
‹‹የባንዳዎችን ሀገር የማፈራረስ ምኞትና የውጭ ኀይሎችን ጣልቃ ገብነትን ለመመከት ሕዝቡ በአንድነት መቆም አለበት›› አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 04/2013 ዓ.ም (አሚኮ)የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ከምክር ቤት አባላት ጋር ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ደም ለግሰዋል፡፡
የባንዳዎችን ሀገር የማፈራረስ ምኞትና የውጭ ኀይሎች ጣልቃ ገብነት ሕዝቡ በአንድነት ቆሞ ሊያከሽፍ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሌሎችን ሀገሮች ጥቅም ያለአግባብ መውሰድ እንደማትፈልግ ኹሉ የራሷንም ጥቅም አሳልፋ እንደማትሰጥ አውቀው የውጭ ወራሪ ኀይሎች ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ወራሪውን ቡድን ለመመከት የምክር ቤት አባላትና የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለመከላከያ ሠራዊቱ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ የምክር ቤት አባላት ደም መለገሳቸውን ተናግረዋል፡፡
የምክር ቤት አባላትም ስንቅ በማዘጋጀት ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን መሰለፋቸውንም ነው አፈ ጉባኤው የጠቆሙት፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የተከበሩ ወይዘሮ ነኢማ መሐመድ በበኩላቸው የመከላከያ ሠራዊቱ የሀገሩን ክብር ለመጠበቅ፣ የውጭ ወራሪዎችን ምኞት ለመግታትና ሀገር ለማፈራረስ የሚመኙትን ጠላቶች ለመመከት መተኪያ የሌላትን ሕይወቱን ለመስጠት በግንባር ከተሰለፈው የመከላከያ ሠራዊት ጎን መሰለፋቸውን ለማሳየት ደም መለገሳቸውን ተናግረዋል፡፡
ሌላው የምክር ቤት አባል የተከበሩ አቶ ተስፋዬ ሮበሌ እኩይ ዓላማ አንግበው ሀገር ለማፈራረስ የተሱት የውስጥ ቡድኖችና የውጭ ጣልቃ ገቦችን ለመመከት ሠራዊቱ ለሚያደርገው ተጋድሎ ከጎኑ ለመቆምና ወገንተኛነታቸውን ለማሳየት ደም መለገሳቸውን ነው የገለጹት፡፡
የውጭ ጣልቃ ገቦችንም ኾነ ሀገር ለማፈራረስ የተነሱትን የሀገር ውስጥ ነቀርሳዎችን ምኞት ለመመከት ሕዝቡ በአንድነት ቆሞ ሊመክት እንደሚገባውም መግለጻቸውን ከምክር ቤቱ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m