መሸነፉ የማይቀርን ቡድን እድሜ ማራዘም እንደማይገባ የሐይቅ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከበደ ካሳ ተናገሩ።

213
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 06/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከተማ አስተዳደሩ ከደጀንነት ባለፈ ወደ ግንባር በመግባት የትህነግን አሸባሪ ቡድን ለመደምሰስ እየሠራ መኾኑን አስታውቀዋል።
የሐይቅ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከበደ ካሳ ትህነግ በሕዝብ ላይ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት ወጣቱን አደራጅተው እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። በከተማዋ ከ20 በላይ ኬላዎችን በማዘጋጀት እየተሠራ ነውም ብለዋል። ወደ ከተማዋ የሚገባ የትህነግ ርዝራዥ ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ በተጠንቀቅ ላይ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
የከተማዋ ወጣቶች በከተማዋ ከሚሠሩት የጸጥታ ሥራ ባለፈ ወደ ግንባር እየሄዱ መኾናቸውንም ተናግረዋል። የከተማዋ ማኅበረሰብ በአደረጃጃት ውስጥ ያለ ነውም ብለዋል። ሰርጎ ገብ ይገባባቸዋል ተብሎ የሚታሰቡ ቦታዎችን በጥንቃቄ እየጠበቁ መኾኑንም አስታውቀዋል። ጠላትን ባለበት ለማክሰም ከደጀንነት ባለፈ ወደ ግንባር በመግባት የትህነግን ቡድን ለመደምሰስ እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። ለሠራዊቱ ስንቅና ትጥቅ እያቀረቡ እንደኾነም ነው ያስረዱት።
ትህነግ ሐሰተኛ ወሬዎችን የመንዛት ሥራው አብሮት ያደገ ነው ያሉት ከንቲባው የከተማዋ ማኅበረሰብ በሐሰት ወሬ እንዳይደናገጥና የበሬ ወለደ መረጃን እንዳይቀበል የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። ሕዝቡ ለጠላት እጅ እንዳይሰጥ መግባባት መፈጠሩንም ተናግረዋል። የከተማ አስተዳደሩ መሪዎች ከኅበረተሰቡ ጋር በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
ትህነግ እየተደመሰሰም የተለያዩ ከተማዎችን ይዤያለሁ እያለ እንደሚያስወራም ገልጸዋል። አብዛኛዎቹን ከተሞች በአሉባልታ የመፍታት ስትራቴጂ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መኾኑን ሕዝቡ ሊረዳ እንደሚገባ የተናገሩት ከንቲባው ለዚያ የማይበገር ማኅበረሰብ ሊኖር ይገባል ብለዋል።
በከተማዋ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው የመጡ ዜጎችን የመደገፍ ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ወጣቶች ከወገን ጦር ጋር በመቀናጀት ጠላትን ለመደምሰስ ከፍተኛ ተነሳሽነት እያሳዩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። “ከእኔ ጀምሮ ጠላትን ለመደምሰስ ወደኋላ የሚል ሠው የለም” ነው ያሉት።
ጠላትን ባለበት ማክሰም ካልተቻለ መሀሉ ዳር ስለሚኾን ጠላትን ባለበት ለመደምሰስ ሁሉም እንዲነሳ ጥሪ አቅርበዋል። ዳሩን ማጠናከር ይገባልም ብለዋል። ጠላት በጅምላ እንደሚመጣ የተናገሩት ከንቲባው ”የእኛ ሕዝብም በሕብረት ተነስቶ ሊያጠፋው ይገባል“ ብለዋል። ትህነግ በአሉባልታ እንጂ የተለየ አቅም ያለው ኀይል እንዳልኾነም ነው ያብራሩት። ባለበት ማክሰም ካልተቻለ ኢትዮጵያን እንደሚበትናት ነው የተናገሩት።
በዘረፋ እና በውንብድና ንጹሐንን የሚጎዳ ቡድን በመኾኑ ባለበት መደምሰስ ይኖርበታል ብለዋል። ኅብረተሰቡም ከጸጥታ አካሉ ጋር በመኾን ጠላትን በአጭር ጊዜ ማክሰም ይገባል ነው ያሉት። አንድ በመኾን የጠላትን እድሜ አሳጥሮ ወደ ሌሎች ሥራዎች መግባት እንደሚገባም ገልጸዋል። መሸነፉ የማይቀርን አሸባሪ ቡድን እድሜ ማራዘም እንደማይገባም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ወቅቱ ሀገር የምናድንበት በመሆኑ ማንኛውንም መስዋእትነት መክፈል ጊዜው የሚጠይቅ ነው” የኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባላት
Next articleጀግናው የደቡብ ዕዝ የ21ኛ ጉና ክፍለ ጦር አሸባሪውን የትህነግ ቡድን በጉባ ላፍቶ ወረዳና አካባቢው በከፍተኛ የጀግንነት ስሜት በመደምሰስ ላይ እንደሚገኝ መከላከያ ሠራዊት ገለጸ ።