
ከተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች ከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ገልጿል።
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 08/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አበበ ገብረ መስቀል ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ወገኖችን የሚቀበሉ ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን ገልጸዋል። ለተፈናቀሉ ወገኖች ስምንት መጠለያ ጣቢያ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል። ለተፈናቃዮችም ከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እያደረገ ነውም ብለዋል።
በከተማዋ 55 ሺህ የሚገመት ተፈናቃይ ወገኖች መኖራቸውንም ገልጸዋል። የከተማዋ ማኅበረሰብ ለተፈናቃዮች እያደረጉት ያለው ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑንም ተናግረዋል። ወሎ የመተሳሰብና የፍቅር ሀገር መሆኑን አስመስክረዋልም ነው ያሉት። ለተፈናቃዮች ድጋፍ የማድረጉ ሥራም ይቀጥላል ነው ያሉት።

የከተማዋን ሰላም አስጠብቆ ለመዝለቅ ልዩ ልዩ ተግባራት ተከናውነዋል ያሉት ከንቲባው አሸባሪው የትህነግ ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያደርገውን እኩይ ድርጊት ለመቀልበስ አደረጃጀት ተሠርቷል ብለዋል። የከተማዋን ደኅንነት የሚጠብቅ ተጠባባቂ ኃይል ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።
የከተማዋ ወጣት ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ ሥራዎችን እየሠሩ ነው ብለዋል። ወጣቶች ፀጉረ ልውጥን በመቆጣጠርና ኬላዎችን በመጠበቅ እየሠራ ነውም ብለዋል።
በከተማዋ የተጣለው የሰዓት ገደብ ፀጉረ ልውጦችን ለመያዝ እንዳስቻላቸውም ተናግረዋል።
በከተማ አስተዳዳሩ የጸጥታ፣ የሀብት አሰባሳቢ እና ሌሎች ኮሚቴዎች ተቋቁመው እየሠሩ መሆናቸውም ተናግረዋል። ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ አባላት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት ከንቲባ አበበ፡፡
በከተማዋ በአይነትም በገንዘብም 50 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡንም ገልጸዋል። የከተማዋ መሪዎችም በከፍተኛ ተነሳሽነት እየሠሩ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።
ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ