
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በወሎ ግንባር የሚገኘውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ አባላት በግንባር ተገኝተው አበረታቱ።
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአምባሰል ወረዳ ውጫሌ ከተማ ተገኝተው ሠራዊቱን አበረታተዋል።
አቶ ደመቀ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሀገሪቷ የገጠሟትን ፈተናዎች ፊት ለፊት በመፋለም ከፍተኛ መስዋእትነትን እየከፈለ ያለ ሕዝባዊ ሠራዊት መሆኑን ገልጸዋል።
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ሀገርን ለመበተን ባለው ፍላጎት ሠራዊቱን ከጀርባ ለመውጋት ቢሞክርም በጀግናው የመከላከያ ሠራዊት አባላትና መላው ኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ እየደረሰበት እንደሆነ አስታውቀዋል።
በአማራና አፋር ክልሎች በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች አሸባሪው ቡድን ሕዝቡን ከመኖሪያ ቀየው በማፈናቀል፣ በመረሸንና ሀብትና ንብረቱ እንዲወድም በማድረግ፣
ሕጻናትና ሴቶችን በመድፈር፣ የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻል የተዘረጉ መሰረተ ልማቶችን በማውደምና ሌሎች ያደገበትን ሴራዎች ሁሉ ሕዝብ ላይ በመፈጸም ኢትዮጵያ ጠልነቱን በተግባር እያሳየ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያ ኩራትና የክብር ማሳያ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ደመቀ መከላከያ ሠራዊቱ፣ ሌሎች የጸጥታ ኀይሎችና በመላ ኢትዮጵያዊያን ትግል ይህ አሸባሪ ቡድን ተደምስሶ ኢትዮጵያ አሸናፊ የምትሆንበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ተናግረዋል።
በቀጣይም ሕዝቡ የውስጥና የውጭ ኀይሎች ሊፈጽሙት የሚችሉትን ማንኛውንም ጥቃት የሚመጥን የሥነ ልቦናና ወታደራዊ ዝግጁነቶችን በመላበስ በህልውናው ላይ የመጣን ጠላት ለመደምሰስ እየተደረገ ያለውን ጥረት እንዲያግዝ ጥሪ ማቅረባቸውን ከደቡብ ወሎ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ