
አሸባሪውን ትህነግ ለመደምሰስ መዘጋጀታቸውን የምዕራብ ጎጃም ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር: ነሐሴ 04/2013 ዓ.ም(አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ በአማራ ክልል ወረራ በመፈጸም ሀገርን ለመበታተን የከፈተውን ጦርነት በአንድነት መታገል እንደሚገባ የምዕራብ ጎጃም ዞን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤ አባላት ከምዕራብ ጎጃም ዞን ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱ ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት፣ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ የሃይማኖት አባቶችና ወጣቶች ተሳትፈዋል፡፡
የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤ ሊቀመንበር ገበያው ጥሩነህ (ዶክተር) መድረኩ የተዘጋጀው ሁሉም ኅብረተሰብ የህልውና ዘመቻውን ተረድቶ እንዲንቀሳቀስ የሚያስችል አደረጃጀት መፍጠር ላይ ያተኮረ መኾኑን ገልጸዋል።
ሕዝቡ በመንግሥት የቀረበውን የክተት ዘመቻ ጥሪ በመቀበል በጦር ግንባር በመሠለፍ የተጋረጠውን የህልውና አደጋ ሊመክት ይገባልም ብለዋል፡፡

ሀገርን ከመበታተን በማዳን ለትውልድ ማስተላለፍ ውዴታ ሳይኾን ግዴታ ነው ያሉት ደግሞ የውይይቱ አስተባባሪ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ ናቸው፡፡ ትህነግ ሀገር እና ሕዝብ ሊያጠፋ የመጣ አሸባሪ ኀይል በመኾኑ እንደ ሕዝብ በጋራ መመከት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል መልዓከ ጥበብ መርጌታ ስሜነህ አበበ እና ወይዘሮ እናትነሽ በዛብህ አሸባሪው ትህነግ የአማራን ሕዝብ ሰላም በመንሳት ሀገሪቱን ለማፍረስ እየሠራ መኾኑን በመረዳት በተባበረ ክንድ ለመመከት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የአሸባሪው ትህነግ አሁናዊ እንቅስቃሴ እና እየፈጸመ ያለውን ወረራ እንዲሁም እኩይ ድርጊቱን ለመመከት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በምሁራን ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎ የጋራ ግንዛቤ ተይዟል፡፡

ዘጋቢ፡-ዘመኑ ይርጋ -ከፍኖተ ሰላም
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ