
አባቶቻችን ብለን ስንጀምር ቀድሞ የሚመጣው ድል አድራጊነታቸው ነው። “የአባቶቻችን ልጆች ነን” ስንል ኩራት እንጅ ሀፍረት አይሰማንም። አባቶቻችን ጠላትን አንበርክከው ሀገር ስላቆሙ የምንኮራባቸው ናቸው። በዚህም ምክንያት ስለ አባቶቻችን ታሪክ ሲወራ እኛም የእነሱን ፈልግ መከተል የግድ እንደሚለን እንተማመንበታለን። ለዛም ነው እንደ አባቶቻችን እንሁን የምንለው።
“እንደ አባቶቻችን እንሁን” ስንል አባቶቻን ያበረከቱትን አስተዋፅኦ በሀቀኛ ታሪክ አስመስክረን ነው። ከጥንት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ድል አድርገው ሀገር ያቆዩበት ታሪክ በተጨባጭ አለን። ያም ሆኖ ግን ብዙ ወደኋላ ታሪክ መጓዝ ሳያስፈልገን የቅርብ ጊዜ ገድሎችን አንስተን የቀጠለውን የአባቶቻችን ታሪክ መድገም እንዳለብን የሚያስገነዝቡ ሀቆችን መጥቀስ እንችላለን። ወደኋላ ታሪክ ሳንሄድ በቅርብ አመታት የሆነውን እንመልከት። 2008 ዓ.ም፣ በዚህ ረገድ አርበኛ ጎቤ መልኬን መጥቀስ እንችላለን!
አርበኛ ጎቤ መልኬ በሰላም ጊዜ ገበሬ፣ ሕዝቡ በተጠቃበት ወቅት የጦር መሪ ሆኖ ያገለገለ አርበኛ ነው። ገበሬም የጦር መሪም ሲባል እንዲሁ በጥቅል ተጠቅሶ የሚያልፍ ብቻ አይደለም። ዝርዝር፣ ትውልዱ ሊማርበት የሚገባው ታሪክ አስደማሚ ታሪክ ባለቤት ነው።
በሬ ለሌለው ገበሬ በሬ የሚሰጥ፣ የታመመች እናትን ወሰ ስራ የሚሄደውን መኪናውን መልሶ ወደ ሕክምና ጣቢያ የሚያደርስ ነበር ጎቤ። 48 ኪሎ ሜትር መንገድ በራሱ ቀይሶ፣ በራሱ ወጭ አስመንጥሮ የሰራ፣ በአማራ ክልል መንግሥት “መሃንዲስ” ተብሎ የክብር ማዕረግ ተሰጥቶታል። ሌሎች ሁለት መንገዶችንም ሰርቷል። እሱ ቀይሶ የሰራው መንገድ በአስፓልት ሲሠራ መሃንዲሶቹ ለክብሩ በየመንገዱ የሚሰሩት ምልክቶች ላይ “ጎ” ፅፈውለታል።
አርበኛ ጎቤ መልኬ ሰፋፊ እርሻ ባለቤት ከሆኑት የአርማጭሆ ገበሬዎች መካከል አንዱ ነበር። ከአዝዕርት ሰብሉ በተጨማሪ የመስኖ ልማትን ለአካባቢው ሕዝብ ያስተማረ አርበኛ ነው። ከአምስት መቶ የሚልቅ የቀንድ ከብቶች፣ ፍየሎችና በጎች ነበሩት። ይህ ሀብቱ ግን ለነፃነቱ ዋጋ ለመክፈል አላሳሳውም።
አሸባሪው ትህነግ ቤተ መንግሥት እያለ በአማራ ሕዝብ ላይ ይፈፅም የነበረውን በደል እያየ ማለፍ ባለመቻሉ ሀብት ንብረቱን ትቶ ዱር ቤቴ ብሎ ዋጋ ከፍሏል።
ወልቃይት ጠገዴ ጠለምትና ራያን ገና ሕገ መንግስቱ ሳይረቀቅ ሕገወጥ በሆነ መልኩ ወደ ትግራይ የከለለው ትህነግ በቅርብ አመታት ደግሞ ግጨውና ጎቤ የተባሉ የጠገዴ ሰፋፊ እርሻ ቦታዎችን ከአማራ ለመንጠቅ ሲሠራ ፊት ለፊት ከተጋፈጡት ጀግኖች መካከል ጎቤ መልኩ አንዱ ነው። ጉዳዩ በሀገሬው ሽማግሌዎች ምስክርነት ይለቅ ሲባል ትህነግ በመንግሥት በጀት በሐሰት የሚመሰክሩለትም ከትግራይ የመጡ ሰዎች ሲሰበስብ ጎቤ መልኬ በበኩሉ በእውነት የሚመሰክሩለትን በርካታ ሽማግሌዎችን አዘጋጀ። በምስክርነቱ ወቅት ትህነግ ካዘጋጃቸው ይልቅ እነ ጎቤ ያዘጋጇቸው ሽማግሌዎች ቃል አሸናፊ ሆነ። ይህን እውነት መቀበል ያልወደደው ትህነግ አሻፈረኝ አለ። ከሰላማዊ ድርድር ውጭ የሚተማመነውን ስልጣኑንና ሠራዊቱን ለመጠቀም ሲያስፈራራ እነ ጎቤ መልኬ “ይለይልናል” ብለው ማስፈራሪያውን ውድቅ አደረጉት። ይህ የትህነግ ትንኮሳ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት ጥያቄን እንደ አዲስ አጎላው። ከጎቤና ከግጨው ሰፋፊ ግዛቶችና በአካባቢው ከሚኖረው የአማራ ሕዝብ በላይ ትህነግ ያጠፋው ማንነት ላይ በሰፊው ትኩረት ተደረገ።
በወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት ጥያቄ ትግል ውስጥ የእነ ጎቤ መልኬ ሚና ከፍ ያለ ነበር። ከ15 በላይ ወጣቶችን ከወልቃይት ጠገዴ አስመጥቶ መሳርያ ገዝቶ አስታጥቆ ታጋይ አድርጓል። ትህነግ ይህን የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት ጥያቄ በኀይል ለመጨፍለቅ ሲነሳ እነ ጎቤ ተናንቀውታል።
ሀምሌ 5/2008 ዓ.ም ጎቤ መልኬ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ተኝቶ ነበር። ህመሙ ቀላል አልነበረም። የዓይን ሕመም ነው። ዓይኑ ቀዶ ጥገና ተደርጎለት ተሸፍኗል። ትህነግ የፈፀመውን ውንብድና ሲሰማ ግን ጎቤ መልኬ አይኑ ላይ የተደረገለትን መሸፈኛ አንስቶ የኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ከበባ ለመስመር እሄዳለሁ አለ። የታመመ፣ ያውም ዓይንን ያህል ቀዶጥገና የተደረገለት ሰው የተሸፈነውንና ያልዳነውን የዓይኑ ቁስል ላይ የተሸፈነውን አውልቆ ወደጦር ሜዳ ይሄዳል ብለው አላሰቡም። ጎቤ ግን የዓይኑን ሕመም ረስቶ ጦር መርቶ ሲፋለም ዋለ። ኮሎኔል ደመቀ ከቤት ከወጣ በኋላ የአካባቢውን የፖለቲካና የጸጥታ አመራሮች “አሳልፋችሁ ብትሰጡት ደሜን የማነሳው ከእናንተ ነው” ብሎ ለአንድ ባለፀጋ ወደማይመቸው ጫካ አቀና።
ከሀምሌ 5/2008 ዓ.ም በኋላ ትህነግ የሕዝብን ንቅናቄ ለማዳፈን ሲጥር እነ ጎቤ መልኬ “ኧረ ጥራኝ ዱሩ” ብለው ትግሉ እንዳይኮላሽ አድርገዋል። ጎቤ መልኬ በፋኖነት ትግሉን ሲያስቀጥል በርካታ አማራዎች እንዲገድሉት ተልከውበታል። ስልጠና እንዲሰጣቸው፣ አሊያም መንግሥት እያሳደዳቸው ለመጠለል አስመስለው ወደ እነ ጎቤ መልኬ ጦር ይቀላቀላሉ። ዓላማቸው ግን ጎቤን መግደል ነበር። በክትትል ተነቅቶባቸው ሲያምኑ ታዲያ ጎቤ መልኬ “ለምን የራሳቸውን ሰው አይልኩም? የእነሱ ዓላማኮ እኔ ወንድሜን እንድገድል ነው። እኔ አንተን ልገድል ሳይሆን ለአንተ ነፃነት ነው ጫካ የወጣሁት” ብሎ መክሮና አሳምኖ ይለቃቸዋል።

ጎቤ መልኬ ሀብት ንብረቱን፣ ቤተሰቡን፣ ምቾቱን ትቶ በዱር በገደሉ እየተንከራተተ በሚታገልበት ወቅት መኪናዎቹ በትህነግ ተይዘውበታል። ትህነግ የሚመራው ጦር ፍየልና በጎቹን አርዶ ይበላል። ይሄ ሀብት ንብረቱ መውደሙ አያስጨንቀውም ነበር። የእሱ ዓላማ አማራን ነፃ ማውጣት ነበር። ለራሱ ጦር ከ12 በላይ በሬዎቹን አርዶ አብልቷል። የጎቤ ጦር አባላት ጎቤ ለሠራዊቱ የሚያርደውን በሬና የሚያወጣቸውን ወጭዎች ሲመዘግቡ “አርፋችሁ ተቀመጡ። እኔን ዋጋ የሚከፍለኝ ነፃነት ብቻ ነው” ይላቸው እንደነበር ይናገራሉ።
ጎቤ በርካታ አውደ ውጊያዎችን መርቷል። ሦስት ቀን በተደረገ ውጊያ ትህነግ የላከው ኃይል አስከሬን ማንሳት ሳይችል ቀርቷል። በውጊያ እጁን ተመትቶ፣ ጣቶቹ ቆሳስለውም ጦሩን በጀግንነት ይመራ ነው። ለትግሉ ብሎ የዓይኑን ሕክምና አቋርጦ ዓይኑንም እየታመመ ለሕዝብ ነፃነት ትህነግን ሲተናነቅ መስዋእትነት የከፈለ ጀግና ነው።
ጎቤ መልኬ አልተማረም። ለአማራ ሕዝብ ነፃነት የተዋደቀው ምሁራዊ ትንታኔ ሰምቶ አይደለም። ትህነግን የተፋለመው ከርዕዮት ዓለም አንፃር ዝርዝር ጉዳይ ተመልክቶ አይደለም። ትህነግ የሚፈፅመውን ወንጀልና በደል ስለተረዳ ነው። ትህነግን ለመታገል ምሁራዊ አመክንዮ አልጠበቀም። የሚያየው በቂው ነበር።
ጎቤ መልኬ ባለሀብት፣ የቤተሰብ መሪ ነበር። ትህነግ የሚፈፅመውን በደል እያየ ግን ሀብትና ቤተሰቡ አልጎተተውም። የአማራ ሕዝብ ቀጣይ እጣ ፈንታ ከሀብቱ፣ ከክብሩ፣ ከቤተሰቡ፣ ከነፍሱ በልጦበት ያለውን ሁሉ ለአማራ ሕዝብ ነፃነት ከፍሏል። ምቹ ክፍሎቹን ትቶ ድንጋይ ተንተርሶ የታገለው ትህነግ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፅመውን በደል ስለተመለከተ ነው። የሞቀ ቤቱን ትቶ ጫካ ለጫካ የተንከራተተው ትህነግ በአማራ ሕዝብ ሕልውና ላይ የደቀነው አደጋ ስለገባው ነው። በእርግጥ የትህነግ ክፋትና በደል ገብቷቸው ዝም ብለው የሚመለከቱ ሞልተዋል። ጎቤ መልኬ ግን ትህነግ የሚፈፅመውን በደል እያየ ቁጭ ብሎ ማየት አልቻለም።
ዛሬ ጎቤ በሕይወት ባይኖርም በትውልዱ ዘንድ ክቡር ነው። ሥራው ሁሌም የሚታወስ ነው። መስዋእትነቱ የሚዘከር ነው። የተሰዋው ለሕዝብ ክብር ነውና ተከብሮ ይኖራል። ወጣቱም እንደ ጎቤ መልኬ ያሉትን ሲያስታውስ ተግባራቸውን መውረስ አለበት።
በጨለማው ዘመን ትህነግን የተፋለመው ጎቤ በሕይወት ቢኖር ዛሬም ትህነግን ከፊት ሆኖ ይጋፈጠው እንደነበር ጥርጥር የለውም። ዛሬ ጎቤ በሕይወት የለም። በሕይወት ያለው ተምሳሌትነቱ ነው። ጎቤን ስናደንቀው፣ ስናከብረው መኖር ብቻ በቂ አይደለም። ምሳሌነቱን መከተል ያስፈልጋል። ሀብት፣ ንብረት፣ ምቾት፣ ቤተሰብ፣ ሕይወት ከሕዝብ እንደማይበልጥ በማሳየት ጎቤነትን ማስቀጠል ያስፈልጋል።
ድምፀ መረዋው ሰለሞን ደምሌ “ኧረ ጎቤ” በተሰኘው ሙዚቃው
“የገብርዬ የካሳ ሲገርመኝ፣
ጎቤ ደገመኝ።
ጀግንነት ወርሶ ከአባት ከአያቱ፣
አይደራደር በማንነቱ።
የማይጨበጥ ክንደ ነበልባል
ከጠላት መሃል ድንገት ይገባል።
ተትረፍርፎለት ሀብት ንብረቱ
ነፍሱን ሸለማት ለማንነቱ ይለዋል።
ጎቤ እንደ ካሳና እንደ ገብርዬ እንዳስገረመው፣ እኛም እንጎቤ በጀግንነታችን ማስገረም አለበት። ሀብት ንብረት ሳንል ለሕዝብ ነፍሳችን ለመሸለም መቁረጥ ይገባናል። የአባቶቻችን ልጆች ነን ማለት የምንችለው ያኔ ነው።