
ባሕር ዳር፡ መስከረም 15/2012 ዓ/ም (አብመድ) የኢጋድ አባል ሀገራት ሚኒስትሮች በጋራ መክረዋል፡፡
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ገዱ አንዳርጋቸው በኒው ዮርክ እየተካሄደ ከሚገኘው 74ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን በኢጋድ የሚንስትሮች ምክር ቤት ሊቀመንበርነታቸው የአባል ሃገራት ሚንስትሮችን አወያይተዋል፡፡
የአባል ሃገራት ሚንስትሮች የኢጋድ የሚንስትሮች ምክር ቤት አባል ሆነው የተቀላቀሉት የደቡብ ሱዳን እና የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮችም በውይይቱ ተሳትፈዋል፡፡
የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አውት ዴንግ አኩይ በሃገራቸው የሠላም ሂደቱ የደረሰበትን ዝርዝር ሂደት አስረድተው አባል ሃገራት ድጋፋቸውን እንዲሠጡ ጠይቀዋል። አዲሱን የሱዳን ካቢኔ የተቀላቀሉት የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አስማ አብደላ በበኩላቸው የአካባቢው ሃገራትና ኢጋድ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንዲሠጣቸው ጠይቀዋል።
የአባል ሃገራት ሚንስትሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ለአፍሪካ ችግሮች በሚለው መርህ መሠረት ሁለንተናዊ ድጋፋቸውን ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
በዝግጅቱ የኢትዮጵያ፣ የጅቡቲ፣ የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች እንዲሁም የኬንያና የዩጋንዳ ሚንስትር ዴኤታዎች ተገኝተዋል።
ምንጭ፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር