በአማራ ክልል አራት ዞኖች የተቀናጀ የግብርናና ገጠር ልማት የመንደር ንቅናቄ የሙከራ ትግበራ ላይ መሆኑ ተገለፀ፡፡

468

ባሕር ዳር፡ መስከረም 15/2012 ዓ/ም (አብመድ) አርሶ አደር መኳንንት ዘሪሁን እና አርሶ አደር ሰጠኝ ኃይሉ በበደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ ወንጪት ቀበሌ ታች ቀረር ጎጥ ነዋሪ ናቸው፡፡ የአማራ ክልል እና የኮሪያ መንግሥት በትብብር በዘረጉት የተቀናጀ የግብርናና ገጠር ልማት ሥራዎች የመንደር ንቅናቄ በእንስሳት እና በጓሮ አትክልት ልማት እየሠሩ ነው ያገኘናቸው፡፡

አርሶ አደር ሰጠኝ ኃይሉ የተቀናጀ የእንስሳት እርባታ፣ አርሶ አደር መኳንንት ደግሞ የተቀናጀ የጓሮ አትክልት ልማትን እየተገበሩ ነው፡፡ ሥራው ገና በሂደት ላይ ያለ በመሆኑ ጥቅሙን ለመናገር ይቸግራል፤ ነገር ግን በትንሽ መሬት እና በውስን ሀብት እርስ በርሱ የሚመጋገብ የግብርና ልማት ሥራ እየሠሩ በመሆኑ ተስፋ እንዳደረጉ ነግረውናል፡፡

በኮሪያ መንግሥት እና በአማራ ክልል የተቀናጀ የገጠር ልማት ስትራቴጂ እና ሞዴል ማማከር ፕሮጀክት ከፍተኛ የእንስሳት ባለሙያው አቶ ሳሙኤል ይማም ፕሮጀክቱ የሥነ አመጋገብ ችግርን ለመፍታት፣ ለሥነ ምኅዳር ጥበቃ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና አማራጭ የገቢ ምንጭ ሆኖ እንዲያገለግል ታስቦ የተቀረፀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹የሙከራ ትግበራ ሂደቱ በአማራ ክልል በአራት ዞኖች ውስጥ ባሉ አራት ወረዳዎች እና ስድስት ቀበሌዎች ውስጥ ባሉ 20 መንደሮች እየተተገበረ ይገኛል›› ተብሏል፡፡ የሙከራ ትግበራ ከሚፈፀምባቸው ዞኖች ውስጥ ደቡብ ጎንደር አንዱ ነው፡፡ በዚሁ ዞን ውስጥ በደራ ወረዳ ወንጪት ቀበሌ ውስጥ 22 ግሪን ሃውስ፣ 23 ባዮ ጋዝ፣ 33 የዶሮ እርባታ እና በርካታ የተቀናጁ የጓሮ አትክልት እና የዓሳ እርባታ በፕሮጀክቱ ሙከራ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ አርሶ አደሮቹ አማራጭ የውኃ አቅርቦት፣ ሙያዊ እና የቁሳቁስ ድጋፍም ተደርጎላቸዋል ተብሏል፡፡

በክልሉ በሚገኙ ዞኖች እና ወረዳዎች በባሕር ዳር ተሰባስበው የሚመክሩት የአዴፓ አባላት እና ከፍተኛ መሪዎች ዛሬ ጠዋት በደራ ወረዳ ወንጪት ቀበሌ ተገኝተው የፕሮጀክቱን የትግበራ ሁኔታ ጎብኝተዋል፡፡ ከሰሜን ሽዋ ዞን የመጡት የእንሳሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደምሰው መንበሩ ያዩትን እንደ ወረዳቸው ተጨባጭ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ እና ለማስፋት ማሰባቸውንም ለአብመድ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Previous articleሱዳንና ደቡብ ሱዳን የኢጋድ አባል ሀገራት ለሰላማቸው እገዛ እንዲያደርጉላቸው ጠየቁ፡፡
Next articleቺርቤዋ-15-1-2012