
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 08/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ጠላቶች ይፈሩታል፣ ይበልጣቸዋልና ይጠሉታል፣ ወዳጆች ያከብሩታል፣ ዝናውን ይመሰክሩለታል፣ ስሙን እየደጋገሙ በመልካም ያነሱታል። ሲወዱት ፈትፍቶ አፈር ስሆን እያለ ያጎርሳል፣ አሳምሮ ያለብሳል፣ ከፍ አድርጎ ያነግሣል፣ እልል ብሎ ይድራል፣ ይኩላል፣ ወግ ማዕረግ ያሳያል፣። ሲጠሉትና ሲነኩት ደግሞ አነጣጥሮ ይተኩሳል፣ እንደ ንብ ሆ ብሎ ይነሳል፣ እንደ አንበሳ ያገሳል፣ ነፍጡን ያነሳል፣ ተመልከት እያለ ግንባር ይበሳል።
በጦር አይሸነፍም፣ ከወሰን አያሳልፍም፣ ልቡ የኮራ፣ ታሪኩ የጠራ፣ በየዘመናቱ በጥበብ የመራ፣ በጨለመ ዘመን የማይጠፋ ጀንበር ያበራ፣ የልቡን የሠራ፣ ለክፉ ቀን የሚጠራ ነው። ና ሲሉት ፈጥኖ የሚደርስ፣ አድርግ ሲሉት አንጀት የሚያርስ፣ በታሪኩ እንከን የሌለበት፣ ኃያላኑ የሰገዱለት፣ ጀግንነቱን የመሰከሩለት፣ ጠላቶች የሮጡለት፣ በግርማው እጅ የነሱለትም ነው።
አትግጠሙት አትችሉትም፣ አትግፉት አትጥሉትም፣ አትድከሙ አታልፉትም፣ አትጎትቱት አትስቡትም፣ ስትገጥሙት ይመታችኋል፣ ስትሞግቱት ይረታችኋል፣ ስትጎትቱት ይጥላችኋል፣ ድንገት መብረቅ ሆኖ ደርሶ የሚያደርቅ ይሆንባችኋል፣ መሠረቱ አለት፣ መለያው ጀግንነት፣ የልቡ ምት ኢትዮጵያዊነት፣ አንድነት፣ በመከራ መፅናት፣ በጭንቅ ጊዜ ጎልቶ መውጣት ነው።
ጠላቶች ቢበዙም፣ መንገዶች ሁሉ የተዘጋጉ ቢመስሉም ጀግናው መውጫ ቀዳዳ፣ የመፍትሔ ቁልፍ አያጣም። ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም ነውና ነገሩ። የጣልያን ሠራዊት ከሮም ሲንቀሳቀስ፣ በጣልያን መኳንንት እና መሳፍንት አዛዥነት ለድል ድግሥ ሲደግስ፣ ዓለም ደነገጠች፣ ወዮላት ለዚያች የጥቁር ምድር፣ እንዳልነበር ልትሆን ነው፣ እሳቱ ሊገርፋት፣ የሮም ማዕበል ሊውጣት ደርሷልና ወዮላት፣ ምን ጭንቅ ጣለባት አሉ። የሮም ሠራዊት በተለያዩ ግንባሮች ድል ቀንቶት ነበርና ከማሸነፍ ውጭ ጥርጣሬ የገባው አልነበረም። ጠባቂዋ ከምድር ነገሥታት ሁሉ በላይ የሆነው፣ ቅድስቷ ምድር፣ የጀግኖች ሀገር የተደገሰባትን ድግስ እስኪቀርብ ድረስ ዝም አለችው።
የሮም ሠራዊት “ኢትዮጵያ ቅርብ ሮም ሩቅ” ብሎ ተነሳ። ግስጋሴያቸው ፈጠነ ። የሮም አደባባዮች በደስታ ተመሉ፣ ሴቶች እልል አሉ፣ ጎበዛዝቱ በአደባባዩ ተንጎማለሉ። ለተስፋ፣ ለምስክር፣ ለፍቅር እና ለክብር የቀረችው የሰው ዘር መገኛዋ ድንቋ ምድር ድርብ ኃላፊነት ነበረባት። በወራሪዎች ተከልላ በአፍሪካ ምድር ብርሃኗን የጋረደችው ጀንበር ፈፅማ እንዳትጠፋ እና ዳግም ትወጣ ዘንድ ድንቋ ምድር አደራ አለባት፣ ጥቁሮች ፈጣሪ ያከበራትን፣ በየዘመናቱ ከፍ ከፍ ያደረጋትን፣ የአሸናፊነት ጋሻ የሰጣትን ሀገር ተስፋ አድርገዋል። የሮም ማዕበል ካጥለቀለቃት የተስፋዋ ጀንበራቸው ፈፅማ ትጠልቃለች፣ በአሻገር የምትታያቸው ተስፋ ትጠፋለች። እውነተኛው አምላክ ለእውነተኛዋ ምድር ፍርዱን ይሰጥ ዘንድ እየተመኙ ዝም አሉ። ይህች ውብ ምድር ለሌሎች ተስፋም ብቻ ሳትሆን በታሪኳ አይታው የማታውቀውን ሽንፈት ላለመቅመስ፣ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር የአባትና የእናት አደራም ይዛለች። አደራ ከመብላት መሞት ይሻላል ይላሉና አደራዋን ፈፅማ አትበላውም። የጥቁሮችን ተስፋም አታጨልመውም። እውነተኛውን አምላክ ይዛ፣ ለእውነተኛው ተጋድሎ ትገባለች እንጂ።
ዓለማት በአፍሪካ ምድር በምሥራቅ ንፍቅ በምትገኘዋ ቀዳሚት ሀገር የሚሰማውን ዜና ለመስማት ጓጉተዋል። የጣልያን ሹማምንት ደስታው ፈንቅሎ ሊጥላቸው ነው። “የምኒልክ ተስፋው እግዚአብሔር ነው” ብለው ተስፋቸውን በእግዚአብሔር የጣሉት ከታላቁ ሕዝብ የወጡት ታላቁ መሪ በዛቻው ሳይደናገጡ በብራና ግማሽ ጥሪያቸውን አቀረቡ። ነገር አላበዙም የሚወዳቸውንና የሚወዱትን ሕዝብ ለሚወዳት ሀገሩ ይዋደቅ ዘንድ በግማሽ ብራና ቃላቸውን አስፍረው፣ ነጋሪት አስጎሰሙ፣ አዋጅ አሰሙ። ” …….. እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር። አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት ሀገሬን አሳልፌ አልሰጠውም። የሀገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም። አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ ለሚስትህ ለሃይማኖትህ ስትል በሀዘን እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ። አልተውህም። ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም።…..” በሰንደቅ ተጠርቶ፣ የኢትዮጵያ ስም ተነስቶ፣ የንጉሡን ቃል ሰምቶ ችሎ የሚያድር የለምና የሀገሬው ሰው ስንቁን ቋጠረ፣ ትጥቁን አጠበቀ። ዘመቻው ተጀመረ።
በግማሽ ብራና የሠፈረችው የእናት ሀገር ጥሪ፣ ከሮም አደባባይ ድንፋታ፣ ከወይዛዝርቱ እልልታ ሁሉ ከፍ ብላ ተሰማች። ሀገር አሰባሰበች፣ ሕዝብ አንድ አደረገች።
“ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ” እቴጌ ጣይቱ ነገሩን ሁሉ በጥበብ ያስሄዱት ጀምረዋል። በአንድነት፣ ለኢትዮጵያዊነት ለአሸናፊነት ተጋጠሙ። የዓለም ግምት ወና ሆነ። በግማሽ ቀን የተዳከመችው የጥቁሮች ጀንበር በዓለም ዙሪያ ከፍ ብላ አበራች። ከወደ ሮም የድል ዜና የሚጠብቁ ጀሮዎች ያልጠበቁት ደረሳቸው። ድንጋጤ ወረሳቸው፣ የኢትዮጵያውያን ጀግንነት አንገታቸውን አስደፋቸው። የሮም አደባባዮች ቆፍን ያዛቸው፣ ነገሥታቱ፣ መኳንንቱና መሳፍንቱ ወኔ ራቃቸው። ወይዛዝርቱ ሀፍረት ወረሳቸው። ዳሩ አርፈው አልተቀመጡም፣ ዓመታት አስልተው፣ በብዙ ተዘጋጅተው ሌላ እድል ሞከሩ፣ እድል ከዳቸው ጀንበር ጠመመችባቸው፣ ወደ ኢትዮጵያ አዘነበለችባቸው። ሠራዊቱን ሁሉ የኢትዮጵያውያን ጎራዴና ጦር በልቶ አስቀረው።
አንተ የምኒልክ ልጅ ነህ፣ ጀግንነቱ የገዘፈው፣ ዝናው ከዓለም እስከ ዓለም በተስፋፋው። አንተ የእነዚያ አርበኞች ልጅ ነህ ሳንጃህ ድል የሚሸተው፣ የማይሸበሩት፣ የማያወላውሉት፣ በወዳጅ ሳይሆን በጠላት አንደበት የተደነቁት። አንተ የጀግኖች ልጅ ነህ በደምህ እና በአጥንትህ ሀገር የገነባህ፣ ለሀገር ፍቅር ለሀገር ክብር ስትል ነብስህን ያለ ስስት የሰጠህ። አዎን አንተ የጀግና ልጅ ጀግና አማራ ነህ። ልብ በል ዛሬም እንደ እምዬ ምኒልክ ለሀገር ፍቅር ለወገን ክብር ሲባል ክተት ተብለሃል።
ጠላት አንገትህን ሊያስደፋህ፣ ከመንገድህ ሊገታህ፣ በሚስትህ፣ በልጅህ፣ በርስትህና በሃይማኖትህ መጥቶብሃል። እንደ ትናንቱ ተነስተህ፣ እንኳን ተላላኪውን ላኪውንም እንዳልነበር እንዳደረከው ንገረው። እንዳልነበር አድርገው፣ በምድርህ የተዘራውን ክፉ አረም ንቀለው። ዝም ብለህ ብትቀር ግን የእነ ምኒልክን አደራ፣ የአምስት አመቱን አርበኞች ቃል ኪዳን አደራ ትበላለህ። ሞተው መኖርን አስተምረውሃል። አንተም ለክብር ተነስ፣ ጠላትህ ምሎ ተገዝቶ ሊያጠፋህ ተነስቷልና።
እንደ ቀደመው ዘመን በክተቱ ተነስተህ በእኩለ ቀን ጠላትህ አጥፍተህ ተመለስ። አንተ በስምህ፣ በግብርህ፣ በአፈጣጠርህ፣ በታሪክህ ነፃ የሆንክ ሕዝብ ነህ። ነፃነት የሚጋፋ፣ እሴት የሚያጠፋ፣ አንገት የሚያስደፋ በመጣብህ ጊዜ ሁሉ እየመታህ መልሰሃል፣ አንገቱን አስደፍተሃል፣ በጠላቶችህ መቃብር ላይ ነፃነትክን አውጀሃል። ታዲያ በዚህ ዘመንስ አንተን ማን ችሎ ይገፋሃል?
አሸባሪው ትህነግ በዙሪያ ገባህ ከቧል፣ እድል ካገኘ ያስከፋሃል፣ ነፃነትክን ይገፋሃል፣ ዛሬ ተነስ ቆመህ እንዳትጠብቀው፣ በየአገኘህበት ስበረው። በደረሰበት ቅበረው። አማራ እንደማይሸነፍ፣ ከክብርህ የሰናፍጭ ፍሬ ያክል እንደማታስነካ አሳየው። አዎን አንተ የማትሸነፈው አማራ ነህ! ታሪክ በወርቅ ቀለም የዘከረህ፣ ጠላትህን አሸንፈህ በመቃብሩ ላይ ታሪክህን ከፍ የምታደርግ። ተሰብሰብ እና ድልህን አፍጥን።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m