ፋኖ ጀግኒት በወልቃይት!

3006

ፋኖ ጀግኒት በወልቃይት!

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 03/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያዊያን የጀግንነት ታሪክ ውስጥ ሴትነት የተለየ ቦታ አለው፡፡ ዓለም ከፍላን ዴቪ እስከ ሮዛ ፓርክስ የነፃነት ታጋይ ሴቶችን ሳይተዋወቅ ኢትዮጵያ ግን በጀግና ሴቶች ትመራ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ከህንደኬ እስከ ሳባ፤ ከጣይቱ እስከ ዘውዲቱ ዓለምን በጀግንነታቸው እና በቆራጥነታቸው አጃይብ ያሰኙ የጀግና ሴቶች ባለቤት ነች፡፡ ትናንት በሕግ ማስከበር ዘመቻው ምሽግ ሰብረው ከሃዲ የማረኩ እና ባንዳ አግተው ለሕግ ያቀረቡ ጀግና ሴቶችን አይተናል፤ አይተንም በዚህ ዘመን “እቴጌዎች” ተስፋ አድርገናል፡፡

ዛሬ ደግሞ ባለፉት ዓመታት “ከፋኝ” ብለው በዱር በገደሉ ሲዋደቁ የነበሩ እና “አማራነት ወይ ሞት” ያሉ፣ የሕግ ማስከበር ዘመቻው ፈርጦች እና የሕልውና ዘመቻው ተስፋዎች የሆኑትን የተከዜ ወዲህ ማዶ ሴት ፋኖዎችን እናስተዋውቃችሁ፡፡

ልምላሜው ቀልብን በሚስበው እና መልከዓ ምድራዊ አቀማመጡ ብርታትን በሚፈታተነው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ድንበር አካባቢ ጀግንነትን የሚፈታተን የሴት ልጅ ሽለላ ይሰማል፡፡ በዚያ ጫካ ውስጥ የሚያንጎራጉሩት ሴቶች ያለፈ ዘመን በደልን መልሶ እና መላልሶ ያስታውሳል፡፡

ወያኔ በሬ አርዶ ሻኛ ቀርቦላቸው፣
ሳይበሉት ተነሱ ፋኖ ደርሶባቸው
ጥሊያን በሮቢላ ያቃታትን ሰው፣
ወያኔ በሃሺሽ ልትዋጋው ነው፣
ገለባ በዛና እሳትን ጎበኘው ስትል ለሰማ ሁሉ እረፍት ትነሳለች፡፡ ያለፈ በደል ያበረታቸው፣ ሕዝብን ከራሳቸው በፊት ያስቀደሙት ሴት ፋኖዎች ለዳግም የሕልውና ዘመቻ “ዱር ቤቴ” ብለዋል፡፡

ፋኑስ ቸኮለ እና አማረች እሸቴ ከሦስት ዓመታት በላይ በፋኖነት በሶሮቃ በረሃ ውስጥ በትግል አሳልፈዋል፡፡ “ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ላይ መሬት እንጅ አማራ ማየት አንፈልግም” የሚሉት ወራሪዎች #የሞቀ ቤቴን እና ቤተሰቤን ትቼ ጫካ እንደግባ አስገደደኝ; ትላለች ሴት አርበኛ ፋኖ ፋኑስ ቸኮለ፡፡

ፋኖ ፋኑስ ታስረሽ ታውቂያለሽ? ስንል ላነሳንላት ጥያቄ “ያውም ሁለት ሦስቴ” ካለች በኋላ ምክንያቷን ስትነግረን ከተከዜ መለስ ትግሬ እንጂ ትግራይ የለም፤ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ የአማራ ነው ማለቷ ከወራሪዎቹ ጥርስ ውስጥ እንዳስገባት ነግራናለች፡፡ በዳንሻ ከተማ በሆቴል ሥራ ትተዳደር የነበረችው ፋኑስ “ማርዘነብ ምግብ ቤት” የሚለው የድርጅቷ መጠሪያ በትግረኛ ካልተጻፈ በሚል በወቅቱ ከነበሩት የአካባቢው አመራሮች ጋር ግጭት ውስጥ አስገባት፡፡ ለመቀየር ፈቃደኛ ባለመሆኗ ቤተሰቦቿን ትታ የድርጅቷን መጠሪያ እና አንድ ኮልት ሽጉጥ ብቻ ይዛ በቅራቅር በርሃ ውስጥ ፋኖን ተቀላቀለች፡፡

ሌላኛዋ ሴት አርበኛ ፋኖ አማረች እሸቴ “የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ አካባቢ ሰው መሳሪያ መታጠቅ የለበትም፤ ሁላችሁም መሳሪያውን ለመንግሥት አስገቡ” ይሉ ከነበሩት የአሸባሪው ትህነግ አመራሮች ጋር ግጭት ውስጥ የገባችው ፋኖ አማረች በየጊዜው መነታረክ ሲሰለቻት “ዱር ቤቴ” ብላ ፋኖን በቅራቅር በርሃ ውስጥ ተቀላቀለች፡፡

አሸባሪው ትህነግ በዳንሻ ላይ የፈጸመን ጥቃት በብቃት ከመከቱት የአማራ ልዩ ኀይል፣የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ሚሊሻ ጎን እኒህ ጀግና ፋኖዎች ነበሩ፡፡ ተከዜ ድንበራችን ነው እንዳሉትም እስከ ተከዜ እያሳደዱ ሸኟቸው፡፡ ድንበራቸውን በመሳሪያቸው ማንነታቸውን በተጋድሏቸው አስከብረው ከጫካ ወደ ዳንሻ በጀግና አቀባበል ተመለሱ፡፡

ከምንም በላይ አያት ቅድመ አያቶቻችን እንደ ታሪክ የሚያወሩት ማንነት በዚህ በእኛ ዘመን ያውም በትግላችን ተመልሶ ማየታችን አስድስቶናል ያሉት የፋኖ አባላት ዳግም ባርነት አይደለም በእነርሱ ዘመን በመጭው ትውልድ እንኳን የማይታሰብ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ካገኙት የነፃነት እፎይታ በኋላ “በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል” እንዲሉ እነዚህ የፋኖ አባላት ለዳግማዊ የሕልውና ዘመቻ ዱር ቤቴ ካሉ ሰነባብተዋል፡፡ ፋኖ ፋኑስ ቸኮል አሸባሪው ቡድን ባለፉት ዘመናት በስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት በዘረፈው ሃብት እና ንብረት ከውስጥም ከውጭም ተላላኪዎችን ገዝቷል ነው የምትለው፡፡

ወያኔ ዳግም ከምትመለስ መሞት በብዙ እጥፍ ስለሚሻል አቅማቸውን ተጠቅመው ግብዓተ መሬቱን ለመፈጸም እንደተዘጋጁም ነግራናለች፡፡ ፋኖ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ለዓመታት ባደረገው መራር ተጋድሎ ማንነቱን አስመልሷል ብላለች፡፡

ኢትዮጵያ ለዘመናት በልጆቿ መራር ተጋድሎ ታፍራ እና ተከብራ ኖራለች ያሉን እነዚህ ጀግና ሴት ፋኖዎች ማንነታቸውን አስከብረው ለመቀጠል እና የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ለማስከበር ዝግጁ መሆናቸውንም ነው ያረጋገጡት፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው – ከሁመራ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleበኩር ጋዜጣ ነሐሴ 03/2013 ዓ.ም ዕትም
Next article<<መክፈል የሚገባውን መስዋእትነት በመክፈል ሀገርን መታደግ አለብን>> የወልድያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሙሐመድ ያሲን