“ለገንዘብ የሚሞት ይቅር አይወለድ ፣ አይበጅም ለወገን አይሆንም ለዘመድ”

250
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 08/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በህልውናዋ ላይ ጥቃት ሲቃጣባት ዛሬ የመጀመሪያዋ አይደለም፡፡ አሸናፊነቷ፣ የታሪክ ገናናነቷ እና ከፍታዋን በጥላቻ የሚመለከቱት የውጭ ኀይሎች ከውስጥ ባንዳ ጋር በመመሳጠር ኢትዮጵያን ለመበተን ቢጥሩም ጀግኖች ሀገር ወዳድ አርበኞች እንደ ረመጥ ተፋጅተው እንደ አንበሳ አግስተው ጠላትን ዶግ አመድ አድርገው ሀገራቸውን በክብር አቆይተዋል፡፡
በተለይ ፋሽስት ጣሊያን ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም የፈጸመው ወረራ ለኢትዮጵያውያን እጅገ ፈታኝ ጊዜ ቢሆንም ጀግኖች አርበኞች የጠላትን ኀይል በየገባበት መውጫ መግቢያ በማሳጣት ለሀገራቸው ክብር በፅናት በመታገል አያሌ ጀብዱዎችንም ፈጽመዋል። በጽናት ቆመውም የፋሽስት ኀይልን ድል ነስተው የኢትዮጵያን ነጻነት እና ልእልና አስቀጥለዋል፡፡
ተድላ ዘዮሃንስ ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ከወልወል እስከ ጎንደር በሚለው መጽሐፋቸው በአምስት ዓመታቱ የነበረውን ሁኔታ “በሥነ ቃል እንዲህ ተገልጾ ነበር”ብላው ከትበውልናል፡፡
ፋሽት ጣሊያን ኢትዮጵን መውረሩ ሲረጋገጥ አርበኞች ከየአቅጣጫው ተንቀሳቀሱ፡፡ ይሄን ከኢትዮጵያ ጋር ሲነጻጸር እጅግ የዘመነ ትጥቅ ያለውን ወራሪ ለመፋለም ፈታኝ ቢሆንም ለነጻነት መሞት ክብር መሆኑን
“አልበላንም አልጠጣንም አልጠናም ክንዳችን፣
እንዲሁ እንሞታለን ለነጻነታችን”
በማለት እየሸለሉ ለነጻነት ህይወታቸውን መስጠትን ቀጠሉ፡፡
ይሁን እንጅ አንዳንድ ባንዳ ሃሰተኛ መረጃዎችን እየነዛ የብዙ ሀገር ወዳድ ጀግኖችን ሥነ ልቦና ለመስለብ ሞክሯል፡፡ አርበኞችም ለሀገር ክብር ለመፋለም የሚያመነቱ ሰዎችን በተመለከቱ ጊዜ
“እንሂድ አርበኞች ወርደን እናምሰው፣
ምን ይመልሰናል ማተብ የሌለው ሰው”
በማለት ህልውና ሲባል በእምነትም የመጣ መሆኑን በሽለላ መልክ ነግረዋቸዋል፡፡
ባንዳ ዛሬም ብቻ ሳይሆን ትናንትም ነበር፡፡ ለሆዱ አድሮ ከጠላት ጎን የተሰለፈው ቀላል አልነበረም፡፡ ለጀግኖች አርበኞችም ይሄ ባንዳ የድል ቀናቸው በአጭሩ እንዳይሆን ፈተና ቢሆንባቸውም ድሉ ግን የእነርሱ ነበር፡፡
ጀግኖች አርበኞችም በጣሊያን ገንዘብ እየተታለሉ ሃገራቸውን የከዱ ባንዳዎችን አስመልከቶ
“ለገንዘብ የሚሞት ይቅር አይወለድ፣
አይበጅም ለወገን አይሆንም ለዘመድ” በማለት ይሸልሉ ነበር፡፡
ቀስ በቀስም የወራሪው ፋሽስት ጣሊያን ጭካኔ ተገለጠ፡፡ ህጻናትን እና ሴቶችን ሳይቀር በአደባባይ መግደል ማቃጠልን ተያያዘው፡፡ ይህም የበለጠ ጀግኖች አርበኞችን አጠነከራቸው እንጂ ወደኃላ እንዲሉ አላደረጋቸውም፤ የአርበኞች ብርታትና ጀግንነትም ብዙዎች ከጎናቸው እንዲሰለፉ አደረገ። እንዲህ በማለትም ሕዝቡን በሽለላ ይቀሰቅሱ ነበር
“እንግዲህ ባገሬ ነጭ ጤፍ አይብቀል
አረም ነው እያሉ ከስሩ ነው መንቀል”
ፍሽስት ኢትዮጵያን ከወረረ በኋላ ነገሮች ሁሉ እንዳሰበው ቀላል አልሆኑለትም፤ ጀግኖች አርበኞች ፋታ ነሱት፤ ረመጥ ሆነው ለበለቡት፡፡ አንገት እየቀላ በእሳት እያቃጠለ ሕዝቡን በአደባባይ ሰብስቦ ጀግኖችን ቢረሽን የሚፈራ ቀርቶ የሚደነግጥለት ጠፋ፡፡ ይሄንን የወራሪውን መደንገጥ የተረዱ ጀግኖችም እንዲህ በማለት ሸለሉ።
“ተጉዞ ተጉዞ ነጭ እንደ ደመና፣
መመለሻው ጠፋው ያገሩ ጎዳና”
ከአምስት ዓመታት ተጋድሎ በኋላም አይቀሬው ድል መጣ፤ ይሁን እንጅ ብዙ ዋጋ ተከፍሏል፡፡ አጥንት ተከስክሷል፣ ደም ፈሷል፡፡ ለኢትዮጵያ ሲባል ነፍሳቸውን ለሰጡ ጀግኖችም
“የተዘራው ደምህ መቸ ከንቱ ቀረ፣
ነጻነት አፍርቶ ስምህ ተከበረ“
በማለት ዘመን አይሽሬ ሙገሳን አስቀምጠውላቸዋል፡፡
ታሪክ ዛሬም ራሱን ይደግማል፡፡ኢትዮጵያን ክብሯን ለመንካት የመጣን ባንዳ አይቀጡ ቅጣት ለመቅጣት እልፎች ተሰልፈዋል፤ ባንዳውም ምኞቱ አይሳካም፡፡ በባንዳ ጎኗን የተወጋችው ኢትዮጵያም በጀግኖች ልጆቿ ከህመሟ ትፈወሳለች። እንደ ትናንቱ ዛሬም ነገም በከፍታዋ ትቀጥላለች፡፡ ክብር ለጀግኖች ይሁን!
በፈረደ ሽታ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በወሎ ግንባር የሚገኘውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ አባላት በግንባር ተገኝተው አበረታቱ።
Next article“አንድ ሆነን አሸባሪውን ትህነግ መቅበር አለብን፤ ያን ጊዜ ነው የአባቶቻችን ልጆች መሆናችንን የምናስመሰክረው” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ