“ፊፊ” የመስቀል በዓል ድምቀት!

258

ባሕር ዳር፡ መስከረም 15/2012 ዓ/ም (አብመድ) ፊፊ በጃዊ ወረዳና አካባቢው የመስቀል በዓል መምጣቱን ተከትሎ የሚከወን ባሕላዊ ጨዋታ ነው፡፡ በጥንት ጊዜ ጠላትን ለመከላከል የሚጠቀሙበት የመግባቢያ መሣሪያም ነው ፊፊ፡፡

ፊፊ በአዊኛ ቋንቋ “ውጣ እንውጣ” እንደ ማለት ነው፡፡ ጠላትን ለማጥቃት ውጣ እንውጣ ለማለት የተጠቀሙበት ቃል መሆኑን ደከጃዊ ወረዳ አብመድ ያነጋገራቸው አዛውንት ንጋቱ ዋሴ ገልጸዋል፡፡ “ፊፊ የባሕላዊ ጨዋታ ብቻም ሳይሆን የአዊዎች የጀግንነት ማሳያም ነው” ብለዋል፡፡

“በወቅቱ የነበሩ ግብር አስገባሪዎች በአዊዎች ላይ አላስፈላጊ ቀረጥ እና ዕዳ ከመጫን ባለፈ ልጃገረዶችን ጭምር ሕዝቡ እንዲገብር ፍላጎት ስለነበራው ይህንን በመቃወም የተጀመረ ባሕላዊ ጨዋታ ነው፤ ጨዋታው የአዊዎችን ጀግንነት እና አልሸነፍ ባይነትን ስለሚያሳይ ከትውልድ ወደ ትውልድ መሸጋገር ስላለበት በየዓመቱ እንጫወተዋለን›› ብለዋል ታሪክ ነጋሪው አዛውንት፡፡

አዊዎች በአንድ ወቅት ጠላትን ለመከላከል የተጠቀሙበት ፊፊ በዚህ ወቅት ባሕላዊ የትንፋሽ መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ነው፡፡ ፊፊ አምስት ዓይነት ዜማዎች እና ሰባት የተለያዩ ድምፆች ያላቸውን መሳሪያዎች ይጠቀማል፡፡ ከቀርቀሃ ተክል የሚዘጋጅ ሲሆን ሰባት ወንዶች በጋራ ይጫወቱታል። ሴቶቹ ደግሞ ዙሪያውን እየዞሩ በእልልታ ያጅባሉ፡፡ ይህ ደግሞ ዓመቱ የብርሃን፣ የጥጋብ፣ የሠላም እና የፍቅር እንዲሆንላቸው የሚመኙበት ማሳያም ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

የፊፊ ጨዋታ ከሐምሌ 5 እስከ መስከረም 18 ምሽት 5፡00 ድረስ ታዛቢ ሽማግሌዎች ባሉበት ወጣቶቹ ልምምድ ሲያደርጉበት ከርመው መስከረም 21 ቀን በድምቀት የሚካሄድ ባሕላዊ ጨዋታ መሆኑን የጃዊ ወረዳ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታመነ ደምስ ተናግረዋል፡፡

የፊፊ ባሕላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች ከሽመል ተክልም ይሠራሉ፡፡ ጨዋታው በራሱ ቅንጅትና ልምምድን ይጠይቃል፡፡ የሙዚቃ መሳሪያዎቹ እንደ ቁመትና ውፍረታቸው የድምፅ ልዩነት ይፈጥራሉ፡፡ መሳሪያዎቹ ሰባት ዓይነት ሲሆኑ የየራሳቸው ስያሜና ሚና አላቸው፡፡ አሁን በጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉት ደግሞ አምስት ብቻ መሆናቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ ባሕላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎቹ የሚፈጥሩት ዜማ ትርጉም አለው፡፡

 

የመጀመሪያው ዜማ “ጊኝ ጊኝ” ይባላል፡፡ ትርጉሙም “ጠላቶች ሲመጡ ሩጠህ ተሰብሰብ” የሚል መልዕክት አለው፡፡ ሁለተኛው ዜማ “አጎተኒ” ይሰኛል፡፡ ትርጓሜውም “አይዞህ በርታ ደርሰንልሃል” ማለት ነው፡፡ ሦስተኛው “ወሴ አዴል” ይሰኛል፤ “ጠላትህን ተከላከል፣ የአፀፋ መልስ ስጥ፣ አትዘናጋ” የሚል ፍች አለው፡፡ ሌላኛው “አኹ ባምባኒ” ይሰኛል፤ “ውኃ ቢሞላብህ እኳን ጠላቶችህን ውኃውን ዋኝተህ አጥቃ” የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ “ይማንጀ ቲኪሊ” የተሰኘው ደግሞ “በሄድንበት አካባቢ ሁሉ ጥረን ግረን እንሥራ” የሚል ሐሳብ አለው፡፡ ይህ ጨዋታ ጠላት ድል ከተደረገ በኋላ የሚከወን ባሕላዊ ጨዋታ ነው፡፡

የፊፊ ባሕላዊ ጨዋታን የሚጫወቱ ልጃገረዶች ባሕላዊ ቀሚስ ይለብሳሉ፡፡ ወንዶች ደግሞ በጥንት ዘመን አባቶች ሲለብሱ የነበሩትን አለባበስ ነው የሚለብሱት፡፡ የመስቀል በዓል በብሔረሰብ አስተዳድሩ ክረምቱ መገባደዱ የሚገለፅበት፤ ወደ ብርሃንና አዲስ ዘመን መሸጋገሪያም ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

የፊፊ ባሕላዊ ጨዋታ የአካባቢውን ባሕል በማስተዋወቅ እና ትስስር በፍጠር ከፍተኛ ሚና እንዳለወም አቶ ታመነ አስረድተዋል፡፡ ባሕሉን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ የመሣሪያው ተጫዋቾች፣ የባሕልና ቱሪዝም ባለሙያዎች እንዲሁም ባሕሉን ተረካቢ ወጣቶች ትኩረት ሰጥተው በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ “ፊፊ” የተባለ የባሕል ቡድን በማቋቋምም ባሕሉ በተደራጀ አግባብ እንዲያዝ እየተደረገ መሆኑን የባሕልና ተሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊው ገልጸውልናል፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

Previous articleየቅጥር ማስታወቂያ
Next articleሱዳንና ደቡብ ሱዳን የኢጋድ አባል ሀገራት ለሰላማቸው እገዛ እንዲያደርጉላቸው ጠየቁ፡፡