
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 05/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪውን የትህነግ ቡድን ለመደምሰስ ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረገ ለሚገኘው የጸጥታ ኃይል ከኅብረተሰቡ ጋር ሁለንተናዊ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን የሰሜን ጎንደር ዞን ብልጽግና ፖርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ብርሃኑ ዘውዱ አስረድተዋል።
የወራሪውን ኃይል ለመደምሰስ በግንባር እንደተሰለፉ የገለጹት አቶ ብርሃኑ የአካባቢው ወጣቶች፣ ሚሊሻ እና ፋኖ ከልዩ ኀይልና ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በጥምረት ሽብርተኛውን ትህነግ ለመደምሰስ በቂ ዝግጅት አድርገናል ብለዋል፡፡
በዞኑ ውስጥ የሚገኙት ባለሀብቶችም የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ እስከ ግንባር በመሠለፍ እየሠሩት ያለው ሥራ የሚያኮራ መሆኑን አቶ ብርሃኑ አብራርተዋል።
ጠላት በሰሜን ጎንደር ዞን በተለያዩ አካባቢዎች ውጊያ ቢከፍትም በወገን ጦር ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰበት ነውም ብለዋል።
ሕዝቡ ያለውን መሣሪያ ይዞ ሽብርተኛውን ቡድን ለመደምሰስ የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉንም ኀላፊው አስታውቀዋል፡፡
በሰሜን ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ የማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀል ክፍል ኀላፊ ኮማንደር አበበ ወረት እንደገለጹት ሽብርተኛውን ትህነግ ለመደምሰስ ወጣቱ በተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ ተካቶ ወታደራዊ ስልጠና ወስዷል፤ ስምሪትም ተሰጥቶታል። በዞኑ ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱ ወጣቶች ተደራጅተው ወራሪውን ቡድን እየደመሰሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
“ወያኔ ሰርጎ ገቦችን እያስገባች ነው” ያሉት ኮማንደር አበበ ወጣቱም ሰርጎ ገብንና ነዋሪውን ጠንቅቆ ስለሚያውቅ የአሸባሪውን ሰርጎ ገቦች ለሕግ እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሕዝቡ በሁሉም አካባቢዎች የሀገር መከላከያ ሠራዊቱ፣ የልዩ ኃይሉ፣ ሚሊሻው እና ፋኖ ደጀን ሆኖ እየሠራ ነው ብለዋል።
የደባርቅ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሰለሞን ተዘራ “መሪዎቹ ግንባር ተሠልፈናል፤ ለጸጥታው ኀይልም ስንቅ እያቀረበ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
የህልውና ዘመቻውን በድል ለማጠናቀቅ ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡
ጀግናው የደባርቅ ሕዝብ ዛሬም እንደወትሮው ሁሉ ዝግጁ በመሆን አሸባሪውን ቡድን እንዲደመስስ ከንቲባ ሰለሞን ጥሪ አስተላልፈዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ