
❝ህልውናችንን ለማስጠበቅ ከሚያስፈልጉን ሥነ ልቦናዊ፣ አካላዊ እና ቁሳዊ ዝግጅቶች መሳ ለመሳ እየተደማመጡ የመሥራት ልምዳችንን ማጎለብት ያስፈልገናል❞ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ
ባሕር ዳር: ነሐሴ 07/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ እንዳሉት አሁን የምንገኝበት ሁኔታ የህልውናችንን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚያስፈልገንን መስዋእትነት ሁሉ እየከፈልን ያለንበት ወቅት ነው፡፡
የህልውናችን ቀጣይነት የሚረጋገጠው በህልውናችን ላይ የመጣውን ትህነግና ከትህነግ ጀርባ የሸመቁ የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችንን አራግፈን ስንጨርስ ብቻ እንጂ በአንዲት ጀንበር በሚገኝ የጦር ሜዳ ድል አይደለም ብለዋል።
❝በአንዲት ጀንበር ውስጥ የሚከፈል የጦር ሜዳ መስዋእትነትን ነጥሎ በማውጣት ተሸነፍን ብሎ እምቧከረዩ ማለት የገጠመንን የህልውና አደጋ መጠን በቅጡ አለማወቃችንን እንጂ ነባራዊ ሁኔታውን አያሳይም❞ ነው ያሉት።
ህልውናችንን ለማስጠበቅ የገባንበት ትግል መልከ ብዙ፤ ቅጥልጥል እና ብዙ አይነት ፍላጎት ያላቸው በርካታ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ቡድኖች፣ ተቋማት፣ መንግሥታት ጭምር ተዋናይ የሆኑበት የሞት ሽረት ትግል ነው ያሉት አቶ ግዛቸው ለዚህም የተደራጀ፣ የተቀናጀ እና በትንሽ ድል የማይኩራራ በገጠመው ፈተና የማይዝልና የማይደነግጥ መንፈሰ ጠንካራነትን እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡
❝ተጋድሏችን በእሳት ቃጠሎ ውስጥ ማለፍን በብርቱ ወጀብ ላይ መቅዘፍን ይጠይቃል፡፡ በዚህ ሂደት እየተፈራረቀ የገጠመንን የሀሩር ሙቀት ወይም ከቁር የከፋ ብርድ የስኬታችን ወይም የውድቀታችን መለኪያ ልናደርገው አይገባም❞ ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ❝እኛ ህልውናችንን ለማስጠበቅ የሞት ሽረት ትግል የገጠምን ሕዝቦች እንጂ በጥቂት ሙቀት የምንግል፤ በትንሽ የንፋስ ሽውታ የምንበርድ አይደለንም፡፡ ህልውናችንን ለማስጠበቅ የገባንበት ፍልሚያ መውጣት መውረድን ፤ መውደቅ መነሳትን፤ መራብ መጠማትን፤ ማጥቃትም ሆነ ማፈግፈግን ይጠይቃል፡፡
በትግላችን ውስጥ የሚፈራረቁት ሁነቶች የትግላችንን ሂደት እንጂ ውጤቱን አያረጋግጡም ፡፡ እነዚህን እውነታዎች ታሳቢ በማድረግ ከተለዋዋጩ የትግል መድረክ ጋር ራሳችንን ማላመድ፤ በጠንካራ አደረጃጀት መጋመድ እና እየተደማመጡ መሥራት የግድ ይላል።
በዚህ አግባብ ራሳቸውን ያዘጋጁት የወልድያ፤ የሠቆጣ እና የጋይንት ሕዝብ የትህነግን ወረርሽኝ እንዴት አድርገው እንዳራገፉት ማስታወሱ ጠቃሚ ትምህርት ለማግኘት ይረዳል❞ ነው ያሉት።
ከከተማዋ መሪዎችና ከጸጥታ ኃይሎች ጋር እየተናበበ ለህልውናው የቆመው የወልድያ ከተማ ህዝብ ራሱን ከመከላከል አልፎ ከተማውን እንዳስከበረ ጠላቱን ባለበት ለመቅበር ጫፍ ላይ ደርሷል ያሉት አቶ ግዛቸው በሠቆጣ ዙሪያም አሰፍስፎ ከተማዋን እየተሽከረከረ በተደጋጋሚ የማጥቃት ሙከራ በማድረግ የሠቆጣ ወጣቶችን ጥሶ ለመግባት የሞከሩት የትህነግ ታጣቂዎች ውጥናቸው መሬት የማይነካ ኹኖ በመቅረቱ እጣ ፋንታቸው ማፈግፈግ ብቻ ሁኗል ብለዋል፡፡
ከእልቂቱ ትምህርት መቅሰም ያልቻለውና ወደ ጋይንት ምድር የተመመው የአሸባሪው ትህነግ ቡድን በጋይንት ከተማ መግባት ቢችልም መውጣት ግን አልሆነለትም፤ አሁን ላይም ተቆርጦ የቀረውን የአሸባሪውን ቡድን ለመምታት የወዳጅ ኃይል ብርቱና ውጤታማ ትግል እያደረገ ይገኛል። ይህ የጥፋት ቡድን በከተማዋ በቆየባቸው የሰዓታት እድሜ ውስጥ ያደረጋቸው ሆስፒታል እና የግለሰቦችን ሀብት የመዝረፍ፣ የዱቄት ፋብሪካ የማቃጠል፣ ቤተ ክርስቲያን በከባድ መሳሪያ መምታት እና በንጹሐን ላይ የፈጸማቸው ግድያዎች የአሸባሪውን ቡድን ትክክለኛ ማንነት እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡
የጋይንት ሕዝብ ልክ እንደ ወልድያና የሠቆጣ ሕዝብ ሁሉ በፈጠሩት ቅንጅት እርስ በእርሳቸው እንዲናበቡ እና እንዲደማመጡ ስላስቻላቸው የሽብር ቡድኑ ሊዘርፈው የነበረን ባንክ ተፋልመው ከማስጣላቸው ባሻገር ከወዳጅ ተዋጊ ኃይሎች ጋር ትስስር እየተመሩ ከሞት የተረፈውን የትህነግ መንጋ እያሳደዱ ከጋይንት ወደ ደብረ ዘቢጥ እንዲሸሽ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
❝የአሸናፊነት ድል የሚገኘውና እየተገኘም ያለው ከመደራጀት፤ ከመቀናጀት እና ከመደማመጥ የመነጨ መሆኑን በመገንዘብ ህልውናችንን ለማስቀጠል በፍልሚያ ላይ የምንገኝ ሁሉ የነዚህን ከተሞች አኩሪ ገድል አብነቶቻችን አድርገን ልንከተል ይገባል፡፡ ህልውናችንን ለማስጠበቅ ከሚያስፈልጉን ሥነ ልቦናዊ፣ አካላዊ እና ቁሳዊ ዝግጅቶች መሳ ለመሳ እየተደማመጡ የመሥራት ልምዳችንን ማጎለብት በእጅጉ ያስፈልገናል❞ ብለዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m