“አንድ ሆነን አሸባሪውን ትህነግ መቅበር አለብን፤ ያን ጊዜ ነው የአባቶቻችን ልጆች መሆናችንን የምናስመሰክረው” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

414
“አንድ ሆነን አሸባሪውን ትህነግ መቅበር አለብን፤ ያን ጊዜ ነው የአባቶቻችን ልጆች መሆናችንን የምናስመሰክረው” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እንዳሉት እየተካሄደ ያለው የህልውና ዘመቻ ከአሸባሪው ትህነግ ጋር ብቻ ሳይሆን አፍራሽ ከሆኑ የውጭ ሀገራት እና ከውስጥ ሀገር ተላላኪዎች ጋር የሚደረግ ትግል ነው።
ዋነኛው አሸባሪ ቡድን ትህነግን ጨምሮ አሸባሪው የኦነግ ሸኔ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ነፃ አውጪ ነኝ የሚሉ ኀይሎች ግድያ፣ ዘረፋና ውጊያ እያካሄዱ ነው ብለዋል።
የሽብር ቡድኖቹ በአማራ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል እና ኦሮሚያ ክልሎችም ውጊያ እየፈጸሙ ነው ብለዋል።
አሸባሪው ትህነግ ቆርጦ የተነሳው ኢትዮጵያን ለመበታተን ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ይህን ቡድን ጨርሶ በማጥፋት የሀገሪቱን ሰላም ማስጠበቅ እንደሚቻል ጠቁመዋል። ይህ የጥፋት መፈልፈያ ቡድን ስሩ ከደረቀ ጀሌዎቹ የትም እንደማይደርሱ ነው አቶ ግዛቸው የተናገሩት።
ዋና ዳይሬክተሩ በሰጡት ወቅታዊ መረጃ “ረፍት የምናገኘው አሸባሪውን ቡድን ቦታ በማስለቀቅ ሳይሆን ከምድረ-ገጽ በማጥፋት ነው” ብለዋል። በመሆኑም በተለይ ትናንት ከሰዓት በኋላ በአማራ ክልል ባሉ ሁሉም አውደ ውጊያዎች በተቀናጀው የወገን አሰላለፍ ጠላት ከፍተኛ ሽንፈት ደርሶበታል፤ እስከ ዛሬ ከተካሄደው አውደ ውጊያ የላቀ ድል የተገኘበት መሆኑን ገልጸዋል።
ተቆራርጠው ወደ አማራ ክልል የገቡ የሽብር ቡድኑ አባላት ሳይወጡ እዚሁ መቀበር አለባቸው ብለዋል። ትናንት በተገኘው ድል የተደናገጠው የጠላት ቡድን መውጫ ቀዳዳ እየፈለገ እንደሆነ ነው አቶ ግዛቸው የተናገሩት። በመሆኑም ሕዝቡ የጠላትን መውጫ ቀዳዳ ሁሉ መዝጋት እንዳለበት ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።
የሽብር ቡድኑ በወረራቸው አካባቢዎች ሁሉ ሰላማዊ ሰዎችን እየገደለ፣ ዜጎችን እያፈናቀለ፣ የመንግሥትንም ሆነ የነዋሪዎችን ሀብትና ንብረት ዘርፎ ለመውጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አቶ ግዛቸው ገልጸዋል።
አሸባሪ ቡድኑ ባሕሪው ሕዝብን መጨፍጨፍ ነው ያሉት አቶ ግዛቸው ሕዝብን በማታለል ሊቆምር ስለሚፈልግ ኅብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።
አቶ ግዛቸው ሽብርተኛው ቡድን “ኅብረተሰቡ አጨብጭቦ ነው የተቀበለኝ” በማለት የሐሰት ወሬ እየነዛ ነው ብለዋል። በራሱ አጋፋሪዎች በመታጀብ እያስጨበጨበ ድራማ መሥራት እንደሚፈልግ ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያስረዱት። መላው የአማራ ሕዝብ እንዲህ አይነት ሥነልቦና እንደሌለው መታወቅ አለበት ብለዋል። ይህም ደግሞ የሀራ፣ የወልድያና የደብረ ታቦር ወጣቶች ያሳዩት ትንቅንቅ ምስክር እንደሆነ በአብነት አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት ጠላት በመበታተን ወደ ትናንሽ ቡድን እየተከፋፈለ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ግዛቸው ይህ ጠላት ተደራጅቶ መልሶ እንዳይዋጋ ባለበት ቦታ ሁሉ ሊቀበር ይገባል ነው ያሉት።
“መራራና ረዘም ያለ ትግል ስለሚጠብቀን ከአሁኑ አቅዶ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፤ ሊያጠፋን የመጣን ቡድን መያዝ ብቻ ሳይሆን እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል። በተራዘመው ትግል የአማራን መሬት ማስለቀቅ ብቻ ሳይሆን ቡድኑን ማጥፋት ያስፈልጋል” ብለዋል። ይህ ኀይል ተመልሶ የሚሰባሰብበት እድል ማግኘት እንደሌለበት ገልጸዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት በየቦታው የተበጣጠሰውን ጠላት ከሚያድን በየአካባቢው የሚገኘው ኅብረተሰብ እዚያው ሊቀብረው ይገባል ብለዋል። “ይህን ካደረግን ብቻ ነው ነፃነታችንን የምናገኘው” ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት ባሕር ዳርን ጨምሮ ወደ ተለያዩ ከተሞች ሊገቡ ሲሞክሩ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰርጎ ገቦች አሉ። ዓላማቸው ሀብት መዝረፍ፣ በደረሱበት ቦታ ሁሉ ተቆጣጠርን ማለት መፈለግ መሆኑን አስገንዝበዋል። “እኛው ጋር ኖረው ለአሸባሪው የሚላላከውን ሥርዓት ማስያዝ አለብን። በተጨባጭ ማስረጃ ንጹሕ የሆኑትን ለይተን ተላላኪዎች ላይ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፤ ከአሸባሪ ጋር ድርድር ማድረግ አያስፈልግም፤ ዓላማችን ትልቅ ስለሆነ በትናንሽ ድሎች መኩራት፣ በትናንሽ ጉድለቶችም መረበሽ አያስፈልግም” ብለዋል።
“አንድ ሆነን አሸባሪውን ትህነግ መቅበር አለብን፤ ያን ጊዜ ነው የአባቶቻችን ልጆች መሆናችንን የምናስመሰክረው” ነው ያሉት አቶ ግዛቸው፡፡
ኅብረተሰቡ በተለይ ለሐሰት ፕሮፖጋንዳ ተጋላጭ መሆን እንደሌለበት አቶ ግዛቸው አሳስበዋል። ኅብረተሰቡ ተዓማኒ ከሆኑ የመረጃ ምንጮች ብቻ መረጃ መውሰድ እንደሚገባውም ተናግረዋል።
የሰቆጣ የኀይል አሰላለፍ፣ የወልድያ፣ የመርሳ፣ የሀራ፣ የደብረ ታቦር፣ የሰሜን ጎንደርና ሌሎችም አካባቢዎች ትንቅንቅ በሁሉም አካባቢ ሊሰፋ እንደሚገባ ገልጸዋል። የሚደረገው የሕዝብ ትግል ሁሉ በተደራጀ መልኩ መሆን እንዳለበት ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል። የሕዝብ አደረጃጀቱ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ለገንዘብ የሚሞት ይቅር አይወለድ ፣ አይበጅም ለወገን አይሆንም ለዘመድ”
Next articleአስማረ ዳኜ: የዚህ ዘመን ወጣት ምልክት