
ኢትዮጵያ ካለችበት ውስብስብ ችግር እንድትወጣ የዲያስፖራው ማኅበረሰብ ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ ለሀገሩ እንዲሠራ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማኅበራት ጥምረት ጥሪ አቀረበ፡፡
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 07/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተለያየ ጊዜያት ሀገራቸውን በመደገፍ በጎ አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ ቆይተዋል፤ እያበረከቱም ይገኛል።
ዲያስፖራዎች በተለይ በሕዳሴ ግድብ እያበረከቱ ያለው ሚና የሚደነቅ ነው ያለው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማኅበራት ጥምረት በወቅታዊ የሀገሪቱ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የጥምረቱ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሶስና ወጋየሁ ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ፈተና ለመሻገር ሁላችንም የበኩላችንን እንወጣ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዲያስፖራው በተለያዩ መንገዶች ለሀገሩ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል፡፡
በሀገር ላይ የተደቀነው የሕልውና አደጋ በኢኮኖሚው ላይም እየታየ ነው ያሉት ሰብሳቢዋ ሀገሪቱን ለመበተን የሚፈልጉ የውጭ ረጅም እጆች የገንዘብ ዝውውሩ ከመንግሥት ቋት ውጭ እንዲኾን እየሠሩ እንደኾነም አንስተዋል፡፡ ይህንም ለመከላከል ዲያስፖራው ለወዳጅ ዘመዱ ገንዘብ ሲልክ በሕጋዊ የገንዘብ ማስተላለፊያዎች ሊኾን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ዲያስፖራው በሕልውና ዘመቻው ላይ የገንዘብ እገዛ እያደረገ እንደኾነ የተናገሩት ወይዘሮ ሶስና በገንዘብ አላላኩ ላይ ለማጭበርበር የሚሞክሩ አካላት እንዳሉም አንስተዋል፡፡
በመኾኑም ወቅታዊ የሀገራቸውን ጉዳይ በገንዘብ ለመደገፍ የሚፈልጉ ሁሉ መንግሥት በሚያወጣቸው የታወቁ የገንዘብ መሰብሰቢያ ቋቶች ብቻ ቢያስገቡ ሀገራቸውን ይጠቅማሉ ብለዋል፡፡
ሀገራት የፈረሱትና ከባድ የኢኮኖሚ ስብራት የደረሰባቸው በውስጣቸው በሚፈጠሩ ችግሮች ነው ያለው ጥምረቱ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ለሀገር ሰላም ጥረት ማድረግ እንዳለበት አመላክቷል፡፡
ይሁንና ይህን የውስጥ ችግር በማባባስ፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በማጋጨት እና ኢትዮጵያ ድጋፍ እንዳታገኝ በማድረጉ ላይ የግብጽ ሴራ ያለ በመኾኑ ይህን ሴራ ለማክሸፍ ዲያስፖራው ግንባር ቀደም ሚና ሊወጣ ይገባል ብለዋል የኦሮሚያ ዲያስፖራ ማኅበር የቦርድ ጸሐፊ እና የጥምረቱ አባል አቶ ሙሳ ሸኩር፡፡
በተለይ የሚዲያ ጦርነቱን ለመቋቋም ዲያስፖራዎች የተለያዩ ቋንቋዎችን ተጠቅመው የሀገሪቱን እውነታ በማስረዳትም ኾነ ለጉዳዩ ባላቸው ቅርበት ሀገራዊ ኀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጥሪ ቀርቧል፡፡
ዘጋቢ፡- አንዱአለም መናን-ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m