የዘመኑ አርበኛ ነው። ለሕዝብና ለሀገሩ ሲል የማይተካ ሕይወቱን ሳይሳሳ የሰጠ ሰማዕት በመሆኑ በትውልዱ ሲዘከር ይኖራል። ጠላቶቹ እንደሚገድሉት በየቀኑ እየዛቱበት፣ እየደበደቡት፣… ወደኋላ ማለትን ያልፈለገ የትግል ዓላማ ሰው ነበር። ሳሙኤል አወቀ እርሱ ቢገደል እንኳን ትግሉ በእርሱ ትውልድ እንደሚቀጥል አምኖ ለወጣቱ አርዓያ በመሆን ህይወቱን አሳልፎ የሰጠ፣ በሕይወቱ የትውልዱን የነጻነት ራዕይ ለማስቀጠል የቆረጠ የዘመናችን ጀግና ነው።
ሳሙኤል አወቀን ለረዥም ጊዜ ክትትል ያደርግበት የነበረው ጌታቸው አሰፋ ይመራው የነበረው የብሔራዊና መረጃና ደኅንነት ተቋም ነበር፡፡ ይህ የአፈና ተቋም በምን አይነት ሴራ እንደገደለው ከለውጡ በኋላ የክልላችን የጸጥታ ኃይል ከባለድርሻ አካላት ጋር ሆኖ ግድያውን አጣርቷል፡፡ መረጃውንም ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
እነ ጌታቸው አሰፋ ያሰማሩት ገዳይ ቡድን ሲከታተለው፣ ሲያዋክበው ሳሙኤል አወቀ “ይገድሉኛል” ብሎ ቀድሞ መፃፉ የሚታወቅ ነው። እንደሚገድሉት እያወቀ አልፈራም፣ አልሸሸም፡፡ በወቅቱ ሕዝባዊነትን መሰረት ያደረገውን የትግል ዓላማውን አጠናክሮ ነበር የቀጠለው፡፡
ሞትን የናቀው ሰማዕቱ ሳሙኤል ቢገድሉት ምን መደረግ እንዳለበት ለዘመኑ ወጣት ቋሚ መልዕክት አስተላልፎ መስዋእትነት ያስከፈለውን ትግል በመቀጠል ቁርጠኝነቱን በተግባር አሳይቷል።
ሳሙኤል ትግሉ ከሚቆም መስዋእትነት ከፍሎም ዓላማውን ማስቀጠልን ነበር የመረጠው። ለዚህም ነበር በታሪክ ሲጠቀስለት የሚኖረውን መልዕክቱን ለዘመን ተጋሪ ወጣቶቹ ያስተላለፈው፡፡
ሳሙኤል አወቀ መስዋእትነት ከመክፈሉ ቀደም ብሎ ባስተላለፈው መልዕክት እንዲህ የሚል የአደራ ቃል አስቀምጧል፡- “ይገድሉኛል። ከገደሉኝ ትግሌን አደራ። በተለይ የእኔ ትውልድ ትግሌን አደራ” ይህ ነበር የሰማዕቱ የአደራ ቃል። ሳሙኤል በራሱ ተነሳሽነት እንጅ ማንም አደራ ሰጥቶት ትግል አልጀመረም። እሱ ግን በተግባር ቆራጥነትን አሳይቶ ለዘመን ተጋሪዎቹ የትግል አደራ አስቀምጦ አልፏል፡፡ የሳሙኤል አደራ ከባድ ነው።
ሳሙኤል ወደፖለቲካ ትግል ሳይገባ በጥብቅና ሙያው ብቻ የግል ሕይወቱን መኖር ይችል ነበር፤ ይሁንና የወጣበት ሕዝብ መጠቃት የእግር እሳት ሁኖበት ወደሰላማዊ ትግሉ ለመግባት ተገድዷል፡፡ ጉዞውም እስከ ቀራኒዮ ስለመሆኑ በመስዋእትነቱ አስመስክሯል፡፡ ሕዝብ እየተበደለ የግል ሕይወትን ለማቆየት የሚደረግ የፈሪ ኑሮ ከንቱ መሆኑ ስለገባው እርሱ አልፎ ታሪኩን ለትውልዱ የትግል ዓላማ ጽናት መማሪያ እንዲሆን አድርጓል።
ብዙዎች ለጥቅም አድርው ታሪክ አልባ ሁነው አልፈዋል፤ ሳሙኤል ግን ዛሬም መልካም ስሙ ከመቃብር በላይ ይውላል፡፡ ከጠላት ጋር ሲሠሩ ቆይተው የሞቱት ሕዝብ በባንዳነት እንጅ በጀግንነታቸው አያስታውሳቸውም፡፡
ብዙዎች ተረስተዋል፤ ስማቸው ከተነሳም በአሉታዊ ጎኑ ነው፡፡ ሕዝብ ቀርቶ በፖለቲካ ልዩነት ያላቸው የስጋ ዘመዶቻቸው በቅጡ አያስታውሷቸውም። ገንዘብና ሥልጣን ሲያግበሰብሱ ያለፉ፣ ሕይወታቸው የረከሰ ታሪክ አልባዎች ሁነው አልፈዋል።
የሳሙኤል አወቀ ሕይወት ውድ የሆነው ለሕዝባዊ ዓላማ፣ ያውም በቆራጥነት ያለፈች ሕይወት ስለሆነች ነው። ይች ውድ ሕይወት ከባድ አደራ ጥላብናለች። ትግሌን አደራ ብላናለች። በተለይ በተለይ… የእኔ ትውልድ አደራ ብላ አሳስባናለች።
በዚህ ወቅት ሳሙኤል በሕይወት ቢኖር ጦር ግንባር ከሚሰለፉት ወጣቶች ቁጥር አንዱ እርሱ ነበር። ይሁንና የአማራውን ትውልድ መቅጠፍን የፖሊሲው አካል አድርጎ የተነሳው፣ አማራን መሪ አልባ ማድረግን የፖለቲካ ግቡ አድርጎ ሲሠራ የኖረው ትህነግ ሳሙኤልን በጭካኔ ገድሎታል። የትግል ዓላማ ውርሱ ግን ለትውልዱ ተላልፏል፡፡
ቀድሞውንም መስዋእትነት እንደሚከፍል የሚያውቀው ሳሙኤል ከህልፈቱ ቀደሞ የትግል አደራውን ጥሎብናል፡፡ ያ ጀግና በዚህ ወቅት ቢኖር ወራሪውን ትህነግ ፊት ለፊት ይጋፈጠው እንደነበር ሳይታለም የተፈታ ነው። ትግሌን አደራ ያለውም ቃሉ ዛሬ የአማራ ሕዝብና ኢትዮጵያ የተጋረጠባቸውን አደጋ የሚያጠቃልል ነው፡፡
የትህነግ አውዳሚ ፖለቲካ ከአፈና ወደለየለት የሽብርና ወረራ አድጓል፡፡ ትላንት በበላይነት ይዞት በነበረው መንግሥታዊ የአፈና ተግባሩ የተቆጣው ሳሙኤል ዛሬ በህይወት ቢኖር ይህን ግልጽ የሽብርና ወረራ ተግባር በብረት እንደሚፋለም ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ግና ትውልዱ የትግል አደራ ቃል አለበትና ለቃሉ ሊታመን ግድ ይለዋል፡፡
አሁን የሳሙኤልን አደራ ማስታወስ ያለብን ታሪካዊ ወቅት ላይ እንገኛለን። የሳሙኤልን ከትግል ዓላማ አለማፈግፈግ፣ በጽናት መቆምን፣ ለዓላማ መስዋእት ሆኖ ለሌሎች ነጻነት መኖርን መልመድ ያለብን በዚህ ግዜ ነው። ከመቼውም ጊዜ በላይ የትግል ጽናትና ቁርጠኝነት ውርሱ የሚያስፈልገው በዚህ ወቅት ነው፡፡ የሳሙኤልን የአይበገሬነት ተምሳሌት፣ የሳሙኤልን እያወቀው ለትግል መስዋእት የመሆንን የአባት አደሩ ጀግንነት ፈፅመን መዘከር ያለብን፣ ውድ መስዋእትነት፣ ታዋሽ ታሪክ፣ የማይነጥፍ ጀግንነትን ለማስቀጠል ጊዜው አሁን ነው!
ይህ ትውልድ የሳሙኤል አወቀን አደራ የማስጠበቅ ታሪካዊ ኀላፊነት ትክሻው ላይ ወድቋል፡፡ ይህ ትውልድ ሰማዕቱ ሳሙኤል ከሞተለት ዓላማ በላይ የከፋ አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ ቀላል የማይባል ዋጋም እየተከፈለ ነው፡፡ አሸባሪውና ወራሪው ትሕነግ በቅድመ-ስሪቱ የጥላቻ ፖለቲካ እየተመራ በአማራ ሕዝብ ላይ ጭፍጨፋ፣ ዘረፋና ውድመት በማድረስ ላይ ይገኛል፡፡
‹‹በአማራ ላይ ሒሳብ አወራርዳለሁ›› በሚል ግልጽ የዘር ማጥፋት መመሪያ ለወረራ እንደሕዝብ የዘመተው ይህ ኀይል፣ በዚህ ትውልድ ክንድ ድባቅ ሊመታ ይገባል፡፡ ቅጥረኝነት ያበረታው ጥንተ-ጠላት ትህነግ እንደሕዝብ ሽብርና ወረራ በመፈጸም ላይ ነው፡፡ ስንታገለውም እንደሕዝብ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ወቅት የሳሙኤል አደራን አብዝተን የምንከፍልበት የተጋድሎ ጊዜ ነው። መሰዋእትነቱን የምንቆዝምበት ሳይሆን የበለጠ የምንዘምርበት አስተማሪና አርዓያ ጀግናችን አድርገን ዳግም የምናስታውስበት ወቀት ነው!
የሳሙኤልን ትውልዶች ነን። አደራችን አንበላም። ትግላችን በመስዋእትነት ከግብ አድርሰን ለቀጣዩ ትውልድ የሳሙኤልን አደራ በክብር እናስረክባለን!
Previous articleበአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ላይ የማያዳግም እርምጃ እየተወሰደበት እንደሚገኝ የአፋር ልዩ ኀይል ገለጸ፡፡
Next articleየሕዝብን ማንነት በማጥፋት የህልውና አደጋ የሆነውን ሽብርተኛ ቡድን ለመደምሰስ በሚደረገው ዘመቻ ሁሉም እንዲሳተፍ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር ገለጹ፡፡