
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያስተላለፈውን መልዕክትና ሀገራዊ ጥሪ አንዳንድ ዓለምአቀፍ የሚዲያ አካላት ሐቅ እንዳዛቡ የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ አስታወቀ።
ባሕር ዳር: ነሐሴ 05/2013 ዓ.ም (ኢሚኮ) ትናንት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያስተላለፈውን መልዕክትና ሀገራዊ ጥሪ ውሳኔ መሰረት በማድረግ አንዳንድ ዓለምአቀፍ የሚዲያ አካላት ሐቅ ማዛባታቸውን እንደቀጠሉ የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ አስታውቋል።
አሸባሪው ሕወሓት እያደረሰ ያለውን ጥፋትና ሰቆቃ ለማስቆም ለ100 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግልጽ ተደርጎ እንደተላለፈ እየታወቀ አንዳንድ የሚዲያ ተቋማት ግን መልእክቱን ያስተላለፉበት መንገድ የተዛባና ኾነ ተብሎ ባልተገባ መንገድ ተተርጉሞ የቀረበ መሆኑን ጠቁሟል።
አሸባሪው ሕወሓት በአጎራባች የአፋርና የአማራ ክልል ንጹሐን ላይ ጭፍጨፋ ሲፈጽም አይተው እንዳላዩና ሰምተው እንዳልሰሙ ያለፉት የሚዲያ ተቋማቱ የህልውና ትግል ጥሪው ላይ የተዛባ ምስል ሊፈጥሩ መሞከራቸውን ገልጿል።
“ተቋማቱ ያወጧቸው ርእሰ ዜናዎች አሸባሪው ሕወሓት ያደረሳቸውን ጉዳቶች ሆነ ብለው ዘንግተዋቸዋል” ብሏል።
ትግራይ የሉዓላዊት ኢትዮጵያ አንዷ ክፍል መሆኗ ግልጽ ኾኖ እያለ የትግራይ ኀይሎች የሚል ስያሜ በመስጠት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከመዳፈራቸውም በላይ ሁኔታውን በሁለት ሀገራት መካከል የሚደረግ ጦርነት የማስመሰል ተደጋጋሚ ሙከራና ኢትዮጵያውያንን የመከፋፈል ጥረቶች እንደነበሩ አስገንዝቧል።
ዜናዎቹ አሸባሪው ሕወሓት በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ላይ ሲያደርስ የነበረውን ሰቆቃ ባለማንሳት የኢትዮጵያ መንግሥትን በአጠቃላይና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመኮነን ላይ ማተኮራቸውን ገልጿል።
በርካቶቹ ዘገባዎችም ተቆርጠው የተቀጠሉና እርስ በርስ የተቀባበሏቸው መሆናቸውን አሳውቋል።
ተቋማቱ የአሸባሪው ድርጅት አመራሮች መብረቃዊ ጥቃት ያሉትን እርምጃ አወድሰው መከላከያ ሠራዊት ላይ ጉዳት በማድረሳቸው የሕግ ማስከበር ዘመቻው እንደተጀመረ ማስታወስ አለመፈለጋቸውን የመረጃ ማጣሪያውን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።
ኤኤፍፒ፣ ኤፒ እና ዋሽንግተን ፖስት በሕገመንግሥታዊ መንገድ ሽብርተኛ ለተባለው ድርጅት ከሙያዊ ሥነምግባር ባፈነገጠ ሁኔታ ጥብቅና የቆሙበት ምክንያት ጥያቄ መፍጠሩን አንስቷል።
ከ100 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ያላት ኢትዮጵያ ያወጣቻቸውን ሕግጋትና ሉዓላዊነቷን ባለማክበር የሚደረጉት ሐቆችን የማዛባት ተግባራት ላለፉት ዘጠኝ ወራት ተጠናክረው መቀጠላቸውንም አስታውሷል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ