
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 01/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ነሐሴ 1/2008 ዓ.ም ከስናይፐር እስከ ክላሽንኮብ፤ ከአስለቃሽ ጭስ እስከ እጅ ቦንብ የታጠቁ የአጋዚ ቅልብ ወታደሮች የባሕር ዳር ከተማን ዋና ዋና መስመሮች ገና በጠዋቱ ነበር የወረሩት፡፡ ከተማዋ ከማለዳው የአእዋፍት ማራኪ ሕብረ ዝማሬ ቀጥሎ የእናቶችን መራር ዋይታ ታስተናግዳለች ብሎ ያሰበ ባይኖርም ድባቡ ግን ደስ አይልም ነበር፡፡ በባዶ እጃቸው እና በሙሉ ልባቸው ወደ አደባባይ የሚወጡት ወጣቶች ቁጥር ቀስ በቀስ በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ እየደመቀ መጥቷል፡፡
ኢትዮጵያዊ ጀግንነትና ጨዋነት አብዝቶ የሚስተዋልባቸው ወጣቶቹ እስካልነኳቸው ድረስ ሐሳባቸውን በጨዋ ደንብ እየገለጹ ፍትሕ፣ ማንነት እና ዴሞክራሲ ይስፈን ሲሉ ድምጻቸውን አሰሙ፡፡ ከሐሳብ ልዩነት የተናጠቡት፣ ከዴሞክራሲያዊ ውይይት ጋር የማይተዋወቁት እና ፍርሃት ለእርምጃ የሚዳርጋቸው ትህነጋውያን ስልጡን አስተሳሰብ አይመቻቸውምና ሰላማዊ የነበረውን ሰልፍ ወደሁከት ቀየሩት፡፡ በርካቶች ህይዎታቸው አለፈ፣ በርካቶች አካላቸው ጎደለ እንዲሁም የበዛውን ወጣት ለእስርና እንግልት ዳረጉት፡፡
ፍትሕ በራቀባት እና አምባገነኖች በናኙባት ምድር ምናልባትም የነፃነት ታጋዮች ያልፉ ይሆናል እንጂ ትግላቸው ፈጽሞ አይኮላሽምና ትህነግ ከቤተ መንግስት ወርዳ ጫካ እስክትገባ የወሰደው ጊዜ የበዛ አልነበረም፡፡
ዛሬ ያ የግፍና መከራ ዘመን አልፎ እነዚያን “ወልቃይት ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” ያሉ የነፃነት ቀንዲሎች በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሁመራ ከተማ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ሲታሰቡ ውለዋል፡፡
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሸተ ደምለው ትግላችሁ በምክንያት የተጀመረ ስለነበር ያለምክንያት አልቆመም ነው ያሉት፡፡
“ወልቃይት” እያሉ ህይወታቸው ያለፈ ወጣቶች ጥያቄያቸው ማንነት ነበርና በትግላቸው ማንነታችን ተመልሷል ብለዋል፡፡
አሸባሪው የትህነግ ቡድን ከአለፈ ስህተቱ ሳይማር በዳግም ወረራ ወደ አማራ ግዛቶች አልፎ ገባ ሲባል ይሰማል ያሉት አቶ አሸተ “ይገባ ይሆናል፤ ነገር ግን መልሶ አለመውጣቱን ግን በእርግጠኝነት እነግራችኋለሁ” ሲሉ ትግሉ የሕልውና መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚያ ድቅድቅ ጨለማ ስናይፐር እና ቦንብ የታጠቀን ኀይል በባዶ እጁ ታግሎ የጣለ የአማራ ሕዝብ አሁን ያለው ወቅታዊ ቁመና ለሽንፈት የሚዳርግ አለመሆኑን ማመን ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን አሉ ዋና አስተዳዳሪው “ሙት ይዞ ይሞታል ነውና” አላስፈላጊ መስዋእትነት ላለመክፈል አካባቢን ነቅቶ መጠበቅ ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
አሸባሪው የትህነግ ቡድን እድል ካገኘ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ አይተኛም ያለው የነሐሴ 1 ጉዞ አስተባባሪ ኃይሌ አድማሱ “የአማራ ሕዝብ መራር ተጋድሎ በጥንተ ጠላቱ አሸባሪው ትህነግ መቃብር ላይ የመጨረሻውን ድል ያስመዘግባል” ብሏል።
ወጣቱ ትናንት የጀመረው ትግል ዛሬ የድል ብስራት ጮራ አሳየ እንጂ አልተጠናቀቀም ያሉት ወጣቶቹ ትግሉን ሕዝባዊ መሰረት አስይዞ በድል ለማጠናቀቅ ባለአምስት ነጥቦች የትግል አቋሞችን አስተላልፈዋል፡፡
አንድነትን ማጠናከር የአማራ ሕዝብ የመጀመሪያው ተልዕኮ ነው ያሉት ወጣቶቹ ከአሸባሪው ትህነግ ከውስጥ ራስን ማጽዳት ሁለተኛው የትግል ስልት ነው ብለዋል፡፡
የአማራ የማንነት ጥያቄዎች በልጆቹ መስዋእትነት ተረጋግጧል ያሉት ወጣቶቹ በዚህ ዙሪያ የሚታዩ የውጭ ኀይሎች ጣልቃ ገብነት ተቀባይነት እንደማይኖረውም አረጋግጠዋል፡፡
የሐሰት መረጃ ሥርጭት እና የፕሮፖጋንዳ ጦርነት አሸባሪው ትህነግ ያለፈበት ግን ያላሻሻለው ቁሞ ቀር አስተሳሰብ መሆኑን አውስተው፤ ለዚህም አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት ወጣቱ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ ይህንን የሕልውና ዘመቻ በሚመለከት ያለው ብቸኛ አማራጭ ማሸነፍ ብቻ መሆኑንም ወጣቶቹ ገልጸዋል፡፡
አማራ በታሪኩ ሽንፈትን አያውቅም ያሉት ወጣቶቹ ዛሬ ያለው ወጣት የሕልውና ዘመቻውን አሸንፎ የአባቶቹን ታሪክ እንዲያድስ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከሁመራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
