
“አሸባሪው ቡድን ግብዓተ መሬቱ እውን ካልሆነ ከወረራ እንደማይታቀብ ስለሚታወቅ ቡድኑን ለመደምሰስ ወልቃይት ወረዳ በሁሉም ዘርፍ በቂ ቅድመ ዝግጅት አድርጓል” የወልቃይት ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ክብረአብ ስማቸው
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 05/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በመላው አማራ አካባቢዎች ላለፉት ዓመታት “ወልቃይት ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” ያሉ ወጣቶች ስለስሟ ሲሉ የሕይዎት፣ የአካል እና የሥነ ልቦና መስዋእትነት ከፍለዋል፡፡
ወልቃይት የአማራ የማንነት ጥያቄ የአማራ ሕዝብ የትግል ምልክት የሆነችው በእድል ሳይሆን በምክንያት ነው፡፡ ታሪክ አዋቂ የሆኑ እና አማራነታቸውን በግልጽ ያቀነቀኑ የወልቃይት ነዋሪዎች የወያኔ የግፍ በትር ደርሶባቸዋል፡፡
“አማራ ነን” ያሉ ወልቃይቴዎችን ገድሏል፣ አፈናቅሏል፣ ለእስር ዳርጓል፣ ሌሎች ግፎችንም ፈጽሟል።
ወልቃይቴዎች ይህ ሁሉ ግፍ ሲፈጸምባቸው እና “እናንተን ሳይሆን የምንፈልግ መሬቱን ነው” ሲባሉ አሜን ብለው አልተቀበሉም ነበር፡፡ “ከፋኝ” ብለው ጤዛ እየላሱ፣ ድንጋይ እየተንተራሱ፣ በዱር ውለው በጫካ አድረው የግፍ አገዛዙን እንደማይቀበሉት አሳይተዋል፡፡
ወልቃይቴዎች የእግር እሳት የሆኑበት ሴረኛው የትህነግ ቡድን ሕዝቡን ከማሰቃየት አልፎ መለኮታዊ ክብር የተሰጠውን ታላቁን የዋልድባ ገዳም ሳይቀር ለማፍረስ እስከመጣር ለበቀል ተነሳስቶም ነበር፡፡ የቀደመው የወልቃይት ሕዝብ የነፃነት ትግል ሲውል እና ሲያደር ይበልጡን እንደብረት ጠነከረ፤ እንደአለት እየጠጠረ መጥቶ የመላው አማራ ሕዝብ የትግል ምልክት ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
አሸባሪው የትህነግ ቡድን ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ በፈጸመው አስነዋሪ ክህደት በአማራ ልዩ ኀይል፣ በአማራ ሕዝባዊ ሠራዊት እና በሀገር መከላከያ ሠራዊት ብርቱ ክንዶች ተለበለበ፡፡ የዳንሻው ጦርነት ሳያልቅ ቀድሞ “ወልቃይትን እንደ ኪራይ ቤት ለቆ ወጣ” ይላሉ የወረዳዋ ነዋሪዎች፡፡
በወፍ አርግፍ ከተማ ያገኘናት የሚሊሻ አባል ብርጭቆ አበበ “ቀን የወጣልን ያኔ፤ መኖር የጀመርነውም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው” ብላለች፤ ሽብርተኛው ትህነግ ከወልቃይት የወጣበትን ቀን በመጥቀስ፡፡
በርካቶችን ለህልፈት፣ ለስደት እና ለአካል ጉዳት ዳርጎ የተገኘውን ነፃነት አስጠብቆ ለመቀጠልም ቀን ከሌሊት አካባቢያቸውን በንቃት እየጠበቁ መሆናቸውን ነው ሚሊሻ ብርጭቆ የነገረችን፡፡
ሌላው አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያነጋገራቸው የወልቃይት ወረዳ ነዋሪ አቶ አዛናው ገብረሚካኤል ሕዝቡ ላለፉት 40 ዓመታት ታሪክን እና ማንነትን መሰረት ያደረገ ትግል ሲያደርግ መቆየቱን ነግረውናል፡፡ ተስፋፊነት ካልሆነ በቀር ትግራይን ከተከዜ መለስ አናውቅም ያሉት አቶ አዛናው ይህ ማንነት ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታልና አሳልፈን የምንሰጠው ኀይል አይኖርም ብለዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ ሰኔ 24/2013 ዓ.ም ሽብርተኛው ትህነግ በመጀመሪያ ወረራ የሞከረው በተከዜ በኩል እንደነበር የወልቃይት ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ክብረአብ ስማቸው ተናግረዋል፡፡
በአማራ ልዩ ኀይል ምኒልክ ብርጌድ እና በአካባቢው ሕዝባዊ ሠራዊት በቂ ምላሽ ተሰጥቶታል ብለውናል፡፡ በተለያዩ መንገዶች ሰርገው ለመግባት ሙከራ ያደረጉ ሰላዮችን የመያዝ እና ከውስጥ ያሉ ባንዳዎችን የመለየት ሥራ መሠራቱን ነው ዋና አስተዳዳሪው የተናገሩት፡፡
በአካባቢው ያለው የጸጥታ ኃይል መናበብ እና ቅንጅት መልካም ነው፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊቱም ሕዝቡ ምን ያክል አስተማማኝ ደጀን መሆኑን ተረድቷል ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው፡፡
በየደረጃው ያለው የመንግሥት የሥራ ኅላፊ ግንባር ድረስ በመውረድ ታግሎ እያታገለ መሆኑን የገለጹት አቶ ክብረአብ “እኛ እንደ አሸባሪው ትህነግ ህጻናትን ፊት ለፊት ማግደን በድሃ ደም አንቀልድም” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አሸባሪው ቡድን ግብዓተ መሬቱ እውን ካልሆነ ከወረራ እንደማይታቀብ ስለሚታወቅ ቡድኑን ለመደምሰስ ወልቃይት ወረዳ በሁሉም ዘርፍ በቂ ቅድመ ዝግጅት ማደረጉን ነው ዋና አስተዳዳሪው የገለጹት፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከወልቃይት
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ