
<<መክፈል የሚገባውን መስዋእትነት በመክፈል ሀገርን መታደግ አለብን>> የወልድያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሙሐመድ ያሲን
ባሕር ዳር: ነሐሴ 03/2013 ዓ.ም (አሚኮ) መሪ አሻጋሪ፣ መስመር አስማሪ ነው። በጥሩ ስትመራ ሀገር ታሻግራለህ፣ ወገንህን ታስከብራለህ፣ አንገትህን ቀና አድርገህ ትሄዳለህ፣ ታሪክ ትሠራለህ፣ በታሪክም ትዘከራለህ። የትህነግ አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ፣ ክብሯን ለማንኳሰስ በመፍጨርጨር ላይ ነው። በተለይም ደግሞ የአማራን ሕዝብ ለመጉዳት የማይሞክረው ነገር የለም። በዋሻ ውስጥ የከረመው አሸባሪው ትህነግ ለትግራይ ሕዝብ እፎይታ ለመስጠት በተሰጠው የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ እድሜ ቀጥሎ ውጊያ ከፍቷል።
አሸባሪው ትህነግ በተደጋጋሚ አንገቱን የደፋባት፣ የተሸፈነባትና ክብሩን ያጣባት ከተማ አለች። ይህችም ከተማ ወልድያ ናት።
የአሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ ከሌሎች ክልሎች ልዩ ኀይል ጋር በመሆን ተጋድሎ እያደረገ ነው።
የወልድያ ከተማ ጠላት እንዳይገባባትና ሕዝቡ በጽናት እንዲታገል በማድረግ በኩል ቀዳሚ ሥፍራ ላይ የሚቀመጡ ሰው አሉ – የወልድያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሙሐመድ ያሲን። የከተማዋ ወጣቶች ከንቲባው የዘመኑ ጀግና ናቸው ይሏቸዋል። በክፉም በደግም ቀን ከፊት ለመውደቅ ዝግጁ የሆኑ ጀግና ናቸውም ይሏቸዋል።
ከንቲባው ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ የአሸባሪው ትህነግ ተስፋፊ ቡድን የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ወልድያን ለመያዝ ጥረት ቢያደርግም በጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ ዘመቻ ህልሙ ቅዠት እንዲሆን እየተመታ ነውም ብለዋል። ወልድያን ለመያዝ በሚያደርገው ሙከራ አብዛኛው ተደምስሷል ፣ ከፈሉም መፈርጠጥ የየዕለት ተግባሩ መሆኑን ነው የገለፁት። አንድም የአሸባሪው ትህነግ ቡድን ወልድያን ረግጦ አለመምጣቱንም ገልፀዋል።
አሸባሪው ትህነግ በግብረ አበሮቹ ወልድያን ይዤያታለሁ ቢልም ወልድያ የአሸባሪውን ቡድን እየቀበረች በጽናቷ ቀጥላለች ነው ያሉት። ወልድያን እና አካባቢውን ለመያዝ እያደረጉት ያለው ሙከራ በተደጋጋሚ እየከሸፈ መሆኑንም ገልጸዋል።
አሸባሪው ትህነግ ገና በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ካደረሰበት ጊዜ ጀምሮ ቡድኑን ለመደምሰስ የወልድያ ከተማ አስተዳደርና የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር በቅንጅት ሲሠሩ እንደነበርም አስታውሰዋል። አሸባሪ ቡድኑ ዳግመኛ ጥቃት ሲጀምርም ከሁልጊዜው በበለጠ መልኩ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመቀናጀት ሰላምን ለማስፈንና ተስፋፊውን ቡድን ለመደምሰሰ ተከታታይነት ያለው ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል። በተሰጠው አቅጣጫ በሰሜን ወሎ ዞን የሚገኙ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ድጋፍ በማድረግ ኀላፊነቱን ሲወጣ መቆየቱንም ከንቲባው ተናግረዋል።
በከተማዋ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር ሲሠራ መቆየቱንና አሁንም እየተሠራ መሆኑን ነው የተናገሩት። የከተማዋ ወጣቶች በመደራጀት ቀንና ማታ በመፈተሽና ሰላሙን በማስጠበቅ አስደናቂ ሥራ መሥራታቸውንም ተናግረዋል። የሥራ ኃላፊዎች መናበብና ከወጣቶች ጋር በቅንጅት መሥራት ውጤታማ ማድረጉንም አስታውቀዋል። ለሠራዊቱ እውነተኛ ደጀን የሆነ ሕዝብ መሆኑን ያረጋገጠ ነውም ብለዋል። በተፈጠረው ቅንጅትና ቁርጠኛ አሠራር የጠላት ኀይል እቅዱ እንዲከሽፍበትና ከፍተኛ የሆነ ኪሳራ እንዲደርስበት መደረጉንም ተናግረዋል። የከተማዋ ማኅበረሰብ እና አስተዳደሩ የሚጠበቅበትን እያደረገ ነውም ብለዋል።
የከተማዋ ወጣቶች ለሠራዊቱ ምግብ በማቀበል፣ ከተማዋን በመጠበቅና አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን በመመካከር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል። ከተማዋን ለማሸበር የሚንቀሳቀሱ ኀይሎችን እያደኑ በመያዝ ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውንም ነግረውናል። ድጋፍ የሚደረገውን ሀብት በግልጸኝነት በመጠቀም ለሚፈለገው ዓላማ እንደሚያውሉም ተናግረዋል። የከተማዋ የሥራ ኃላፊዎች በቅንጅት አስፈላጊውን ነገር በማድረግ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል። የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የአሸባሪው ትህነግ ቡድን በውጊያ እንደማያሸነፍ በመረዳት ያለ የሌለ ኀይሉን እየተጠቀመ ያለው በሐሰት ፕሮጋንዳ ነው ያሉት ከንቲባው ማንኛውም የሥራ ኀላፊ ሳይረበሽ አካባቢውን መምራት አለብትም ብለዋል። ማኅበረሰቡን እያረጋጉ የሚመሩና የሚታገሉ ቁርጠኛ የሥራ ኀላፊዎች በከተማዋም በዞኑም መኖራቸውን ገልጸዋል። የጠላት ዋነኛ መገለጫው ውሸት ነው፣ በውሸት ሳንፈታ፣ መሬት ላይ ያለውን እውነት እያነበብን፣ ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት በተጀመረው አግባብ የምንቀጥል ከሆነ በወሬ የማንፈታ በተግባር የምናሸንፍ እንሆናለን ነው ያሉት ከንቲባው።
ጠላት ባይሳካለትም ኢትዮጵያን ለመበተን ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው ያሉት ከንቲባው ሸብረክ የሚል መሪ ከተገኘ ኢትዮጵያን ለመበተን እና እርሱ በሚፈልገው መንገድ ለመግዛት እንደሚሄድም ተናግረዋል። የውስጥና የውጭ ጠላቶች በመናበብ ኢትዮጵያን ለማሳነስ እየሠሩ በመሆናቸው እያንዳንዱ የሥራ ኀላፊ ይህንን ታሳቢ በማድረግ በሰላም ጊዜ ከሚሠራው በበለጠ የአመራር ሰጭነት ሚናውን ማሳደግ አለበትም ብለዋል። “መከፈል የሚገባውን መስዋዕት በመክፈል ሀገርን መታደግ አለብንም” ነው ያሉት። መኖር የምንችለው ኢትዮጵያ እንደ ሀገር መቀጠል ስትችል ነውም ብለዋል። የሥራ ኀላፊዎችን ከሕዝብ ለመነጠልና ለጠላት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ጥረት የሚያደርጉ ሰዎችም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
እንደ ሥራ ኃላፊ አንድ በመሆን ያለ ረፍት በመሥራት ጠላትን መደምሰስ ይገባል ያሉት ከንቲባው የመጣው ጠላት ሕዝብን ለውርደት፣ ንብረትን ለውድመት፣ ሀገርን ለውድቀት የሚዳርግ እንደሆነም ገልጸዋል። ብቃት ያለው መሪና ሲኖርና መሪውን የሚደግፍ ሕዝብ ሲፈጠር እንኳን የውስጥን ተላላኪ ጠላት ይቅርና የውጭን ጠላት ማንበርከክ እንደሚቻል ታሪካችን ምስክር ነው ብለዋል። የሐሰት መረጃዎችን እንመክታለን ጦርነቱንም አሸንፈን አካባቢያችን ነፃ እናደርጋለንም ብለዋል። ኅብረተሰቡ በሐሰተኛ ወሬ ሳይረበሽ ትግሉን ማፋጠን እንደሚገባውም ጠይቀዋል። የሠራዊቱን እንቅስቃሴ ለጸጥታው ኀይል በመተው ለሠራዊቱ ደጀን በመሆን በአጭር ጊዜ ድል ለመንሳት መረባረብ ያስፈልጋልም ብለዋል። ውጤት ሲመጣ የሚያጨበጭብ ውጤት ሳይገኝ ሲቀር ደግሞ የሚያጥላላ ማኅበረሰብ ካለ ውጤታማ መሆን አይቻልምም ነው ያሉት። አንድነትን በማጠናከር ጠላትን መደምሰስ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
እየተገኘ ላለው ውጤት የሚሰጠውን አቅጣጫ በአግባቡ መተግበር መቻሉ መሆኑንም ተናግረዋል። ከወገን ጦር የሚሰጠውን መረጃ በመተንተን በአግባቡ በመጠቀም መሥራት መቻሉ ውጤታማ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል። ጠላት ግብዓተ መሬቱ እስኪፈፀም ድረስ አስፈላጊውን መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነንም ብለዋል። ጸንቶ የሚቆም መሪ ጸንቶ የሚቆም ሕዝብ ካለው ሽንፈት አያጋጥመውም፣ እስከመጨረሻው ድረስ የሚጠበቅብን ለማድረግ ዝግጁ ነን ነው ያሉት።
በሥፍራው ተገኝተን እንዳረጋገጥነው አሸባሪው ቡድን
ውጊያ ቢከፍትም የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች እየተፋለሙት ነው።
ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m