
‹‹የምዕራባውያን ሴራ በኢትዮጵያ ላይ ሲገለጥ››
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 30/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሜሪካ በየሀገራቱ ጣልቃ በመግባት የራሷን ፍላጎት ለመጫን በርካታ ሴራዎችን ስተገብር ቆይታለች፡፡ ለአብነትም በኢራቅ፣ በሊቢያ፣ በየመን፣ በኮሪያ፣ በቬትናም፣ በላቲን አሜሪካ በሌሎችም ሀገራት ጣልቃ በመግባት የተገበረችው ሴራ የሚታወቅ ነው፡፡
በቅርቡም ምዕራባውያን ሶሪያን በ‹‹ባስማ›› ፕሮጀክት እንዴት እንዳፈረሷት ጂኦፖለቲክስ ፕርስ የተባለው ድርጅት ይፋ አድርጓል፡፡ ባስማ ፕሮጀክት ሶሪያን ለማፍረስ በምዕራባውያን የተተገበረ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት በእርዳታ ስም ጥንታዊቷን ሶሪያ አሁን ካለችበት ደረጃ እንዳደረሳት ጂኦፖለቲክስ አስነብቧል፡፡
ምእራባውያን ሀገሪቷን የማፍረስ ሥራቸውን አንድ ብለው የጀመሩት ‹‹በጦርነቱ የተጎዱት ሶሪያውያን ድጋፍ ለማድረግ›› በሚል የሽፋን ስም ነበር፡፡ ይሁን እንጅ እነዚህ ኀይሎች ወደ ሀገሪቱ የገቡት ሰብዓዊነትን ተላብሰው ሳይኾን በሰብዓዊነት ካባ የጦር መሳሪያ ጭነው ነው፡፡ ምዕራባውያን ሶሪያን በባስማ ፕሮጀክት እንዳፈረሷት ኢትዮጵያንም ለማፍረስ አንድ ፕሮጀክት ነድፈው እየተንቀሳቀሱ መኾኑን ጅኦፖለቲክስ ፕረስ የተባለ ድርጅት አስቀምጧል፡፡
ፕሮጀክቱም ‹‹ኮማንድ ኤንድ ኮንትሮል ፊውዥን ሴንተር- C2FC – ›› የሚል ስያሜ እንዳለው ነው ድርጅቱ ይፋ ያደረገው፡፡ ድርጅቱ ይፋ እንዳደረገው ትህነግ በሰሜን ዕዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በፈጸመ በሳምንቱ ሪፖርት ለተመረጡ የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እንዲቀርብላቸው ተደረገ፡፡ የሥራ ኀላፊዎቹ በኢትዮጵያ ጉዳይ የቀረበውን ባለ ሰባት ገጽ ሪፖርት ላይ ከመከሩ በኋላ ለአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ቀረበ፡፡ ምክር ቤቱ በፌዴራል መንግሥት እና በትህነግ መካከል የተፈጠረውን ጦርነት ከዳሰሰ በኋላ ጉዳዩ ከአፍሪካ ቀንድ አልፎ ለኀያላን ሀገራት ሁለት ስጋቶችን እንደሚፈጥር አስቀመጠ፡፡ አንደኛው ስጋት አውሮፓ በስደተኞች ሊጥለቀለቅ እንደሚችል የሚያመላክት ሲኾን ሁለተኛው ደግሞ በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያ እና በኤርትራ መሪዎች መካከል የተፈጠረው አዲስ ህብረት ለምእራባውያን አደገኛ መኾኑን ነው ያስቀመጠው፡፡
ግጭቱ ከኢትዮጵያ አልፎ ወደ ባህረ ሰላጤው ሀገራትም እንደሚሸጋገር እና ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የገፈቱ ቀማሽ ሊሆኑ እንደሚችሉ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ሀገሪቱ እንድትበታተን ተስማምተውበታል፡፡ ስትፈርስ ግን ፈጽሞ ቀጣናውን በማይረብሽ በሰላማዊ መንገድ መኾን እንዳለበት ምክር ቤቱ ተወያይቷል፡፡
ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኀይሎች ማዕከላዊ መንግሥትን በኀይል አሸንፈው ቢገነጠሉ እንደ ሶማሌላንድ ዓለም አቀፍ ዕውቅና የሌላቸው ግዛት ከመኾን ባለፈ ነፃ ሀገር ሊኾኑ ስለማይችሉ በስልት እንደ ዩጎዝላቪያ መበተን እንደሚገባ አስቀምጧል፡፡ በዚህም የፌዴራል መንግሥት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ በማሳደር ትህነግን ጨምሮ ሁሉም ኀይሎች የሚሳተፉበት ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት እንዲቋቋም ማድረግ ነው፡፡ በዚህም መሰረት በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን መብት ተጠቅመው ክልሎች የመገንጠል ጥያቄ እንዲያነሱ በማድረግ በሕዝበ ውሳኔ ሀገሪቱን ማፍረስ እንደሚገባ አስቀምጧል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ፕሮጀክቱን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀስ ከኾነ ደግሞ በጥንቃቄ እንዲወገድ ማድረግ በአማራጭነት ተቀምጧል፡፡ በትግራይ ክልል የጦር ወንጀል እንደተፈጸመ በማስመሰል እንደ ዩጎዝላቪያው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ስሎቮዳን ሚሎሶቪች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን በሰብዓዊ ጥሰት ወንጀል በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በመክሰስ ሀገሪቱን መበታተን አስፈላጊ እንደኾነ ውይይት ተደርጎበታል ብሏል፡፡
አፈጻጸሙን ዕውን ለማድረግም መቀመጫውን በኬኒያ ያደረገ እንደ ሲ.ኤን.ኤን እና ሮይተርስ የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት እና የተለያዩ ድርጅቶች ከኬኒያ መከላከያ እና ደኅንነት ቢሮ ጋር በጥምረት እንዲሠሩም ተደርጓል፡፡ እነዚህ አካላት ኢትየጵያን የሚመለከቱ መረጃዎች ከማኅበራዊ ሚዲያ፣ ከትህነግ ካድሬዎች፣ ከትግራይ ዲያስፖራ አባላት፣ ከሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች በምንጭነት በመሰብሰብ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ሰፊ ፕሮፖጋንዳ መስራት እንደሚገባ አስቀምጧል፡፡
የትህነግን የፖለቲካ እና ወታደራዊ አጋሮችን የማኀበራዊ ሚዲያ ገጽ የማስተዋወቅ ሥራ እንዲሠራ ተደርጓል፡፡ በኦሮሚያ ክልልም አለመረጋጋት በመፍጠር ሀገሪቱን ቀውስ ውስጥ እንድትገባ ማድረግ ሌላው የዚህ ቡድን ሥራ ነው፡፡ ቡድኑ ስለ አንድነት የሚሰብኩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በማገድ እና የትህነግን አስተሳሰብ የሚያንጸባርቁትን ደግሞ ማበረታታት አንዱ ማፍረሻ ስልት እንደኾነ አስቀምጧል፡፡
እንደ ጌታቸው ረዳ የመሳሰሉ የትዊተር ገጾችን በአጭር ጊዜ የባለቤትነት እውቅና የመስጠት እና የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብሏል፡፡ የተለያዩ የመረጃ መቆጣጠሪያ ስልቶችን በመጠቀም ትህነግን የሚያወድሱ መረጃዎችን በቀላሉ ለበርካታ ሰዎች እንዲደርሱ የማድረግ ሥራ እየሠሩ መኾኑንም አስቀምጧል፡፡
የአሜሪካው ስቴት ዲፓርትመንት፣ ረድኤት ድርጅቶች፣ የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎች የሚዲያ ተቋማት ሀገሪቱን ለማፍረስ በተቀናጀ መንገድ እየሠሩ መኾኑን አስቀምጧል፡፡ ይህንን መረጃ ሊያጠናክርልን የሚችል ተጨማሪ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ታደሰ በቀለ ‹ከቀዳማዊ እስከ ቀዳማዊ› በሚለው መጽሐፋቸው እንግሊዞች ኢትዮጵያን ‹‹የትግሬ መንግሥት፣ የአማራ መንግሥት እና የኦሮሞ መንግሥት›› በሚል፣ ጣሊያን ደግሞ ‹‹የኤርትራ መንግሥት፣ የአዲስ አበባ መንግሥት፣ የኦሮሞ መንግሥት፣ የአማራ መንግሥት፣ የሲዳማ እና የሱማሌ መንግሥት እና የሀረር መንግሥት›› በሚል ወደ ተለያዩ ሀገራት እንድትበታተን ይሠሩ እንደነበር ማንሳት ይቻላል፡፡
በ1972 ሄነሪ ኪሲንገር የተባለው አሜሪካዊም “ኢትዮጵያን ለማዳከም እና ለመበታተን ሁሌም በጦርነት ማባዘን ይገባል›› የሚል ፖሊሲ ይፋ አድርጓል፡፡
በቅርቡም ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ የግብጽን እና የሱዳንን ሀሳብ እንድትቀበል አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን ያሳዩት ጣልቃ ገብነትን በማሳያነት ማንሳት ይቻላል፡፡
በዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
