አደረጃጀት ፈጥረው አካባቢያቸውን ከሽብርተኛው ትህነግ ሰርጎ ገቦች እየጠበቁ መሆናቸውን የደባርቅ ዙሪያ ወረዳ ወጣቶች ገለጹ፡፡

206
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 03/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአሸባሪው፣ ተስፋፊው እና ዘራፊው የትህነግ ቡድን ሊፈጽመው ከሚችለው ወረራ አካባቢያቸውን ለመጠበቅ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኃይል እና ከፋኖ ጋር በመሆን በንቃት እየሠሩ መሆናቸውን የሰሜን ጎንደር ዞን ወጣቶች ተናግረዋል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የጋዜጠኞች ቡድን በሰሜን ጎንደር ዞን ተዘዋውሮ እንደተመለከተው በደባርቅ ዙሪያ ወረዳ የሚገኙ ወጣቶች ጠላትን ለመደምሰስ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በቅንጅት እየሠሩ ይገኛሉ።
በደባርቅ ዙሪያ ወረዳ ድብ ባሕር ቀበሌ ያነጋገርነው ወጣት ሙሉቀን ጌጡ በአካባቢው ተደራጅተው በሚያደርጉት ጥበቃ ሽብርተኛው ትህነግ የሚልካቸውን ሰርጎ ገብ ተላላኪዎችን በመያዝ ለሕግ እያቀረቡ መሆናቸውን አስረድቷል። ወጣቱ ለአካባቢያቸው የጸጥታ ስጋት የሚሆን ጉዳይ ሲመለከቱ ለጸጥታ ተቋማት በመጠቆም በጋራ እየሠሩ መሆናቸውንም ተናግሯል፡፡ በሁሉም ኬላዎች የአካባቢው ወጣት ተሠማርቶ 24 ሰዓት እየጠበቀ መሆኑንም ነግሮናል። በመሆኑም የጠላት ሰርጎ ገብ ወደ አካባቢው የመምጣት አቅም የለውም ብሏል።
ሽብርተኛውን ትህነግ ለመደምሰስ የሚያስችል ዝግጅት ማድረጋቸውንም ወጣት ሙሉቀን ተናግሯል።
ሌላኛው የድብ ባሕር ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ሰንደቅ አምሳል እንደገለጸው በመደራጀት አካባቢያቸውን በንቃት እየጠበቁ ነው። የወልድያ ወጣቶች እየሠሩት ያለውን ጀብድ ሁሉም ወጣት መተግበር አለበትም ብሏል።
ወጣቶቹ የመግቢያ በሮችን ከመጠበቅ ባለፈ በአካባቢው ለተሠማራው የጸጥታ ኀይል ሁለንተናዊ ድጋፍ እያደረጉ ነው።
የድብ ባሕር ቀበሌ የሰላምና ሕዝብ ደኅንነት ኀላፊ ደጀን ወልዴ ኅብረተሰቡ በሐሰት ፕሮፓጋንዳ ሳይደናገር ጠንካራ አደረጃጀት መሥርቶ ጠላትን የመደምሰስ ሥራ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የሥራ ኅላፊዎችም ዋና ዋና በሮች እንዲጠበቁ በማድረግ ድጋፍና ክትትል እያደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ኀላፊው ወጣቶች ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከልዩ ኃይል እና ከሚሊሻው ጋር በመተባበር እየሠሩ ያሉትን ሥራም ማጠናከር እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ አዳሙ ሽባባው-ከደባርቅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ሽብርተኛውን ቡድን ላይመለስ በመቅበር አንድነታችንን አጠንክረን መያዝ አለብን” የኢፌዴሪ ገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው
Next articleበኩር ጋዜጣ ነሐሴ 03/2013 ዓ.ም ዕትም