“እንደቀድሞው ሁሉ የሚወደን ሰይፉን ይዞ ይከተለን” የዳንሻ ከተማ ነዋሪዎች

185
“እንደቀድሞው ሁሉ የሚወደን ሰይፉን ይዞ ይከተለን” የዳንሻ ከተማ ነዋሪዎች
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 30/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአሸባሪው ትህነግ ቡድን የስልጣን ዘመን አከርካሪው የተሰበረው፣ የፈላጭ ቆራጭነት እርካብ የሾለከው እና የኢትዮጵያዊያን የነፃነት ጎህ ብቅ ያለው እዚህ አካባቢ ነበር፡፡ ከወትሮው ስለነፃነታቸው እና ስለማንነታቸው በድንጋይ ሳይቀር የተፋለሙት የዳንሻ ወጣቶች አሸባሪው ትህነግ በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን አስነዋሪ ድርጊት ዳንሻ አካባቢ ባለው የሰሜን ዕዝ አምስተኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር መምሪያ ላይ ሊደመድም እና አልፎ ወደጎንደር ሊያቀና ሲል ምኞቱ ሁሉ ህልም መሆኑ የገባው እዚህ ዳንሻ ላይ አይቀጡ ቅጣት ሲያገኝ ነበር፡፡
“በትህነግ የግፍ አገዛዝ ዘመን መሬቱን እንጂ እናንተን አንፈልጋችሁም” ተብለናል የሚሉት የአካባቢው ነዋሪዎች የግፍ ጽዋ ሞልቶ ሲፈስስ በደላቸው እጃችን ላይ ጣላቸውና የእጃቸውን ከፈልናቸው ይላሉ የጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም መጨረሻ ቀናትን ጀብዱ እያስታወሱ፡፡ አሸባሪው ትህነግ በአገዛዝ ዘመኑ በርካቶቹን የአካባቢውን ተወላጆች የት እንዳደረሷቸው አይታወቅም፣ የሀገር አውራ የሚባሉትንም ነገ ስለትናንቱ እንዳይመሰክሩ ሲባል በግፍ ተገድለዋል፤ የቻሉት ከአካባቢው ፈቀቅ ብለው ጊዜና ቦታ ሲጠብቁ ቆይተዋል፡፡
ይህን ሁሉ ግፍ ያሳለፈ አካባቢ ጀግና እንደ እርግማን ይመክንበታል ቢባልም እሱ ግን አልሆነም ይላሉ ነዋሪዎቹ፡፡ ያለመስዋእትነት ጀግንነት የለምና በክፉ ጊዜ ብዙ ጀግኖች እንዳሉን አይተናል ነው ያሉት፡፡ ከበዛ ግፍና መከራ ማክተም በኋላ ነፃነታቸውን ካጣጣሙ ገና ዘጠኝ ወራትን ብቻ ያስቆጠሩት የአካባቢው ነዋሪዎች የሕልውና ጦርነት ውስጥ ስለመሆናቸው ብዥታ የለባቸውም፡፡ አካባቢያቸውን ነቅተው ይጠብቃሉ፤ የሚጠበቅባቸውንም ሁሉ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች እና ወጣቶቹ የአሸባሪውን ቡድን አቅም እናውቃለን፤ ቡድኑ ተከዜን ከተሻገረም እንደማይመለስም ተናግረዋል፡፡ “እንደቀድሞው ሁሉ የሚወደን ቢኖር ሰይፉን ይዞ ይከተለን” ያሉት የዳንሻ ከተማ ነዋሪዎች አሸባሪው ቡድን የሽብር ጥቃት በሚፈጽምበት የትኛውም አካባቢ ዘምተው ለመፋለም ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች ለህልውና ዘመቻው ከኢትዮጵያዊያን የሚጠበቀው በርካታ ነገር ነውም ብለዋል፡፡ መዝመት የሚችለው ወጣት የአሸባሪውን ዱካ እየተከታተለ በሁሉም አቅጣጫ በመዝመት የአሸባሪውን ቡድን ግብዓተ መሬት ማፍጠን፤ ሌሎቹ ደግሞ ደጀን ሆነው በስንቅ እና ትጥቅ አቅርቦት እንዲደግፉ ጠይቀዋል፡፡
ወጣቶቹ በፕሮፖጋንዳ የሚፈርስም ሆነ የሚገነባ ሀገር የለም፤ ኢትዮጵያም በፕሮፖጋንዳ የምትናጥበት ዘመን አክትሟል ብለዋል፡፡ የአሸባሪው ቡድን ርዝራዦች በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ከሚያናፍሱት የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በመራቅ ለኢትዮጵያ እውነት እና አሸናፊነት የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎችን መቀላቀል ተገቢ ነውም ሲሉ ይመክራሉ፡፡ አሸባሪው የትህነግ ቅሪት በሌሎች የአማራ ክልል አካባቢዎች እንደሚያደርገው የሽብር ተግባር ሁሉ በዚህ አካባቢም ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጓል የሚሉት የአካባቢው ነዋሪዎች በመጣበት መንገድ ምላሽ ተሰጥቶታል ነው ያሉት፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት በመቆም አሸባሪውን ትህነግ መደምሰስ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
የውጭ ኀይሎችን የበዛ ጣልቃ ገብነት እና የተንሸዋረረ እይታ ተቋቁመን ጠንካራ ሀገር መገንባት የምንችለው በአንድ መቆም ስንችል ነውም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleኢትዮጵያዊያን ሉዓላዊነታቸውን የሚፈታተኑ ድርጊቶችን በምንም ሁኔታ እንደማይቀበሉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ፡፡
Next article“አሸባሪው ህወሓት ከ“አልቃይዳ እና አይኤስ” የበለጠ የሽብር ድርጊትን ፈጽሟል” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ