“ዓባይ ሞልቶ ድልድዩን ሲያለብሰው ፣ ምን ጥልቅ አረገው ዋኝቶ የማይወጣ ሰው።”

770

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 02 /2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከዋሻ ውስጥ የነበረ፣ አፉ ብቻ የቀረ፣ በሁሉም ነገር የተቸገረ ኀይል ተስፋ ሳይቆርጥ ሲመታህ፣ ክብርህን ሲነካህ፣ ከደረጃህ ሊያወርድህ ሲውተረተር ያለውን ንጠቀው፣ ተስፋውን አሳጠው። በባርነት እንኳን እንድትኖር ለማይፈቅድልህ፣ የሁልጊዜ ጠላትህ፣ ሲመጣ የአባቶችህን ክንድ አንሳበት፣ የሚፋጀው ፊትህን አዙርበት፣ እያነጣጠርክ ተኩስበት፣ ምድርህን እሳት አርግበት። እንከን የሌለበት፣ ማሸነፍ እንጂ መሸነፍ የማይታወቅበት ታላቅ ታሪክ ይዘህ በአንተ ዘመን የሚመጣውን ትንሽ ቡድን በነዲድህ አቃጥለው። ስምህ ብቻ የሚያስፈራቸው፣ ድምፅህ ብቻ የሚያስደነግጣቸው፣ ክንድህን ስታነሳ ደግሞ እንዳልነበር የምታደርጋቸው አንተ ጀግና ነህ።

በልክህ የተሠራ፣ በእኩያህ የሚጠራ ኀይል የለም። ግርማው የሚያስፈራ፣ ጀግንነቱ የሚያኮራ፣ የጨለመውን የሚያበራ፣ የልቡን የሚሠራ ነው አማራ። ጠላቶችህ የሚበዙት፣ በየዋሻው የሚማማሉት፣ ስለሚፈሩህ ነው። አሸናፊ ስለሆንክ ከአንተ ላይ አሸናፊነትን ለመውሰድ ይጥራሉ፣ ስትይዛቸው የውጪ አጋዥ ይጠራሉ፣ ስትለቃቸው ማነው ወንዱ ይላሉ። ችለው አይገፉህም፣ ሆኖላቸው አያሸንፉህም፣ አንተ በግርማህ፣ በጀግንነትህ፣ በአርቆ አሳቢነትህ፣ በብልሃትህ ሁሉ ከእነርሱ ትበልጣለህ። አማራ አሸናፊ፣ መከራን በፅናት አላፊ፣ ለሀገር ጉዳይ ከፊት ተሰላፊ ነው።

ለሀገር ፍቅርና ለወገን ክብር ሲል ደሙን፣ አጥንቱን፣ ሕይወቱን ይሰጣል፣ ለኢትዮጵያ የሚሳሳው አንዳች ነገር ስለሌለው። አማራን እንኳንስ ከዋሻ ውስጥ በመከራ የወጣ ይልቅና ከሮም የመጣ ወራሪ እንኳን አልቻለውም፤ ክንዱን ቀምሶ፣ በመጣበት ተመልሶ ነው የሄደው።

“ተከዜ ገዳይ ከቁልቁለቱ
ራያም ገዳይ ከቁልቁለቱ
ተመልከት ብሎ ደፋው ባናቱ’’ እያለ የውጪን ወራሪ ከውስጥ ተቀጣሪ ጋር አዳብሎ የወቃ፣ በደሙ ያጠቃ ጀግና ሕዝብ ነው። እንደ ሰው አንደበት ቢኖራቸው፣ የሚመዘግቡበት ብራና ቢሰጣቸው፣ በዘመናት ቅብብሎሽ የታየውን ቢጠይቋቸው የአማራን ጀግንነት፣ አንድነት እና ቆራጥነት የኢትዮጵያ ሠንሰለታማ ተራራዎች በመሰከሩ ነበር።

ፋኖ ከተነሳ፣ ነፍጡን ካነሳ፣ አፈሙዙን ከወለወለ የሚያቆመው ጠላት አይገኝም። ቢሻው ደረቱን፣ ቢሻውም ባቱን እየመታ ልኩን ይሰጠዋል። ትህነግ አማራን ለመውጋት፣ አንገቱን ለማስደፋት ቢሻውም ለማጥፋት ቆርጦ ከተነሳ ዓመታት አልፈዋል። ከበረሃ ጎትቶ ቤተመንግሥት አስገብቶት፣ ዙፋን ላይ አስቀምጦት፣ ካባ አጎናፅፎት፣ ያላየውን አሳይቶት ሲያበቃ እሱ ግን ያጎረሰውን፣ ያለበሰውን፣ ወግ ማዕረግ ያሳየውን ጀግና ሕዝብ ሊገድል፣ ሊያሰቃየው ጀመረ።

ለሀገርና ለፍቅር ሲል ከአሁን አሁን ልብ ይገዛል ብሎ ቢጠብቀውም በክፋቱና በማን አለብኝነቱ ቀጠለበት። በአሸባሪው ትህነግ ክፉ ሥራ የተበሳጨው አማራ መርቶ ዙፋን ላይ እንደሰቀለው፣ ጎትቶ ወደ ጉድጓድ ጨመረው። በጉድጓድ ሥር የኖረው ትህነግ ትንሽ ፋታ ሲያገኝ አማራን ይወጋ ጀምሯል። አሁን ግን ዳግም መንገድ የሚጠርግላቸው፣ ዙፋን ላይ የሚያስቀምጣቸው፣ ወደ ቤተመንግሥት የሚወስዳቸውና የሚሸኛቸው አማራ የለም። ይልቅስ ባገኘበት ሁሉ ይወጋቸዋል፤ እያፈነ ወደ ወዲያኛው ዓለም ይሸኛቸዋል እንጂ። ሁለተኛ የሚሳሳት፣ ሀገሩንና ክብሩን አሳልፎ ለወሮ በላ የሚሰጥ የለም። ክተት ተብሏል፤ በየአካባቢው ከትቷል።
“መተኮስ ነው እንጂ እንዲቀር እንዲቀር
ከባልንጀራ ፊት አንገት ከማቀርቀር’’ እንዳለች ጃሎ ባይዋ አሁን ላይ ባሻገር እንዲቀር መተኮስ፣ ምሽጉን ማፍረስ፣ ሕልውናውን መደምሰስ ግድ ይላል። ለዚያም አማራ ተማምሎ እየተኮሰ ነው።

የአሸባሪው ትህነግ እድሜ ረጅም አይሆንም፣ በኋላ ላይ ጀግኖች ተዋግተው አሸንፈው ሲመለሱ ከቤት ቆይቶ አንገት ከማቀርቀር፣ ወደ ጠላት ሰፈር መትመም ግድ ነው። ወደፊት ገስግስ፣ በአሻገር መልስ። አማራ ማለት ጀግንነቱ ከምድር ተራራዎች የበለጠ፣ ታሪኩ ከፍ ብሎ የተቀመጠ፣ ዝናው በዓለም የናኘ፣ በመከራ ቀን ከፊት የተገኘ፣ እውነት ተናጋሪ፣ ታሪክ ሠሪ፣ ለፍትሕ ተከራካሪ፣ በጥበብ መንገድ የተራመደ፣ በጥበብ ያራመደ፣ ከፈጣሪው ጋር የተዋደደ፣ ሕዝብ እንዳይራብ አራሽ፣ ሀገር እንዳትደፈር ተኳሽ፣ ገፍቶ የመጣን መላሽ፣ ወደ ከፍታ ገስጋሽ፣ ጀግናን አንጋሽ፣ ጠላትን ደምሳሽ ነው። አማራ ከጣላቶቹ ስለሚልቅባቸው፣ በሁሉም ስለሚበልጣቸው፣ ሊበትኑት ይሞክራሉ፣ ሊያጠቁት ይዘምታሉ ዳሩ ከምክርም በላይ ነውና ሊያጠፉት የመጡትን ያጠፋቸዋል። አንገቱን ሊያስደፉት የመጡትን አንገታቸውን ያስደፋቸዋል። ከክብራቸውም ያወርዳቸዋል።

አሸባሪው ትህነግ አማራን ስለሚፈራውና በጀግንነት ስለሚበልጠው ከመነሻው እስከ መድረሻው ድረስ አማራን ለመጉዳት ያልመከረበት ቀን አልነበረም። ቀናት አልፈው ዓመታት ሲተካኩ ገዳዮች እያለቁ፣ አማራው እያሸነፈ ቀጥለዋል። የትህነግ ጀሌዎችም በየድንጋዩ ሥር ሬሳ ሆነው ቀርተዋል። ያሉትም ተከበው እየተመቱ ነው።
“ዓባይ ሞልቶ ድልድዩን ሲያለብሰው
ምን ጥልቅ አረገው ዋኝቶ የማይወጣ ሰው’’ አማራ ሞልቷል። ማዕበል ኾኗል። ጠላቱን ይወስዳል፣ ደፍሮት የገባን ይጠርጋል፣ ትህነግ ከሞላው ውኃ ውስጥ ገብታለች። ዋኝታ ከማትወጣው ሙላት ተዘፍቃለች። ወደፊትም ወደኋላም አትዋኝም። አማራጯ ተጠርጋ መሄድ ወይም ከደለል ጋር መቀላቀል ብቻ ነው። ዋኝተው ላይሻገሩት፣ ገድበው ላያስቆሙት፣ ችለው ላይወጡበት፣ ተራመድው ላያልፉበት ገብተዋል።

እንደ ማዕበል የወጣው አማራም ከመካከሉ የገባውን ጠላት እንደ አሻው ያገላብጣል፣ እያገላበጠም ነው፣ ገፋፍቶ ማዕበል ውስጥ የጨመራቸው፣ ለእልቂት የዳረጋቸው ኀይልም ምን እንደሚመልስ መላው ይጠፋዋል። አማራን እና አብዝቶ የሚወዳትን ሀገሩን የነኩት ሁሉ በማዕበል ተጠርገዋል፣ ከዙፋናቸው ወርደዋል፣ ከግርማቸው ተዋርደዋል፣ ከኀያልነታቸው ተንኮታኩተዋል፣ በዓለም ፊት አፍረዋል፣ አደባባዮቻቸው ሁሉ በሀዘን ተውጠዋል። ዘመናቸው ተጠናቅቋል፣ ሠራዊታቸው አልቋል።
“ግፋ በለው ይገፋል በግዱ
ያገሩ ጎዳና ሲጠፋው መንገዱ’’ ወደፊት ግፋ በለው፣ አፈሙዝህ ሲገርፈው፣ መውጫ መግቢያ ቀዳዳ ሲጠፋው፣ ግራው ሲገባው ወዶ ሳይሆን ተገድዶ ይገፋል። ትህነግ አፈሩን አራግፎ ማሸነፍ ሲያስብ አንተ ግን ከነክብርህና ከነሞገስህ ያለህ ነህና ያራገፈውን አፈር ዳግም መልስበት፣ በቀቢፀ ተስፋ የሚመለካታትን ጀንበር ለዘላለም አጥልቅበት፣ ለውሸት ወሬዎች ጆሮህን ዝጋበት፣ አሸንፈው፣ የተገፋኸውና ለፍትሕ የምትታገለው አንተ መኾንህን እርግጠኛ ሁን።

በታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“እስከ ሕይወት መስዋእትነት ዋጋ በመክፈል አሸባሪውን የትህነግ ቡድን ለመደምሰስ ዝግጁ ነን” የደባርቅ ከተማ ወጣቶች
Next article“ዝምተኛ ጀግኒት” ሴት የአማራ ፋኖ