
“አሸባሪው ትህነግ አሁን ወደ ደደቢት በርሃ ሳይሆን ወደ መቃብር መውረድ አለበት” በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁር
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የራሷ ነፃነት፣ ጀግንነት፣ አኩሪ ድል፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ፣ ወግ እና የተፈጥሮ ጸጋ ባለቤት ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ተጠብቃ ቆይታለች።
ክብሯን በሚያስጠብቁ ልጆቿም በዓለም አደባባይ ስሟ ከፍ ብሎ ተደማጭነትን አግኝታለች።
አሸባሪው ትህነግ ስልጣን ላይ በቆየባቸው ጊዜያት የሀገር ሀብት ዘርፏል፤ በዘረፈው የሀገር ሃብት በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ቅጥረኞችን በማስቀመጥ የኢትዮጵያን ሳይሆን የራሱን ተቀባይነት ለማጉላት ለዘመናት ሠርቷል።
መምህር ቱሬ መኳንንት በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ ትምህርት ክፍል መምህር ናቸው። ሽብርተኛው ትህነግ ወደ ስልጣን ሲመጣ ከእሱ በፊት የነበሩ የመንግሥታትን ሥራ በውሸት መርዝ ቀምሞ፣ ሕዝብ በጥላቻ እንዲተያይ ሠርቷል ብለዋል።
“አሁንም ኢትዮጵያን ለማፍረስ መነሳቱን ያወጀው አሸባሪው ቡድን ሕዝብን ለማወናበድ የምዋጋው ከአማራ ኤሊትና ከእሱ ደጋፊዎች ጋር ነው፤ ከሕዝብ ጋር አይደለም” በማለት የተለመደ የውሸት ማደናገሪያውን እየረጨ ነው ብለዋል መምህር ቱሬ።
በ1967 ዓ.ም በደደቢት በርሃ ተመስርቶ የትግራይን ሕዝብ ነፃ አወጣለሁ በማለት አማራን ደግሞ በጠላትነት ፈርጆ ለዓመታት መሥራቱን ተናግረዋል።
“ አጥፊ ቡድኑ አሁን ወደ ደደቢት በርሃ ሳይሆን ወደ መቃብር መውረድ አለበት” ብለዋል።
የታሪክ መምህሩ እንዳብራሩት አሸባሪው ትህነግ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚጥሩ ሀገራት ጋር ሽርክና ፈጥሮ ኢትዮጵያን ለውጭ ጠላት አሳልፎ ሰጥቷል፡፡
አሸባሪው ትህነግ ከሸኔ ጋር የመሠረተው ጋብቻም ሀገር ለማፍረስ የሚያደርገው ጥረት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ቡድኑ ይህን ቢያደርግም አሁን ሕዝባዊ ማዕበል ሊበላው ተቃርቧል ነው ያሉት የታሪክ ምሁሩ።
መምህር ቱሬ ሽብርተኛው ትህነግ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የፈፀመው የመጀመሪያው ሴራ ሕዝቡ ያላመነበትን የራሱ ማኒፌስቶ የሆነውን ሕገ መንግሥት አርቅቆ ተግባራዊ ማድረጉ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ሕዝብ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ሳያረጋግጥ ለዘመናት እንዲዘልቅ ማድረጉን ገልጸዋል።
በተለያዩ መንገዶች የፈጠራቸው የኢኮኖሚ አሻጥሮችን በመጠቀም በእርዳታ የሚመጣ ገንዘብን ለራሱ ቡድን አውሎታል፤ ሌላውን ማኅበረሰብ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ውጭ አድርጓል ሲሉም ተናግረዋል።
መምህር ቱሬ ሀገሪቱን ለማዳከም የተጠቀሙበት አንዱ ስልትም ወደብ አልባ ማድረግ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ይህም ሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መሥተጋብር እንድታጣ አድርጓታል ይላሉ። አሸባሪው ትህነግ በስልጣን ዘመኑ የቋንቋና የባህል እኩልነት አመጣለሁ እያለ ብሔርን ከብሔር አጋጭቷል፤ አንዱ ጨቋኝ ሌላው ተጨቋኝ፣ አንዱ የበላይ አንዱ የበታች በማስመሰል የጋራ ስሜትን አደብዝዞ ቆይቷል ብለዋል፡፡
ሽብርተኛው ትህነግ አሁን የፈጸመውን ወራራ ለመመከት የከፋፈላቸው ብሔር ብሔረሰቦች ሴራውን ቀድመው ተረድተው በአንድነት እንዲቆሙ እንዳደረገ ምሁሩ አንስተዋል፡፡ እንደ መምህሩ ገለጻ ከሽብርተኛው ትህነግ ውድቀት በኋላ በሕዳሴ ግድብ ላይ የተሠራው ሥራ እና ሀገሪቱን ለውጭ ጣልቃ ገቦች አሳልፎ ላለመስጠት የሚደረገው ትግልም የሚያኮራ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ አሸባሪውን በመፋለም የጋራ ታሪክ ለመሥራት ቆርጦ መነሳት አለበትም ብለዋል። በውጭ የሚገኙት ኢትጵያውያንም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የአሸባሪውን ቡድንና የውጭ አጋሮቹን ሴራ እውነቱን ማሳወቅ እንዳለባቸው አብራርተዋል።
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው -ከደባርቅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ