
ሀገር ሊያፈርስ የተነሳውን አሸባሪው የትህነግ ቡድን ለመደምሰስ ሁሉም በጋራ እንዲነሳ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ አቀረቡ፡፡
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 06/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በወቅታዊ ክልላዊና ሀገራዊ ሁኔታ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ መግለጫውን የሰጡት የአማራ ብልጽግና ፓርቲ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኀይል ንቅናቄ (አዴኀን) ናቸው።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብርሃም አለኸኝ እንደተናገሩት ጠላት ወረራ እየፈጸመ ይገኛል። ይህን ወረራ በአንድነት ሆነን ልንመክተው ይገባል ብለዋል።
አሸባሪው ቡድን በሰሜን ወሎና በደቡብ ጎንደር ወረራ በመፈጸም ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል ያሉት አቶ አብርሃም ይህንን ወረራ ለመቀልበስም በየደረጃው ያሉ የኢትዮጵያ ጀግኖች ከፍተኛ ተጋድሎ እየፈጸሙ እንደሚገኙ ገልጸዋል። አቶ አብርሃም ይህ ተጋድሎ በአጭር ጊዜ እንዲቋጭ በአንድነት ልንረባረብ ይገባል ብለዋል።
የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊዎችና አመራር በአንድነት ሊዘምቱ ይገባል ነው ያሉት። ለጠላት ክፍተት ሳንፈጥር በአንድ አስተሳሰብ መታገል እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
“ኅብረተሰቡ ከሐሰት መረጃ መጠንቀቅ አለበት። እዚህ ደረሱ፣ ቶሎ ልቀቁ የሚል ከፍተኛ ፕሮፖጋንዳ በኅብረተሰቡ ውስጥ እየተሰራጨ ስለሚገኝ መረጋጋትና አለመረበሽ ያስፈልጋል” ብለዋል።
ትግሉ የመላው ኢትዮጵያ ህልውና መሆኑ ታውቆ መላው የሀገሪቱ ሕዝብ ሊዘምትና ዘብ ሊቆም እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ የተቃጣብንን የህልውና አደጋ በጋራ መመከት አለብን ያሉት አቶ አብርሃም ትግሉን በአጭር ጊዜ ለመቋጨት መላው የአማራም ኾነ የኢትዮጵያ የታጠቁ ኀይሎችና ሕዝቦች ወደትግሉ እንዲቀላቀሉ አቶ አብርሃም ጥሪ አስተላልፈዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የውጪ ጉዳዮችና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ቴዎድሮስ ኃይለማርያም (ዶክተር) አሸባሪው ቡድን በአማራ ክልልም ሆነ በኢትዮጵያ ሕዝቦች የህልውና አደጋ ስለፈጠረ ሁሉም የሀገሪቱ ሕዝቦች በአንድነት ሊደመስሱት ይገባል ብለዋል። መላው የአብን ደጋፊዎችና አባላት እንደ ሕዝብ አንድ ሆነው ቡድኑን በከፍተኛ ወኔ እንዲፋለሙም ጥሪ አድርገዋል።
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኀይል ንቅናቄ ሊቀመንበር ተስፋሁን ዓለምነህ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን አፈራርሳለሁ፣ በአማራ ሕዝብ ላይ ሒሳብ አወራርዳለሁ ብሎ የተነሳውን እኩይ ቡድን የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልል ልዩ ኀይሎችና ሕዝባዊ ሚሊሻዎች እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር እየተፋለመውና በተባበረ ክንድ እየደቆሰው ይገኛል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥትም ይህን ከታሪክም ከነባራዊ ሁኔታም በፍጹም ሊማርና ሊጸጸት የማይችል አረመኔ ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስና በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን ለመመለስ ሲል ነሐሴ 4/2013 ዓ.ም የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔውን ማንሳቱ እጅግ ወቅታዊና ተገቢ ርምጃ መሆኑን እናምናለን ነው ያሉት፡፡
መንግሥት “ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ፣ የትም፣ መቼም፣ በምንም” በሚል መሪ ሐሳብ ያቀረበውን ሀገራዊ ጥሪና የአማራ ክልልን የክተት ጥሪ በመደገፍ አስፈላጊውን ሁሉ መስዋእትነት ለመክፈል ፈጣን ምላሽ ለሰጣችሁ መላው ኢትዮጵያውያን፣ የአማራ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ምሁራን፣ ባለሀብቶችና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ልባዊ አድናቆትና ምስጋና እንደሚያቀርቡም ገልጸዋል፡፡
“ለአማራ ሕዝብ ፍትሕና ነፃነት የምንታገል የፖለቲካ ፓርቲዎች ትህነግ እንደ ሕዝብ ያወጀብንን ሒሣብ የማወራረድ ዘመቻ የፖለቲካ፣ የእምነት፣ የእድሜ ፣ የጾታና ማናቸውም ልዩነት ሳይገድበን እንደ ሕዝብ በአንድነት ቆመን እንድንመክት ለመላው አማራ ሕዝብና ኢትዮጵያዊያን ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል ፓርቲዎቹ በጋራ መግለጫቸው ።
የፓርቲዎቹ አባላትና ደጋፊዎች የተቃጣውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ በሚደረገው ፍትሐዊ ጦርነት የተጠየቀውን ሁሉ መስዋእትነት ለመክፈል በፍጹም አንድነትና ቁርጠኝነት በግንባር ቀደምትነት እንድትሰለፉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ