
“ኢትዮጵያ በሱዳን ድንበር በኩል ርዳታ እንዲገባ ብቻ ሳይሆን ለጊዜው ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንዳይደረግ የመዝጋት ሉዓላዊ መብቷ የተጠበቀ ነው” በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 30/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በትግራይ ልሂቃን ዘንድ የጀርመኑ ናዚ ፓርቲ የወለደው አይነት ብሔርተኝነት እየተስተዋለ ነው፡፡ ናዚ አውሮፓን ለመከራ እንደዳረገው ታሪክ ይመሰክራል፡፡ አሸባሪው ትህነግም ኢትዮጵያን ለማጥፋት ቆርጦ ተነስቷል፡፡
አሸባሪው የትህነግ ቡድን ከአደረጃጀቱ ጀምሮ በኢትዮጵያ በብሔራዊ ጥቅም ላይ ሲቆምር ቆይቷል፡፡ የሚጠላትን ሀገር ሲመራ በነበረባቸው ጊዜያትም ኢትዮጵያን በዝብዟል፣ ሕዝቦቿንም በድሏል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብን የእኩልነት ጥያቄ ባለመቀበሉ ከዘመናት የግፍ አገዛዝ በኋላ ከመንበረ ስልጣኑ ወርዶ በቀበሮ ጉድጓድ መሽጓል፡፡ አሁን ‹ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እንገባለን› በማለት የተዳከመች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
መንግሥት ለተኩስ አቁም ውሳኔው ታማኝ ቢሆንም አንዳንድ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሀቁን ለመቀበል አልፈለጉም፡፡ ገለልተኛነትና ፍትሐዊነት በእጅጉ የሚጠበቅባቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀሩ የአሸባሪውን ቡድን የሐሰት ፕሮፖጋንዳ መደገፋቸው ደባ መኖሩን ያሳያል፡፡
በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ሀሳቡ ደስታ እንዳሉት በፕሮፖጋንዳ ዘመቻ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር እየተሞከረ ነው፡፡ በተለይ አሸባሪው ቡድን የሚያቀናብራቸውን የውሸት መረጃዎች በተቀናጀ መልኩ እየተቀባበሉት ይገኛሉ፡፡ ዘላቂ ሰላም ከማስፈን ይልቅ የአሸባሪውን ሕልውና አራዝሞ የግል ፍላጎትና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ያለመ መሆኑንም አንስተዋል፡፡ ይህም በሀገሪቱ ላይ ኢ-ፍትሐዊ ጫና እንዲፈጠር ያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ሀቁን በማስረዳት አካሄዱን መቀልበስ አለበት ብለዋል፡፡
አዲስ አበባ ከብራሰልስና ከኒዮርክ ቀጥላ ሦስተኛዋ የዲፕሎማሲ ከተማ መሆኗ ይታወቃል፡፡ ይህም ዲፕሎማት ማሰማራት ሳያስፈልግ ሀገር ውስጥ ላሉ አምባሳደሮች ማብራሪያ በመስጠት ሀገራት በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ በጠላት ብቻ የተከበበች አይደለችም፡፡ በርካታ ወዳጅ ሀገራትም አሏት፡፡ በጸጥታው ምክር ቤት ተጽዕኖ ለማሳደር የቀረቡ የውሳኔ ሀሳቦች ውድቅ እንዲደረጉ የወዳጅ ሀገራት ሚና የጎላ መሆኑም ለዚህ ማሳያ ነው፡፡
ጠንካራ የዲፕሎማሲያዊ ሥራ ለኢትዮጵያ መንግሥት ወሳኝ ተግባር መሆን አለበት ያሉት መምህሩ ወዳጅ ሀገራትን በማብዛት ጫናዎችን መቀነስ እንደሚቻል ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለተጎጂዎች ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርስ የማድረግና ምቹ ሁኔታን የመፍጠር ግዴታ እንዳለባት ይታወቃል፡፡ ይህ ማለት ግን ድጋፍ አድራጊዎች ያሻቸውን ያደርጋሉ ማለት አይደለም፡፡ ምንም እንኳን ተቀባይነት ባያገኝም ከሰሞኑ በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ በሚል ሰበብ አንዳንድ ምዕራባዊያንና ተቋሞቻቸው በወልቃይት ጠገዴ በኩል መተላለፊያ ኮሪደር እንዲከፈት ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ ይህ የሀገሪቱን የማይገሰስ ሉዓላዊ መብት የተጋፋ በመሆኑ ፈጽሞ ለድርድር መቅረብ የለበትም ብለዋል፡፡
በአንድ በኩል በተከፈተው በር በቂ ርዳታ ሳያስገቡ ሌላ ጥያቄ ማንሳቱ ተገቢነት የለውም፡፡ በሌላ በኩል በኤርትራ በኩል የአሰብ ወደብ ቅርብ ሆኖ ሳለ በሱዳን ድንበር የተፈለገበትን ምክንያት ማጤን ይገባል ነው ያሉት፡፡ አሸባሪው ትህነግ ከዚህ በፊት ሲያደርግ እንደነበረው የጦር መሳሪያ ለማስገባትና የሚቀርበውን ድጋፍ አውጥቶ ለመሸጥ እንደሚሆን በመጥቀስም ከውጪ የሚገባ ርዳታን በደንብ መፈተሸ ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በድንበር ውዝግብና እና በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ከሱዳን ጋር ዲፕሎማሲያዊ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቷ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንጻር በሱዳን ድንበር በኩል ርዳታ እንዲገባ ብቻ ሳይሆን ለጊዜው ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንዳይደረግ የመዝጋት ሉዓላዊ መብቷ የተጠበቀ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ጠንካራ አቋም ሊይዝበት ይገባልም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
