
ባሕር ዳር: ነሐሴ 08/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገር መከላከያ ሠራዊትንና የሶማሊ ክልል ልዩ ኀይል የሚደግፍ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ዛሬ በጅግጅጋ ከተማ ተካሂዷል።
በጅግጅጋ ከተማ ስታዲዬም በተካሄደው ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የከተማው ነዋሪዎች ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍና አሸባሪውን የሕወሓት ቡድን የሚያወግዙ የተለያዩ መልክቶችን አስተላልፈዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር ሙስጠፌ ሙሐመድ እንዳሉት አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ለረጅም ጊዜ ሲሠራ የቆየውን ኢትዮጵያን የማፍረስ እኩይ ድርጊቱን ለማክሸፍ ሁሉም ዜጋ በአንድነት ሊረባረብ ይገባል።
አሸባሪውን የሕወሓት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ግብዓተ መሬቱን በመፈፀም የሀገሪቱን ሰላም ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የሶማሌ ሕዝብ ባለፉት 30 አመታት በጁንታው የተጎዳ ሕዝብ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ርእሰ መሥተዳደሩ የክልሉ ሕዝብ አሸባሪውን የሕወሓት ቡድን ለማጥፋት ከመላው የሀገሪቱ ሕዝብ ጎን ተሰልፎ የሚጠበቅበትን ተጋድሎ ያደርጋል ብለዋል።
ወቅቱ የመላው የሀገሪቱ ሕዝቦች አንድነት የሚያስፈልግበት ወቅት በመሆኑ ኅብረተሰቡ በየአከባቢው ግጭትና መከፋፈል የሚፈጥሩ ኀይሎችን እኩይ ሴራ በማክሸፍ በፍቅርና በአንድነት መንቀሳቀስ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የከተማው ነዋሪዎች አሸባሪው ሕወሓት ንጹሓን ዜጎችን በመግደልና በመጨፍጨፍ ታሪክ ይቅር የማይለው የጥፋት ተግባር እየፈፀመ መሆኑን ገልጸዋል።
የሀገር ነቀርሳ የሆነውን አሸባሪውን ቡድን በተባበረ ክንድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊነቀል ይገባል ብለዋል።
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ባለፉት 30 ዓመታት በሶማሊ ክልል ሕዝብ ላይ የፈፀመው አስከፊ በድሎችን እንደፈጸመ የገለጹት ነዋሪዎቹ አሸባሪውን የሕወሓት ቡድን ለማጥፋት በሚደረገው ትግል ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከሌሎች የሀገሪቱ የጸጥታ አካላትና ከሕዝቡ ጋር ተሰልፈው የህይወት መሰዋእትነት ለመክፈልና የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን እንደገለጹ ከሶማሊ ክልል መገናኛ ብዙኀን ኤጀንሲ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ