ለአሸባሪው ትህነግ ወረራ መልስ ለመስጠት በቂ ዝግጅት ማድረጉን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አስታወቀ፡፡

202
ለአሸባሪው ትህነግ ወረራ መልስ ለመስጠት በቂ ዝግጅት ማድረጉን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 05/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ የማይካድራውን ዘግናኝ ታሪክ እንዳይደግም የአማራ ሕዝብ ያለው ብቸኛ አማራጭ የሕልውና ዘመቻውን በአሸናፊነት ማጠናቀቅ መሆኑን ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ገልጸዋል፡፡ የጥፋት ቡድኑ ካለፈ ስህተቱ ተምሮ ይቅርታ መጠየቅ ሲገባው በአማራ እና በአፋር ክልሎች ዳግም ወረራ እየፈጸመ ይገኛል፡፡ ከሰኔ 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በሚገኙ አካባቢዎች ተደጋጋሚ የማጥቃት ሙከራዎችን ጀምሮ እንደነበር የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ እና የሰላምና ሕዝብ ደኅንነት ጉዳዮች መምሪያ ኅላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡
ዞኑ በአሸባሪው ቡድን የዘመናት የዘር ማጽዳት ወንጀል ሲፈጸምበት እንደነበር ኮሎኔል ደመቀ አንስተዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ሕዝቡ የተስፋፊውን ትህነግ ወረራ የሚታገስበት ምክንያት የለም ነው ያሉት፡፡ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በሚገኙ አምስት የከተማ እና አራት የገጠር ወረዳዎች ውስጥ በቂ የጸጥታ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል ኮሎኔል ደመቀ፡፡
የአማራ ልዩ ኃይል፣ የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊት እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቅንጅት አስተማማኝ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ለጸጥታ ኃይሉ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በማድረግ እና በደጀንነት የሚያገለግለው የሕዝብ ተሳትፎም ጠንካራ መሆኑን ነው ኮሎኔል ደመቀ የገለጹት፡፡
ኮሎኔል ደመቀ አሸባሪው ትህነግ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ያደገበት ባህሪው መሆኑን ገልጸው የአማራ ሕዝብ ከዳር ዳር ለሕልውና ዘመቻው እና ለክተት ጥሪው ተግባራዊ ምላሽ ያስፈልጋል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ሰርጎ ገቦች ጥቃት እንዳይፈጽሙ ኬላዎች አካባቢ ጥብቅ ጥበቃ እና ፍተሻ ያስፈልጋል ያሉት ኮሎኔል ደመቀ ለዚህም የማኅበረሰቡ ክትትል እና ጥቆማ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ አሸባሪው የትህነግ ቡድን ከዚህ ቀደም እንደማይካድራ አይነት ዘግናኝ የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን በተለያዩ አካባቢዎች ለመፈጸም አቅዶ እንደተደረሰበት ኮሎኔል ደመቀ ጠቁመዋል፡፡
ያንን ዘግናኝ ታሪክ እንዳይደግም የአማራ ሕዝብ ያለው ብቸኛ አማራጭ የሕልውና ዘመቻውን በአሸናፊነት ማጠናቀቅ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡ “ከአያት ቅድመ አያቶቻችን የወረስነውን የአሸናፊነት ሥነ ልቦና በመላበስ በየግንባሩ ወርደን እንገናኝ” ብለዋል ኮሎኔሉ፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከሁመራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየሽብር ተልእኮን ለመፈፀም ቦንቦችን ታጥቆ ሲንቀሳቀስ የነበረን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የሰቲት ሁመራ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
Next articleየአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአፋር ክልል በፈንቲ ረሱ በጋሊኮማ ጊዜያዊ መጠለያ ተጠልለው በነበሩ ሕጻናት፣ ሴቶችና አርብቶ አደሮች ላይ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በፈፀመው አሰቃቂ ጭፍጨፋ የተሰማውን ሐዘን ገለጸ፡፡