
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳድር በመጀመሪያ ዙር ያሠለጠናቸውን የተጠባባቂ ኀይል አባላትን አስመረቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 02/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሰተዳደር በስድስቱም ክፍለ ከተሞች ወጣቶችን በመጀመሪያ ዙር የውትድርና ስልጠና በማሠልጠን ዛሬ አስመረርቋል፡፡ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳኅሉ (ዶከተር) አሸባሪው ትህነግን ለመደምሰስ ከመከላከያ፣ ከልዩ ኀይል፣ ከሚሊሻና ከፋኖ ጎን ለመሰለፍ ለክልላችሁ ደጀን በመሆን ግንባር ድረስ ለመፋለም የተሠጣችሁን ወታደራዊ ሥልጠና ያጠናቀቃችሁ ወጣቶች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ተመራቂዎቹ ሁለት መሠረታዊ ተግባራትን ለመፈጸም ዝግጁ መሆን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡ የመከላከያ ሠራተዊትና የአማራ ልዩ ኀይል ወደ ግንበር ሲገሠግሱ እናንት የአካባቢያችሁን ሰላም ነቅታችሁ በመጠበቅ ሠርጎ ገቦችን አነፍንፎ በመያዝ ሕዝቡ በሠላም ወጥቶ በሰላም እንዲገባ ማድረግ ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡ ዶክተር ድረስ ግንባር ላይ የሚፋለመውን ኀይል በማገዝም የሀገራችሁን ህልውና በማስጠበቅ በአባቶቻችሁ አጥንት እና ደም ተከብራ የኖረችውን ሀገራችሁን ከጠላት እንድትጠብቋት አደራ እላለሁ ነው ያሉት፡፡
ሥልጠናው የነበሩባችሁን ብዥታ ያጠፋ እና ለሀገራችሁ ያላችሁን ቁርጠኝነት ያሳየ፤ የዓላማ፣ የተልኮ ጥራትን ያመጣ ነው፤ የአማራ ሕዝብ አንገቱን ሊደፋ አይገባም በተባበረ ክንድ ጠላታችንን ድባቅ በመምታት ላይመለስ መሸኘት አለበት ብለዋል፡፡
የአማራነትን ሥነ ልቦና ገንብታችሁ አማራን ወደ ነበረበት ከፍታ ለመመለስ የተጣለባችሁን አደራ በትጋት እንድትወጡ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው።
የጠቅላይ ሚንስትሩ የደኅንነት አማካሪ ገዱ አንዳርጋቸው ሽብርተኛው የትህነግ ቡድን ሀገራችንን ለውድቀት ለመዳረግ፣ የሕዝባችንን ክብር ለማዋረድ ሌት ከቀን እየሠራ ቢሆንም እናንተ መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ በመኾናችሁ ክብር ይገባችኋል ብለዋል፡፡ ይህ መስዋእትነት ለፍትሕ ሲባል የሚከፈል በመኾኑ ሁላችንም ሀገር ለማፍረስ የተሠማራውን ወራሪ ቡድን ለመመከት በጋራ ልንቆም ይገባል ብለዋል፡፡
የትህነግ ሽብርተኛ ቡድን አሁን ግልጽ ወረራ አካሂዶብናል፤ ሕዝቡን እየዘረፈ፣ መሠረተ ልማቶችን እያወደመ ስለሆነ ይኼንን ወራሪ ቡድን ለመመከት የሚከፈለው መስዋእትነት ለፍትሕ፣ ለእውነትና ለሕዝብ ክብር ሲባል ነው ብለዋል፡፡
የሕዝባችንን ክብር ከፍ ለማድረግ መብታችንን ለማስከበር የሀገራችን እና የሕዝባችንን ህልውና ለማረጋገጥ ሁሉም ከመከላካያ ሠራዊት፣ ከልዩ ኀይል፣ ከሚሊሻና ከፋኖ ጎን ተሠልፎ መፋለም እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ አንድነታችን ተጠቅመን ወራሪውንና ተሥፋፊውን ኀይል መመከት ተገቢ ነውም ብለዋል፡፡
“ያገኛችሁትን ሥልጠና ተጠቅማችሁ ኀላፊነታችሁን በመወጣ የሀገራችሁ የቁርጥ ቀን ልጆቿ መሆናችሁን ማረጋገጥ ይጠበቅባችኋል” ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ዳኝነት አማረ ከአባት የመጣውን ጀግንነት አና ወኔ ተረክባችሁ ያባቶቻችንን ድል ለመድገም ወታደራዊ ሥልጠና አግኝታችሁ የተመረቃችሁ ምሩቃን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡ የአባቶቻችንን የድል ታሪክ እንደምትደግሙ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለዘመናት ሉዓላዊነቷን አስከብራ የኖረች ሀገር ናት፣ ይኼን ሉዓላዊነት ለመድፈር በርካቶች ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርጉም በአባቶቻችን ተጋድሎ አልተሳካላቸውም፤ ወደ ፊትም አለይሳካላቸውም ነው ያሉት፡፡
አሸባሪው የትህነግ ቡድን ለማሸነፍ በተባበረ ክንድ በአንድነት መኾኑን አጥብቃችሁ ልትረዱት ይገባልም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m