
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 10/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር ረዳት ፕሮፌሰር በጠለ ሞላ በወሎ ግንባር ተገኝተው ከሠራዊቱ ጋር እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በግንባር ተገኝተን አንድነታችን በማሳዬት ሠራዊቱን እያበረታታን ነው ብለዋል። የሕዝቡ ድጋፍ አስደሳች መሆኑንም ገልጸዋል።
የሕልውና አደጋ ውስጥ ላይ እንገኛለን ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር በለጠ ወረራ ተፈፅሞብናል፤ በዚህ አይነት ወቅት ሁሉም የሀገር ልጅ ወታደር ሆኖ መቆም አለበት ነው ያሉት። ሁሉም ደጀንነቱን ማሳየት አለበትም ብለዋል።
በሠራዊቱ ያዩት ነገር ሁሉ ለነገ የተሻለ ተስፋ የሚሰጥ አስደሳች መሆኑንም ነው የተናገሩት። የትህነግና የሸኔ ጋብቻ ያልተጠበቀ ጉዳይ አይደለም፤ ሁለቱም ለኢትዮጵያ አንድነት ቀናዒ ያልሆኑ ድርጅቶች ናቸው ነው ያሉት።
አሸባሪው ትህነግ በመሪነት ዘመኑ በሕዝብ ላይ ከፍተኛ በደል ሲፈፅም ኖሯል፤ አሁንም እየፈፀመ ነው፤ ኦነግ ሸኔም በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት በሕዝብ ላይ ከፍተኛ በደል ሲፈፅል ኖሯል ብለዋል።
የሁለቱ አሸባሪ ድርጅቶች ሀገር ለማፍረስ ያቀዱ መሆናቸው ይፋ አድርገዋል ያሉት ሊቀመንበሩ ኢትዮጵያ ሠፊ ሀገርና ሰፊ ሕዝብ ያላት ሀገር ናት፤ ሁለቱ ኃይሎቹ ምንም አይደሉም፣ ቀሪው ኢትዮጵያዊ አንድ ሁኖ እስከ ቆመ ድረስ ተደምሰሰው የኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ይመጣል ነው ያሉት።
የሁለቱ አሸባሪ ድርጅቶች ቅንጅት ያልተጠበቀ አለመሆኑንና ጸረ ሀገርና ፀረ ሕዝብ መሆናቸውን ነው የገለፁት። አሁን ላይ አመች ነገር የተፈጠረ ስለመሰላቸው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ጥምረት ፈጥረዋል ብለዋል። የኢትዮጵያ ኃይል ሰፊ በመሆኑ ፓርቲ ዘለል የሆነ አንድነትን ጠብቆ ሠራዊቱን በመደገፍ ወደድል መጓዝ አለብን፤ ድሉም እንደማይቀር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል ነው ያለው።
በኢትዮጵያ ላይ ወረራ የፈፀሙት ሸኔና ትህነግ ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያ ጠል የሆኑ ሀገራት ጭምር መሆናቸውንም ተናግረዋል። ትህነግ በፈጠረው ወረራ ማኅበራዊ ቀውስ መፈጠሩንም ተናግረዋል። ማኅበራዊ ቀውሱን በዘላቂነት እንዲፈታ ወራሪውን ቡድን ከአካባቢው ጠራርጎ ማስወጣት ነው፤ይህም የማይቀር ነው ብለዋል።
የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመታደግ ረጅ ድርጅቶችን ጨምሮ ሌሎች አካላት ርብርብ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
አቅሙ የፈቀደ ሁሉ መከላከያ ሠራዊትንና ልዩ ኃይልን በመቀላቀል የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት ነው ያሉት። እነርሱም በሚችሉት ሁሉ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ነው የተናገሩት። ከሁሉም የቀደመው ጉዳይ ሀገርና ሕዝብን መታደግ ነውም ብለዋል።
ሁሉም ሀገርን የመታደግ አንድ ግብ አስቀምጦ በጋራ መሥራት አለበት ነው ያሉት። አሁን ላይ ያለው እንቅስቃሴ ጥሩ መሆኑንም ተናግረዋል። ሁሉም ሕልውናውን ለማስጠበቅ ካልተነሳ ሀገር አደጋ ውስጥ ትገባለችም ብለዋል። አብንም በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ