የአሸባሪው ትህነግ ግፍ በተፈናቃይ ወገኖች አንደበት…

242
የአሸባሪው ትህነግ ግፍ በተፈናቃይ ወገኖች አንደበት…
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 05/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ክፉ ሰው ክፉ ዘመን ያመጣል፣ መልካም ሰው መልካም ዘመን ይሠጣል። አጊጦ መኖር፣ አርጅቶ መጦር፣ በክብር መቀበር ሲዳላና ሰላም ሲሆን ነው። ዓለማት በእኩል ማዬት አቁመዋል፣ ሰብዓዊነትን ረስተዋል፣ ማመዛዘን ትተዋል፣ ሰው በጥቅም ሸጠዋል። የአንዞ እንባ የሚያለቅሰውን እንባውን ሊያብሱለት ደፋ ቀና ይላሉ። ከአንጀቱ የሚንሰፈሰፈውን ደግሞ ጀሮቸው እንዳልሰማ፣ ዓይናቸው እንዳላዬ ዝም ይላሉ። በንጹሐን እንባ ያተርፋሉ፣ በእንባቸው ይሳለቃሉ፣ በቁስላቸው እንጬት ይሰዳሉ።
የአማራ እናቶችን እንባ ለዓመታት ሲፈስስ አይዟችሁ ያላቸው፣ ጀሮ የሰጣቸው፣ ፍትሕ የጠየቀላቸው የለም። የአማራ እናቶችን ለዓመታት ያስለቀሱት፣ የገፉት በትግል ገለል ሲሉ ድምፅ ያልነበረው አንደበት ተናገረ፣ ፍትሕ ያልጠየቀው ችሎት ተከራከረ። የአማራ በደሉ ምን ላይ ይሆን?
በሺዎች የሚቆጠሩት ሲፈናቀሉ፣ ወገን ሳይቀብራቸው በየጥሻው ሲቀሩ የዓለም ጀሮዎች ባልሰማ ዝም አሉ። ገዳዮቹ ድረሱልን ሲሉ ደግሞ አለን አሉ። አሸባሪው ትህነግ በአማራ ላይ የሚያደርሰው ግፍ ዛሬም አልደረቀም።
ከሰሞኑ በወሎ ባደረሰው ጥቃት በሺዎች የሚቆጠሩ አማራዎች ተፈናቅለዋል። ቤት ንብረታቸውን አጥተዋል። ተዘርፈዋል። ታዲያ ይህ ሁሉ ሲሆን ለሰብዓዊነት መከበር እንቅልፍ የለንም የሚሉት ሀገራትና ተቋማት ድምፃቸው አልተሰማም። ግፈኛውን አላወገዙም። ዳሩ ተስፋቸው በእነርሱ ላይ አይደለችም።
እማሆይ አረጋሽ መንገሻ ይባላሉ። የተወለዱት፣ እልል ተብሎ ተድረው ያገቡት፣ ወግ ማዕረግ ያዩት፣ አቅፈው የሳሙት፣ አሽተው የቃሙት፣ በጎብዬ ነው። በዚህች ቀያቸው ዓለማቸውን አይተው፣ ለፈጣሪያቸው ተገዝተው መንኩሰዋልም። እርሳቸው በባድማቸው ልጆቻቸውን እየመረቁ፣ ፈጣሪያቸውን እየለመኑ ነበር የሚኖሩት። እማሆይ እድሜያቸው ምን ያክል እንደሆነ መቆጠር ባይችሉም እድሜያቸው እንደገፋ ነግረውኛል።
በዘመነ ኃይለ ሥላሴ ልጆች ወልደው እንደነበር ነው ያስታወሱኝ። እኒህ አድባር የሆኑ እናት በክፉ እጆች ተገፍተው፣ ከባድማቸው ወጥተው፣ ከቀያቸው ርቀው በደሴ ከተማ በተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ ነበር ያገኘኋቸው። በክብር ተቀምጠው ለፈጣሪያቸው እጅ እየነሱ፣ ምህላ እያደረሱ፣ ወደ ፈጣሪያቸው ቤት እየገሰገሱ ለሀገርና ለወገን መፀለይ ሲገባቸው በግፈኞች ተፈናቅለው፣ የእለት ጉርስ፣ ለገላቸው ልብስ እጃቸውን ወደ ሰው ሲዘረጉ ሲታዩ ያስዛናሉ።
በአሸባሪው ቡድን ወረራ ተገፍተው ቀያቸውን ትተው በደከመ ጉልበታቸው፣ ዓመታትን ካሰለፉባት ጎጇቸው ወጥተው ለሥደት ተዳረጉ። አቀማመጣቸው፣ ትካዜያቸው ያሳዝናል። በእሳቸው ፊት የሁሉም እናቶች ፊት ይታያል። ቀርቤ ጠይኳቸው “እንዳሻው ከቤቴ ልቀመጥ ብዬ ነበር፣ ከዚህ ወዲያ ምን እንዳልሆንኩ ነው። ለየትኛው እድሜዬ ብልም ልጆቼ ጥለንሽ አንሄድም አሉኝ። የእለት ጨርቅ እንኳን ሳናንጠለጥል፣ ዱቄት ሳንይዝ፣ ዝም ብለን ወጣን ያነሳነው ነገር የለም” አሉኝ። ልባቸው በሐዘን እንደተሰበረ የንግግራቸው ቅላፄ ያስታውቃል።
እኒህ አሳዛኝ እናት በክብር በሚጦሩበት ጊዜ መፈናቀል ሲገጥማቸው ልባቸው አዝናለች፣ ዓይናቸው እንባን ታፈስሳለች። በሌለ ጉልበታቸው እየወደቁ እየተነሱ ለሥደት ተዳረጉ። በዘመናቸው እንዲህ አይነት ችግር ገጥሟቸው እንደማያውቅም ነግረውኛል። “እነርሱን አስገድላለሁ ብዬ ፈርቼ እንጂ ለእኔውማ ምን ያጓጓኝ ነበር፣ እዛው እቀመጥ ነበር፣ ቤቱን ዘግታችሁልኝ ሂዱም ብዬ ነበር፣ አልሄድም ልሙት አልኩ፣ ልጆቼ ግን እንቢ አሉኝ” በማለት ያችን ቀን አስታውሰዋል። እሳቸው ሞትን ንቀውት፣ በተዘጋ ቤት ውስጥ ሊቀሩ ወስነውም ነበር።
በእርጅና ዘመናቸው የገጠማቸው ክፉ ጊዜ ከሞትም በላይ እንደሆነባቸው ነው የነገሩኝ። እማሆይ ወደ ቀያቸው ሄደው በክብር መጦርና መኖርን ይሻሉ። ቤታቸው ናፍቃቸዋለች፣ ድንገት እንደወጡ ያን ያክል ቀን እቆያለሁ ብለው አስበው እንዳልነበርም ነግረውኛል። ሀገር ሰላም ሆና፣ ግፈኞቹ ልካቸውን አይተው በቀያቸው በሰላም መኖርን ናፍቀዋል።
በዚያው መጠለያ ውስጥ የ76 ዓመት እድሜ አዛውንት የሆኑ አንድ አባትም አገኘሁ። ሲሳይ ታረቀኝ ይባላሉ። ነዋሪነታቸው በጎብዬ ነበር። በግብርና ቤታቸውን ይመራሉ። እኒህ አባት ልጆች ወልደው፣ ዓለማቸውን አይተው በመጦሪያቸው ጊዜ በአሸባሪው ትህነግ ግፍ ለስደት ተዳረጉ። “ሁለት በሬዎች ነበሩኝ ለወንዶቹ ልጆቼ እነርሱን ጥዬ፣ የልጆቼን ሚስቶችና የልጅ ልጆቼን ይዤ መጣሁ። ትልቁ ልጄ አንድ ቀን ደውሎልኝ፣ እንዳልመጣ በሬዎቹን አርደው ይበሏቸዋል ብዬ ፈራሁ ፣ ላምና በሬ ሲያገኙ አርደው ይበላሉ አለኝ። በሉ አደራችሁን ደፋጣ ቦታ እየመረጣችሁ ተቀመጡ፣ ከወንድምህ ጋር አትለያዩ አልኩት፣ አሁን ግን እንዴት እንደሆኑ አላውቅም። ቤታችን ዝም ብሎ ቀርቷል” ነው ያሉኝ። ልጆቻቸውን በበረሃ ጥለው፣ ከፊሎችን ይዘው፣ ከሞቀ ቤታቸው በክረምት ወጥተው የሰው እጅ ማዬት፣ አገላብጦ ባረሰ፣ ሳይገመግም ነጭና ጥቁር ባፈሰ እጃቸው፣ ለእለት ጉርስ ደጅ መጥናታቸው ልብ ሰባሪ ነው።
“አነሰም አደገም ቤት ቤት ነው፣ አሁን ግን የሰው እጅ ከማዬት ውጭ ምን አለ። ልጆቼ ያለችውን እየከፈሉ ይሰጡኛል እርሷን እየጎረስኩ ተቀመጥኩ። ወደዚያው ጥቅርሻችን (ቤታችን ማለታቸው ነው) ብንገባ ነበር ጥሩ” ብለውኛል።
አርሰው ከማጉረስ፣ የታረዘን ከማልበስ ውጭ ቂምና በደል የሌለባቸው ክፋት ያልተገኘባቸው አባት ዘርተው ማሳቸውን በሚሸፍኑበት ወቅት በጨካኞች ለእንግልት ተዳረጉ። “ከልጆቼ ጋር መገናኘት ነው ምኞቴ። ከዚህ ከመጣሁ ሁለት ወንድሞቼን ተረድቻለሁ። በከባድ መሳሪያ እንደገደሏቸው ሰምቻለሁ” ነው ያሉት።
አሸባሪው ትህነግ ከሀብት ንብረታቸው፣ ከሞቀ ቤታቸው ብቻ አይደለም ያስለቀቃቸው። ወንድሞቻቸውንም ነጥቋቸዋል። እውን ከዚህ በላይ በደል አለን? መልሱን ለፍትሕ አምላክ ትቸዋለሁ።
አንድ እግራቸውን ካጡ 30 ዓመታት እንደሆናችሁ የነገሩኝ ሌላው በመጠለያ ውስጥ ያገኘኋቸው ደግሞ መንገሻ አባተ ናቸው። ነዋሪነታቸው በቆቦ ከተማ ነበር። አሸባሪው ትህነግ አካል ጉዳተኛ፣ ታላቅ ታናሽ፣ ሴት ወንድ ሳይል በግፍ ስለሚገድል ጥይት እንዳይበላኝ ብዬ ነው የመጣሁት ብለውኛል። በደካማ አቅማቸው በቤታቸው መኖር ሲገባቸው በዝናብ ወቅት መፈናቀል ግድ ሆኖባቸዋል።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከዚህ አጥፊ ቡድን ከሞትና ከመፈናቀል ለመዳን በጋራ ዛሬ ነገ ሳይል ቆርጦ በመነሳት ሊታገል እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
“ሕዝቡ ወያኔን መዋጋት አለበት። ተዋግቶ ሀገር ሰላም ማድረግ ነው ሌላ መፍትሔ የለውም። ዝም ካሏቸው አያርፉም” ነው ያሉት ተፈናቃዮቹ።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኀላፊና የአደጋ መከላከል ግብረ ኀይል አባል ሰይድ እሸቱ በተለያየ አደረጃጀት ኮሚቴ በማዋቀር በደሴ ከተማ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮችን ለመርዳት እየተሠራ ነው ብለዋል። ቁጥራቸውን በውል ማወቅ እንዳልተቻለ የተናገሩት አቶ ሰይድ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች በከተማዋ ተጠልለው መኖራቸውን ነው የተናገሩት።
የደሴ ከተማ ሕዝብ ለተፈናቃዮች ያደረገው አስተዋጽኦ የሚመሰገን መሆኑንም ገልጸዋል። የመኖሪያ ቤታቸውን ለተፈናቃዮች መጠለያ እየሰጡ ያሉ የከተማዋ ነዋሪዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል። ከተለያዩ አካላት ጋር ቅንጅት በመፍጠር ተፈናቃይ ወገኖችን የመደገፉ ሥራ እየተከናወነ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል። ደራሽ ምግብ እየቀረበ መሆኑንም ጠቁመዋል። ተፈናቃዮቹ አፋጣኝ መፍትሔ ካልተሰጣቸው በከተማ አስተዳደሩ ብቻ መታደግ እንደማይቻልም አስታውቀዋል።
በከተማዋ ከሰው ቁጥር መብዛት ጋር ተያይዞ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል። ወገኖቻችን ናቸው የመጡት ልንረዳቸው ይገባል በሚል እየተሠራ ነውም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article‹‹የአውደ ውጊያ ውሎ ድል መክተቢያ የወርቅ ብዕራችን እንዳይደርቅ እንፋለማለን›› ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ
Next article“እስከ ህይዎት መስዋእትነት ለመክፈል ተዘጋጅተናል” የምዕራብ ጎጃም ዞን የፖሊስ አባላት