“ጀግናው ጃናሞራ ለጠገበው ጥይት፣ ለራበው እንጀራ ለማጉረስ ተዘጋጅቷል” በሰሜን ጎንደር ዞን የጃናሞራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ

445
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 07/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎንደር ዞን ጃናሞራ ወረዳ መካነብርሃን ከተማ ነዋሪዎች አሸባሪው ትህነግ የአማራ ሕዝብን ለማጥፋት እና ኢትዮጵያን ለማፍረስ የጀመረውን ወረራ ለማክሸፍ በጠንካራ አደረጃጀት መዘጋጀታቸውን ለአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድን አስረድተዋል።
የመካነብርሃን ከተማ 02 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ለምለም ይበይን መንግሥት ላቀረበው የህልውና ዘመቻ ጥሪ ሁሉን አቀፍ ምላሽ እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አቶ ለምለም እንዳሉት ለህልውና ዘመቻው በዓይነት እና በገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ ነው፤ አካባቢያቸውን በንቃት እየጠበቁ ነው፤ ስልጠና በመውሰድ በቂ ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡
ሌላው ለአሚኮ አስተያየት የሰጡት አቶ እስቲፋኖስ ዓለሙ እንደገለጹት የመንግሥትና የግል መሣሪያ የታጠቀ ግለሰብ ሁሉ አሸባሪውን ለመፋለም ተዘጋጅቷል። እሳቸውም የተሠጠውን ስልጠና በመጠቀም ሽብርተኛውን ትህነግ ለመደምሰስ ዝግጅት ማድረጋቸውን አስረድተዋል።
“አሸባሪው ትህነግ መካነ ብርሃን ከተማን እንዳይደፍራት ታጥቀን እንታገላለን፤ ልዩ ኃይሉን እና የሀገር መከላከያ ሠራዊቱን እንደግፋለን፤ በአንድነታችን ነፃነታችንን እናስከብራለን” ብለዋል አቶ እስቲፋኖስ።
አሸባሪውን ትህነግ በመደምስ ሀገርን ከህልውና አደጋ ለመታደግ በታወጀው የክተት ጥሪ ጀግናው የጃናሞራ ሕዝብ ሁለንተናዊ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን የወረዳ አስተዳደሩ ነው የገለጸው፡፡ ሽብርተኛው ትህነግ በተደጋጋሚ የቀረበለትን የሰላም አማራጭ ባለመቀበል ዳግም ወረራ በመፈጸም የንጹሃንን ሕይወት እየቀጠፈ እና ንብረት እየዘረፈ የተረፈውን እያወደመ ይገኛል፡፡
ይህን እኩይ ተግባሩን ለመግታት እና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር የጃናሞራ ሕዝብ አንድ ሆኖ ግንባር ድረስ በመዝመት፣ ድጋፍ በማሰባሰብ፣ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ እየተሳተፈ መሆኑን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ጌታቸው አማረ ተናግረዋል፡፡
ሽብርተኛው ትህነግ ከሚጠቀምባቸው የጦር ስልቶች አንዱ ሰርጎ ገቦችን ወደ ሕዝብ በማስገባት ጥቃት ማድረስ፣ ማሸበር እና የሃሰት ወሬ መንዛት መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው አንስተዋል፡፡
ይህን ዘመን ያለፈበት ስልቱን ለማክሸፍ ሕብረተሰቡ ተቀናጅቶ ቁልፍ በሮች እየጠበቀ እና ጥርጣሬ ሲኖር እርምጃ እየወሰደ ነው ብለዋል፡፡ ከሰሞኑ የአዲአርቃይ ወረዳ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ የነበረው እና ለሽብርተኛው ትህነግ ሲላላክ የነበረ ባንዳ ሕዝቡን ለጠላት አሳልፎ ከሰጠ በኋላ ሾልኮ ለማምለጥ ሲሞክር በሕዝቡ ተሳትፎ ተይዞ ለሕግ ተላልፎ መሰጠቱ የሕዝቡን ንቃት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የሽብርተኛው ትህነግ ቡድን ወደ ጀግናው ጃናሞራ ሕዝብ ከመጣ መውጫ እንዳይኖረው ተደርጎ ይደመሰሳል ብለዋል አቶ ጌታቸው፡፡ “ጀግናው ጃናሞራ ለጠገበው ጥይት፣ ለራበው እንጀራ ለማጉርስ ተዘጋጅቷል” ነው ያሉት፡፡
የወረዳው ሕዝብ ሁሉም ለራሱ ሠራዊት እንዲሆን ግንዛቤ ተፈጥሯል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው በርካታ ወታደራዊ ስልጠና የወሰደ የሰው ኃይል ግምባር ተሰልፎ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከልዩ ኃይሉ ጋር ጁንታውን እተፋለመ እንደሆነም ነግረውናል፡፡
የወረዳው የሥራ ኀላፊዎች ጭምር ግንባር መዝመታቸውን እና የህልውና ዘመቻው ላይ በቀጥታ እየተሳተፉ እንደሚገኙ አቶ ጌታቸው አስታውቀዋል፡፡
የጃናሞራ ሕዝብ ሽብርተኛው እና ወራሪው ትህነግ በሚነዛው የሃሰት ወሬ ላይደናገር ቀድሞ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡ የወረዳው ሕዝብ የህልውና ዘመቻውን በዓይነትም በገንዘብም እየደገፈ መሆኑን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው በዚህም በወረዳ ደረጃ 24 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማሰባሰብ መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፦ አዳሙ ሽባባው-ከጃናሞራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleሕዝቡ አሸባሪው ትህነግን እሾህ ሆኖ እየወጋው እንደሚገኝ የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀለምወርቅ ምህረቴ ገለጹ፡፡
Next articleበአማራ፣ በኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ለሕልውና ዘመቻው 8 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረጉ፡፡