
የሀገር ህልውናን ለማስከበር እና የዜጎች ደኅንነት እንዲጠበቅ ኢትዮጵያውያን በጋራ እንዲቆሙ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ጥሪ አቀረበ፡፡
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 10/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ የሀገር ህልውናን ለማስከበር እና የዜጎች ደኅንነት እንዲጠበቅ ኢትዮጵያውያን በጋራ እንዲቆሙ ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል፡፡
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በሀገሪቱ ላይ እያደረሰ ያለውን ከፍተኛ ጉዳት እና የደቀነው አደጋ ለመመከት ከሕዝብ እና ከመንግሥት ጎን እንደሚቆም የፓርቲዉ ዋና ጸሐፊ አቶ አበበ አካሉ ተናግረዋል።
ፓርቲዉ በየአካባቢዉ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ ያስችል ዘንድ 250 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታዉቋል።
ፓርቲዉ በሠጠው መግለጫ መንግሥት በአሸባሪዉ የሕወሓት ቡድን እና በኦነግ ሸኔ ላይ የማያዳግም እርምጃ መዉሰድ አለበት ብሏል።
መንግሥት «ብሔራዊ የሀገር ሉዓላዊነት እና የሕዝብ ደኅንነት ማሰከበር ዘመቻ ግብረ ኃይል» እንዲያቋቁም እና ወደ ሥራ እንዲገባም ፓርቲው ጠይቋል፡፡
ወደ ግንባር ያቀኑ አርሶ አደሮችን ማሳ ቅድሚያ በመስጠት የአካባቢው ነዋሪዎች የሚያስፈልገዉን ሁሉ ማድረግ እንደሚያስፈልግም በመግለጫዉ አንስቷል።
ለሠራዊቱ ግንባር ድረስ በመገኘት ፓርቲዉ ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታዉቋል።
ፓርቲዉ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ግንባር ላይ ያለዉን ኀይል መደገፍ እንደሚገባቸዉም አሳስቧል።
የፓርቲዉ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ግርማ ሰይፉ ፓርቲዉ የዉጭ ዲፕሎማሲ ላይ እየሠራ መሆኑን አንስተዉ ሁሉም በሀገር ዉስጥም በዉጭም የሚኖር ኢትዮጵያዊ የዲፕሎማሲ ሂደቱ ላይ ተሳታፊ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል። ኢዜማ ምንጊዜም ለሰላማዊ ትግል እንደሚሠራ አስታዉቀዋል። ማኅበረሰቡም ከሐሰተኛ መረጃዎች ራሱን በመጠበቅ ለኢትዮጵያ ህልውና የበኩሉን መወጣት አለበት ሲል ፓርቲዉ መልእክቱን አስተላልፏል።
ዘጋቢ፡-ኤልሳ ጉዑሽ-ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ