“ተመራቂ ሁለገብ ኃይሎች የሽብር ቡድኑን በአጭር ጊዜ በመደምሰስ ደማቅ ታሪክ እንደምትጽፉ እምነቴ ነው” የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው

182
“ተመራቂ ሁለገብ ኃይሎች የሽብር ቡድኑን በአጭር ጊዜ በመደምሰስ ደማቅ ታሪክ እንደምትጽፉ እምነቴ ነው” የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 05/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ ሀገር ለማፍረስ ያወጀውን ጦርነት በመመከት ኢትዮጵያን ለማዳን ወጣቶች በየአካባቢው ሀገር የማዳን የክተት ጥሪውን በመቀበል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን፣ ልዩ ኃይሉን እና ሚሊሻ እየተቀላቀሉ ይገኛል።
በደብረ ማርቆስ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋም ለህልውና ዘመቻው ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱ ሁለገብ ኃይል አባላት ተመርቀዋል።
የደብረ ማርቆስ ወታደራዊ ስልጠና ማዕከል አስተባባሪ ኮማንደር አበበ ፀጋ ተመራቂዎቹ ሽብርተኛው ትህነግን በማስወገድ ኢትዮጵያን ለማዳን በሚደረገው ትግል የአባቶቻቸውን ታሪክ እንዲጽፉ አሳስበዋል።
በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው አሸባሪው የትህነግ ቡድን እንደ ጥገት ላም ሲያልባት የኖራትን ሀገር ለማፍረስ ከጠላቶቿ ጋር በመተባበር እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም በአማራ ሕዝብ ላይ የፈጸመውን ወረራ ጠቅሰዋል።
ከአማራ ሕዝብ በተጨማሪ በኢትዮጵያዊነቱ በማይደራደረው የአፋር ሕዝብ ላይ ግፍ እየፈፀመ ይገኛል ብለዋል።
አቶ ላቀ ኢትዮጵያ ማንም የሰፈር ጎረምሳ የማያፈርሳት እና ጠላት ሲነሳባት ጀግኖች ልጆቿ በአንድነት የሚነሱ መሆናቸውን ታሪክ ምስክር ነው ብለዋል። ዛሬም ኢትዮጵያውያን ጦርነት ያወጀውን ጥቁር ፋሸስት በመደምሰስ የአባቶቻቸውን ታሪክ ለመድገም ‘ሆ‘ ብለው ተነስተዋልም ነው ያሉት ሚኒስትሩ፡፡
የዛሬ ተመራቂዎች ይህን የሽብር ቡድን በአጭር ጊዜ በመደምሰስ በሽብር ቡድኑ መቃብር ላይ ደማቅ ታሪክ እንደሚጽፉ ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል።
የህልውና ዘመቻው ተመራቂዎችም ኢትዮጵያን ለማተራመስ የተነሳውን ሽብርተኛውን ትህነግ በመደምሰስ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፡- ዘላለም አስፋው-ከደብረ ማርቆስ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአፋር ክልል በፈንቲ ረሱ በጋሊኮማ ጊዜያዊ መጠለያ ተጠልለው በነበሩ ሕጻናት፣ ሴቶችና አርብቶ አደሮች ላይ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በፈፀመው አሰቃቂ ጭፍጨፋ የተሰማውን ሐዘን ገለጸ፡፡
Next articleየጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያስተላለፈውን መልዕክትና ሀገራዊ ጥሪ አንዳንድ ዓለምአቀፍ የሚዲያ አካላት ሐቅ እንዳዛቡ የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ አስታወቀ።