“በአሸሽ ስለሚያሰክሩን የምናደርገውን አናውቅም” የአሸባሪው ትህነግ ምርኮኛ

581

“በአሸሽ ስለሚያሰክሩን የምናደርገውን አናውቅም” የአሸባሪው ትህነግ ምርኮኛ

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በምድር ላይ ያሉ ጭካኔዎችንና ግፎችን ሁሉ እያደረገ ነው፣ በግፍ ገድሏል፣ አስሯል፣ አሰቃይቷል። ትህነግ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን ያልሰራው ግፍ ምን አለ? ጭካኔያቸውን እያዬ ፈጣሪ እንዴት ዝም አላቸው? ለምን አልተቆጣም? ለምንስ አላጠፋቸውም? የትዕግስቱ ልክ ምን ይደንቅ? ኢትዮጵያውያንስ ስንቱን ችለውት ኖሩ።

ግርማይ በሪሁን ይባላል። የ13 ዓመት ልጅ ነው። የተወለደው በአላማጣ አጠገብ በምትገኝ የገጠር መንደር ውስጥ ነው። ግርማይ በእናትና በአባት እጅ ተቀማጥሎ የማደግ እድል አልነበረውም። እናቱ በልጅነት እድሜው አልፈዋል። አባቱ የትዳር አጋር ትሆናቸው ዘንድ ሌላ ሚስት አገቡ። በጠዋት እድል የዞረችበት የሚመስለው ግርማይ ከአዲሰቷ ሴት ጋር አልተስማሙም። ቤት ጥሎ ወጣ። በአላማጣ ከተማም የጎዳና ልጅ ሆነ። የተገኘውን እየሠራ ሲገኝ እየበላ ሲታጣ ደግሞ ፆሙን እያደረ ሕይወትን ይገፋት ጀመር።

ትህነግ በዚያ አካባቢ ያልፈፀመው በደል አልነበረም። ከበደል ሁሉ የከፋውን በደል ደግሞ በመከላከያ ሠራዊት ላይ ፈፀመ። የኢትዮጵያ መንግሥትም ሕግ ለማስከበር ተገደደ። ወሰደም። ብዙዎችንም ደመሰሰ፣ ብዙዎችን አሰረ፣ ጥቂቶች ዋሻ ውስጥ ገቡ። በዚህ መካከል የኢትዮጵያ መንግሥት ሲወስደው የነበረውን የሕግ ማስከበር ርምጃ ለትግራይ ሕዝብ የጥሞና ጊዜ ይሆን ዘንድ ሲል ተኩስ አቆመ። የተረፉ የትህነግ ሰዎችም ከቀደመ ባሕሪያቸው ሳይድኑ ለሌላ ጦርነት ተዘጋጁ። ጦርም ለኮሱ።

የትግራይ ታጣቂዎች አካባቢዎችን እየወረሩ አላማጣ ከተማ ገቡ። ሕፃኑ ግርማይና ሌሎች ጓደኞቹ በአላማጣ ከተማ ተገኙ። ታጣቂዎችም በአላማጣ ከተማ ያሉ ሕፃናትን ይሰበስቡ ጀመር። ከግርማይ ጋር ሕፃናትን ሰብስበው የምትጭኑት ነገር አለ ብለው ወሰዷቸው።
“ኑ የምትጭኑት ነገር አለ ብለው ሰበሰቡን፣ ወስደው ካምፕ ውስጥ አስገቡን፣ በየቀኑ አንዳንድ ዳቦ ይሰጡን ነበር፣ በመካከል ግን ወደ ጦርነት አስገቡን፣ ወደ ድልብም ወሰዱን። በዚያም ቆዬን 25ቱን መልሰው ወደ ሃራ ወሰዱ በሃራ በነበረው ውጊያ 24ቱ ሞቱ እኔ ተረፍኩ። ከዛ መትረፌን ሳውቅ ወደመርሳ ሄድኩ። ሐይቅ ስደርስም ተያዝኩ” ነው ያለን።

ግርማይ ያሳዝናል፣ ተጫውቶ ያልጠገበ ነው። ለትምህርት እንጂ ለጦርነት ዝግጁ አይደለም። ብቁም አይደለም። ልጅ ነውና። “አሽሽ ይሰጡናል። ሳቡት እንባላለን። ስንስበው የምናደርገውን አናውቅም። ዝም ብለን እንጓዛለን። ጓደኞቻችን እየሞቱ እያየን ዝም ብለን እንሄዳለን። ክላሽ ተሰጥቶኝ ነበር። ዒላማ ግን አላስተማሩንም። ብቻ ሺሻውን ስትጠቀም የማታደርገው ነገር የለም። ሺሻ አልስብም ያለ ይገደላል። እነርሱ እኛን ወደፊት ገፍተው ከኋላ ይቀራሉ። ፊት ፊት የሚሄደው ይሞታል” ነው ያለን።

አሸባሪው ቡድን ውሸት ይነግራቸዋል። የሕልም እንጀራ ያበላቸዋል። ግፉ እናሸንፋለን፣ የሚያሸንፈን ኃይል የለም እያሉም እንደሚያታልሏቸው ነው የነገረን። ብዙ ሰው ሲረግፍ በትንሽ እድሜው አይቷል። “ለመከላከያ እጅ አትስጡ፣ ትሞታላችሁ ይሉናል። እኔ ግን ዝም ብዬ መጣሁ እንኳን ሊገድሉኝ ተንከባከቡኝ። እኔ ደህና ነኝ 24 ጓደኞቼን እያየሁ አጥቻለሁ። ሌሎቹ 25ቱ የት እንዳሉ አላውቅም። ሞተውም ይሁናል” ግርማይ በሀዘን ይናገራል።

ከዚህ ከመጣሁ ተመችቶኛል። ሌሎች ሕፃናትም እጃቸውን ይስጡና ከሞት ይትረፉ፣ ስናሸንፍ የመንግሥት ሥራ እንሰጣችኋላን፤ ብር ይሰጣችኋል እያሉ ነው የሚያታልሉት ነው ያለው። “አባቴ የት እንዳለሁ አያውቅም። አላማጣ ያለሁ ነው የሚመስለው፣ የሌሎች የሞቱት ሕፃናት ወላጆችም የት እንዳሉ አያውቁም። አልሄድም ማለት አይቻልም። እንዴትስ ትላለህ? ግድዴታ ነው ይገደላል እንጂ። አሁን ከተማ ያለን ይመስላቸዋል” ብሎናል።

ህፃናቱ ለመከላከያ እጅ መስጠት አለባቸው። በእርግጥ አሽሹ ሲሳብ የምናደርገውን አናውቅም ብሏል። ግርማይ ከሞት ስለ ተረፈበት ነገር ሲናገር “ድልብ ላይ እያለሁ አሽሽ ወስጄ ነበር። ወደ ሃራ ሲወስዱን ከዛ ራሴን አወኩ። 24ቱ ጓደኞቹ ሲሞቱ አወኩ። ጥይቱም ሲያጨናንቀኝ ወደ ጉድጓድ ወደኩ። ከዛም ተረፍኩ” ነው ያለው።

በደቡብ እዝ የ21ኛ ክፍለ ጦር አባል ሌትናል ኮሎኔል ከበደ ማዴቦ ሕፃናት ሳይወዱ በግድ እየታፈሱ ወደ ጦርነት እየገቡ ነው ብለዋል። ማኅበረሰቡ እንደዚህ አይነት ሰዎችን ሲያይ ለፀጥታ አካል መስጠት አለበት ነው ያሉት። ሕፃናትን መማገድ በጦርነት ሕግ የተከለከለ ስለሆነ ማኅበረሰቡ ሕፃናትን ሲያገኝ ለፀጥታው አካል እየሠጠ አሸባሪ ቡድኑ እንዲጠየቅ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።

ትህነግ የሠራዊቱን እንቅስቃሴ፣ ዲፖዎችንና ሌሎችን የሚሰልሉለት ተላላኪዎችን ስለበተነ ሁሉም በጥርጣሬ እና በንቃት መጠበቅ አለበት ብለዋል።

ማኅበረሰቡ ከሠራዊቱ ጋር በጋራ ከሠራ አሸባሪውን በአጭር ጊዜ ውስጥ የማናሸንፍበት ምንም አይነት ምክንያት የለም ነው ያሉት። በወሬና በውሸት የተሸፋፈነ ቡድን ስለሆነ እርሱን ማሸነፍ ቀላል ነው ብለዋል። ግዳጁን በድል እንወጠዋለን፣ ገብተን ድምጥማጡን እናጠፈዋለንም ብለዋል።

በጦር ሕግ ሕፃናት፣ አዛውንትና ሌሎች ከለላ ይገባቸዋል። ሕፃናትን ማሰለፍ ወንጀል ነውም ብለዋል። ሠራዊቱ በምርኩ የሚያዙ ሰዎችን በእንክብካቤ ይይዛል፣ ሕዝባዊ ሠራዊት ነው፣ የጁንታው አካላት ለመከላከያ ሠራዊት እጃቸውን መሥጠት አለባቸው ነው ያሉት። በደሴ ከተማ ሽብር ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ የተገኙ ተላላኪዎችም በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተነግሯል።

በታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleThe government’s call to the people is a moment that leads to the elimination of the terrorist TPLF for good and all – Teshale Nigussie, Head of the Tigray Democratic Party (TDP)
Next article“የውሸት ፀሐይ ሲጠልቅ የሤረኞች ወጥመድ ይበጠሳል!!” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)