
አስማረ ዳኜ: የዚህ ዘመን ወጣት ምልክት
አስማረ ዳኜ ከደርግ ሥርዓት ጀምሮ በእምቢ ባይነት የኖረ፣ ለወገን ፍቅር፣ ክብር እና ነፃነት የጫካን ሕይወት የለመደ፣ የዱር የገደሉን መከራ የወደደ፣ የአማራን ያለስሙና ግብሩ መበደል በሚገባ የሚያውቅ ጀግና አማራ ነው።
ትውልዱ በታላቁ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት፣ አሳግርት እና በረኸት ሲሆን የከሰምን እና በረኸትን ቆላ እስከ አፋር ድረስ <<ዱሩ ቤቴ!>> ብሎ የነፃነት ትግሉን እስከ ፍፃሜው ተጋድሎበታል፣ ተዋድቆበታል።
አስማረ በ1983 ዓ.ም በአርባጉጉ ይኖሩ የነበሩ አማሮች ላይ ጥላቻ እና ትንሽነት ያሰከራቸው፣ ያጣመራቸው፣ በክፋት ዳቁነው፣ በከፋፋይነት የቀሰሱት የአቢሲንያ የዘመን ስብራቶች ወያኔ እና ኦነግ በትሕነግ ደቀመዝሙርነት፣ በኦነግ ተላላኪነት የተጫነበትን የበደል ቁና፣ የመከራ ገመድ ይከታተል፣ ያውቅም ነበር።
እየደረሰ የነበረው ዘር-ተኮር የአማራን ጭፍጨፋ ማብቂያ-ማክተሚያ ቢጠፋው፣ አስማረ ወገኖቹን ለመታደግ ከሸዋ ጊናገር 15 ወዳጅ ገበሬዎችን በማስተባበር አርባጉጉ መሸገ።
አስማረ ደፋር፣ ያሰበውን የሚከውን፣ የወገን ባርነት፣ ጭቆና ያንገሸግሸው ነበር። አሸባሪው ትሕነግ ለአማራ አጥፊው፣ አማራን እንደ ሕዝብ ጠላት ያደረገ መሆኑን ቀድሞ የተረዳ፣ ያወቀ፣ ፀረ-ትሕነግ ትግልም ማልዶ የጀመረ፣ ነጭ-ቃታ በልጅጉን ወልውሎ <<እምቢ ለባርነት>> ያለ፣ የራሱን ዓድዋ፣ የትውልዱን ማይጨው በፀረ-ትሕነግ ትግል የጀመረ፣ የ80ዎቹ ወጣቱ ነብይም ነበር።
አስማረ ከሸዋ አርባጉጉ በእግሩ ተወርውሮ በአካባቢው በሚገኙ የኦነግና የሕውሐት ሥርዓት ጀሌ ወታደሮች ላይ በድንገተኛ አደጋ ጣይነት እሳት አዘነበ፣ የክንዱን መራራነት ጋታቸው።
አስማረ ከአባቱ ራስ መኮንን፣ ከጀግናው ኃይለማርያም ማሞ እና ከታላላቆቹ ከእነ ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ አርዓያነትን በመማር፣ ተግባራዊ ንቃቱ እጅግ የደረጀ በመሆኑ እንደ ሲዖል የሚያስፈራ፣ እንደገሃነም የሚፋጅ ጥቃት ከፍቶ የብዙ አማሮችን ህይወት ታድጓል፣ ተስፋም መከታም ሆኗል።
አስማረ ከአርባጉጉ ሲመለስ ጀግንነቱን ከቀድሞ ጀምሮ የሚያውቁት የወቅቱ የትሕነግ ሥርዓት ስለተሸበረ፣ የአስማረንም ቁጣና ክንድ ስለቀመሰ፣ ምናልባት ምናልባት ግስላው ቁጣውን ቢያበርድ ብለው በማሰብ ከማዕከል በቀጭን ትእዛዝ የጊናገር ወረዳ ወይም የአሁኗ አሳግርት አስተዳዳሪ እንዲሆን አደረጉት።
ወይ ፍንክች!
አስማረ ሹመቱን ለመላ፣ ለነፃነት ትግሉ ማስፈፀሚያ ለጊዜው ተቀበለ።
በተሾመ በጥቂት ወራት ውስጥ ትሕነግ የሸዋን አርሶ አደር ትጥቅ አስፈትቶ የቆለፈበትን በወረዳው የሚገኘውን የመሣሪያ መጋዘን በመስበር መሳሪያውን ለሸዋ የአማራ ገበሬዎች እና በከሰም ወንዝ አቅራቢያ ለሚገኙት የአፋር አርብቶ አደሮች በማከፋፈል የአካባቢውን ገበሬ አስከትሎ ዳግም ሸዋና አካባቢውን ከአገዛዙ ነፃ ለማውጣት ተመልሶ ወዳደገበት ጫካ፣ ወደ ተለመደው ፀረ-ትህነግ ትንቅንቅ ገብቶ በመመሸግ ሕዝቡን ነጻ ለማውጣት መሸፈቱን ለሾመው አካል መልእክት ላከ።
ወጥመድ ላጠመደው፣ ወጥመዱን ሰባብሮ፣ ሌላ ወጥመድ አጥምዶ፣
ጎራው ናልኝ…..!
ዱሩ ቤቴ፣ ጫካው ጎረቤቴ፣
ደህና ክረሙልኝ፣ እናትና አባቴ! ብሎ በረኸኛ ሆነ።
በሕዝብ ውግንናው እና በመረረ የትሕነግ ጥላቻው የተበሳጩት ሹማምንትም ሁለት ብርጌድ ጦር ወደጊናገር በመላክ በአስማረ ጦር ላይ ቀጥተኛ ጦርነት ቢከፍቱም የአስማረ ጦር ሊበገር አልቻለም።
ይልቁንስ 20 የማይሞላው የአስማረ ጦር ጠላትን በሞት፣ መሬት ውስጥ በመክተትና ቆርጦ በመምታት በአንድ ቀን ውጊያ ብቻ በርካታ የሕወሓት ዙፋን ጠባቂ ወታደሮችን ረፍርፎ አምስት ወታደሮችን ከነሙሉ ትጥቃቸው ማረኩ።
ቀጥሎ የአራት ኪሎው ሕወሓት በመደናገጡ በሄሊኮፕተር የታገዘ ዘመቻ ጥቃት በአስማረ ጦር ላይ ቢዘምትም አልተሳካም።
ዘመቻው በአስማረ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ የገዢው ሹማምንት አስማረን ለመግደል ሰላዮችን ወደጊናገር ይልካሉ።
ሆኖም አስማረ ሰላዮቹንና አብረው የመጡ ወታደሮች ላይ ተኩስ ከፍቶ ሁለቱን ገድሎ አምስቱን ማረካቸው። የተማረኩትንም ጊናገር ገበያ ላይ አስሯቸው ስለነበር ወታደሮቹን ሕዝቡ እየተመለከተ የአስማረ ምርኮኞች እያለ ይሳለቅባቸው ነበር።
ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ በሎጅስቲክ እጥረት እንደሚቸገር ቀድሞ የተነተነው እና የተረዳው አስማረ ጦሩን አስከትሎ ወደሚወዳቸውና ወደሚያምናቸው አፋሮች ዘንድ ተጓዘ።
ቀደም ሲልም በአፋር ሕዝብ የፀረ-ትሕነግ ትግል ውስጥ አስማረ ከአፋሮች ጋር ልዩ ትስስርና ፍቅር ነበረው። አሰግድ መኮንን የተባለ የታሪክ ጸሐፊ ከዚህ በፊት የአስማረን ገድል ሲከትብ የአስማረን ታሪክ ከአፋር ትግል ለይቶ ለብቻው ለይቶ መፃፍ ጥቁር ድመትን በጨለማ እንደመፈለግ የማይታሰብ ነውና አፋር የአስማረ ውለታ አስማረም የአፋር ውለታ አለባቸው ብለው እንደነገሩት ጸሐፊው አትቷል።
ሕወሓትን እንቅልፍ ነስቷታልና፣ አስማረ ዳኜ አርጎባ አካባቢ በመሸገ በ3ኛው ቀን የሕወሐት-ኢህአዴግ ሠራዊት መረጃ አግኝተው ኖሮ በከባድ መሣሪያ የታጀበ ጦርነት በአካባቢው ላይ ይከፍታሉ። ሆኖም አስማረ ከሸዋ አብረውት በመጡት ገበሬዎች እና የአፋር ወዳጆቹ ድጋፍ በስፍራው የከበበውን ጦር ቀጥቶ ያፈርሰዋል።
ቀጥሎም ከሸዋ አብረውት ከዘመቱ ወታደሮቹ መካከል ሁለቱን አስከትሎ ስንቅ ፍለጋ መተሐራ ወደሚገኘው የትግል አጋሩ ዘንድ ይሄዳል።
ሆኖም የመተሐራው ተወካይ በሕወሐት መሰሪ ተግባር በገንዘብ ተደልሎ ሊያስገድለው መሆኑ በአፋሮች የመረጃ መረብ <<ዳጉ>> ውስጥ ይገባል። በዚህም የተነሳ አስማረ መንገዱን በመቀየር በከሰም በኩል በማድረግ ሽሬ የምትባል የገጠር መንደር ቆይታ አድርጎ ወደስፍራው በመሄድ ከመተሐራው ወዳጁ በተቃራኒ አቅጣጫ መሽጐ ሁኔታዎችን መከታተል ይጀምራል።
በዚህም የመተሀራው ተወካይ ለማስመሰል የወታደር ቀለብ በመኪና ጭኖ ከፊት እየሄደ በሌላ በኩል በርካታ የትሕነግ ወታደሮች የጫነ መኪና ሲመጣ ተመልክቶ ቀድሞ ተኩስ ከፍቶ አንድ በአንድ ሲለቅማቸው የተኩስ ድምፅ የሰማው አንድ ብርጌድ የትሕነግ ታማኝ ሠራዊት በስፍራው በመድረስ በአስማረ እና በሁለቱ ጓደኞቹ ላይ ተኩስ ይከፍታሉ። አስማረም ነጎድጓዳዊ ውጊያ በመክፈት ሞራላዊና ወታደራዊ ውድመት እንዳከናነባቸው በታሪክ በወርቅ ብዕር ቀለም ተመዝግቧል።
ከዚህ ፀረ-ትሕነግ ትንቅንቅ ማግስት ጀምሮ ወጣቱ፣ ኮስታራው፣ የአማራ የአይበገሬነት ምልክት አስማረ የገባበት አልታወቀም።
ሆኖም ይህ ጀግና፣ የአማራ ወጣቶች የትግል ቀንዲል፣ የፍትሕና የነፃነት አብሪ ኮከብ መስከረም 11 ቀን 2012 ዓ.ም በደራሲ አሰግድ መኮንን እና የታሪኩ አስታዋሽ የሸዋ ወጣቶች አስተባባሪነት የፊታውራሪነት ማዕረግ በጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ጽሕፈት ቤት በኩል ተሰጥቶታል።
የአማራ ወጣት ሆይ፣ አስማረ ባንተ ዘመን ትህነግን ወግቷል። አንተም ተነስተህ ለነፃነትህ ዝመት፣ የአባቶችህን ታሪክ ጠብቅ!