
“ሽብርተኛውን ቡድን ላይመለስ በመቅበር አንድነታችንን አጠንክረን መያዝ አለብን” የኢፌዴሪ ገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 03/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በመሠረታዊ ውትድርና ያሰለጠናቸውን ተጠባባቂ ኃይል ትናንት አስመርቋል፡፡
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው “ሽብርተኛውን ቡድን ላይመለስ በመቅበር አንድነታችንን አጠንክረን መያዝ አለብን” ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ ሽብርተኛው የትህነግ ቡድን ለ27 ዓመታት ሳይታክት በሠራው ሥራ ኢትዮጵያን በዘር፣ በሃይማኖት እና በቋንቋ ሲከፋፍል መቆየቱን ገልጸው ይህን ቡድን በመቅበር አንድነትን ማስጠበቅ ይገባል ብለዋል፡፡
አማራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ደፋ ቀና ቢልም አሸባሪው ትህነግ ግን ለዘመናት አማራ በዳይ እና ጨቋኝ እንደኾነ አድርጎ በመሥራቱ ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር ደም ሲያቃባው መኖሩንም አንስተዋል፡፡
ሽብርተኛው ትህነግ አማራን አንገት ለማስደፋት አቅዶ እና በበጀት አስደግፎ መሥራቱ ሳያንሠው ዛሬም “የማወራርደው ሒሳብ አለኝ” ብሎ መምጣቱ ጥላቻው የቆየ መኾኑን አመላካች ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
“አባቶቻችን መስዋእትነትን ከፍለው ነፃ ሀገር አስረክበውናል፤ በእኛ ዘመን ታሪክ ሊበላሽ አይገባም፤ እኛም ለልጆቻችን ነፃ ሀገር ለማስረከብ በጋራ ልንቆም ይገባል” ብለዋል አቶ ላቀ።

ሀገር አደጋ ላይ እያለች “አለቃ ነኝ፤ ቢሮ ሥራ አለብኝ” የሚለው ንግግር ተቀባይነት የለውም፤ ሁሉም የሀገርን ህልውና ለመጠበቅ ወደ ግንባር መሄድ ምርጫ ውስጥ የማናስገባው ጉዳይ ነው፤ ሁሉም ለዚህ ራሱን ማዘጋጀት አለበት ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ሚኒስትሩ ሽብርተኛው ትህነግን መደምሰስ በአጭር ቀን እንጅ በተራዘመ ጦርነት ሊሆን እንደማይገባም አብራርተዋል፡፡
ወጣቱ በማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ በሚያገኘው የተሳሳተ መረጃ ተጠምዶ ጊዜውን ከማሳለፍ መሰረታዊ ሥልጠና በመውሠድ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከልዩ ኀይል፣ ከሚሊሻ እና ከፋኖ ጎን በመሠለፍ የአማራን ሕዝብ ህልውና እየተፈታተነ የሚገኘውን ቡድን ማስወገድ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
አቶ ላቀ ሽብርተኛው ቡድን ዳግም እንዳይመለስ እና ኢትዮጵያ በልማት ጎዳና እንድትራመድ ማኅበረሰቡ እስካሁን ያደረገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአማራ በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጸመ ያለውን ወረራ ለማስቆም “ርብርቡ መደረግ ያለበት አሁን ነው” ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ሚኒስትሩ “አሸባሪውን ቡድን በመቅበር አንድነታችንን በዓለም አደባባይ ልናስመሰክር ይገባል” ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ