ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ምዕራባውያን የሚመጡበት ምክንያት ከኢትዮጵያ እና ሕዝቦቿ ፍላጎት ውጭ ከኾነ ሕዝብ እና መንግሥት ድርጊታቸውን ሊቃወሙ እንደሚገባ ምሁራን አስገነዘቡ፡፡

192

ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ምዕራባውያን የሚመጡበት ምክንያት ከኢትዮጵያ እና ሕዝቦቿ ፍላጎት ውጭ ከኾነ ሕዝብ እና መንግሥት ድርጊታቸውን ሊቃወሙ እንደሚገባ ምሁራን አስገነዘቡ፡፡

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 29/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፍ ተቋማት በተለያዬ አግባብ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ይዘውት የሚመጡት አጀንዳ ግልጽ እና የታወቀ ሊሆን ይገባል፤ ነገር ግን ይዘውት የመጡትን አጀንዳ ወደ ጎን በመተው ድብቅ አጀንዳቸውን ሲያራምዱ ማየት እየተለመደ የመጣ ተግባር እንደኾነ በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ አቶ ቻላቸው ታረቀኝ ተናግረዋል፡፡

አቶ ቻላቸው አንዳንድ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት መሪዎችም ኾኑ ታዋቂ ግለሰቦች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በድጋፍ ሰበብ ይምጡ እንጅ አጀንዳቸው ሽብርተኛውን ትህነግ በመደገፍ ሥውር ተልዕኳቸውን ተግባራዊ ለማድረግ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡

አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ኾኑ ግለሰቦች ሽብርተኛውን የትህነግ ቡድን በመደገፍ ድብቅ ተልኳቸውን ለማሳካት ሲሞክሩ እየታየ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ተገቢውን ምላሽ መስጠት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
አቶ ቻላቸው ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ደካማ መንግሥት እንዲመሠረት አጥብቀው ይሻሉ ብለዋል፡፡ ይኼን ተግባራዊ የሚያደርግላቸውን አካል ለማገዝ እና ለመደገፍም ሳይሰለቹ ደፋ ቀና እያሉ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ አቶ ቻላቸው ኢትዮጵያ ለበርካታ ሺህ ዓመታት ሉዓላዊነቷን አስከብራ የኖረች ሀገር ናት፡፡ ይህን ለዘመናት ሳይደፈር የኖረ ሉዓላዊነት ከሌሎች አካላት ጋር እጅ እና ጓንት ኾኖ በመሥራት ለማፍረስ መሞከር የጥቂት ሰዎች ምኞት ብቻ አይደለም፤ የበርካታ ምዕራባውያን ሀገራት ህልም እንጅ፤ ይኼን ህልም ለማክሸፍ በጋራ መሥራት ይስፈልጋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ አንድነቷ ተጠብቆና ሰላሟ ተረጋግጦ እንድትኖር የሚፈልጉ ሀገራት እና ግለሰቦች ሲመጡ በአክብሮት እና በኢትዮጵያዊነት ባሕል አስተናግዳ እየመለሠች ነው፤ ወደፊትም አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡

አቶ ቻላቸው እንዳሉት ኢትዮጵያ አንድነቷ ተጠናክሮ፣ በፖለቲካ ተረጋግታ በኢኮኖሚ ከበለፀገች፤ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትን እያዋሀደች ከቀጠለች ምዕራባውያን ከአፍሪካ የሚፈልጉትን የተፈጥሮ ሀብት እንደፈለጉት መዝረፍ አዳጋች ይኾንባቸዋል፤ ለዚህ ደግሞ መሣሪያው አንድ እና አንድ ብቻ ነው፤ ኢትዮጵያ የተከፋፈለች እና ደካማ መንግሥት እንዲኖራት አጥብቆ መሥራት ነው፤ ይሄ ተግባራዊ እንዳይኾን ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ መቆም እና መቃወም ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

ምዕራባውያን ሀገራት ኢትዮጵያ ራሷን ችላ እንድትቆም መፍቀድ የራሳቸውን ህልም መና ማስቀረት ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ለዚህ ነው ሽብርተኛውን የትህነግ ቡድንን ለመደገፍ ሲፍጨረጨሩ ይታያሉ ነው ያሉት፡፡

አቶ ቻላቸው አሁን የኢትዮጵያን አንድነት የሚያጠነክር፣ አብሮነቷን የሚደገፍ መንግሥት መምጣት ለምዕራባውያን የራስ ምታት ኾኖባቸዋል ይላሉ፡፡ የእናት ጡት ነካሹ ሽብርተኛው የትህነግ ቡድን ከምዕራባውያን የተሠጠውን የቤት ሥራ ለመሥራት ኢትዮጵያን ለ27 ዓመት በዘር፣ በሃይማኖት እና በቋንቋ ለመከፋፈል ሙከራ ቢያደርግም ኢትዮጵያውያን ልጆቻቸውን መስዋእት አድርገው በተባበረ ክንድ ላይመለስ ሸኝተውታል፡፡

በኢትዮጵያውያን ብርቱ ተጋድሎ ከመንግሥትነት ተነስቶ ወደ ጫካ የተወረወረ ሽብርተኛ ቡድን ዳግም ዕድል ሥጡት ማለት ምን ማለት እንደኾነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊረዳው እና ሊገነዘበው ይገባል ነው ያሉት አቶ ቻላቸው፡፡ ማኅበረሰቡ ጉዳዩን ተረድቶ ዝም ማለት ብቻ ሳይኾን ተቃውሞውን ማሠማት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ ለመኖር አምጣ በወለደቻቸው የቁርጥ ቀን ልጆቿ ትመራለች እንጅ ምዕራባውያን እጃቸውን አስረዝመው የባርነት ቀንበራቸውን እንዲጭኑባት አትፈቅድም፤ ለዚህ ደግሞ በርካታ ማሳያዎች መኖራቸውን መምህሩ ጠቁመዋል፡፡

አቶ ቻላቸው ኢትዮጵያን ከመፍረስ ለመታደግ የሁሉም ኀላፊነት ነው፤ ኀላፊነትን ለመወጣት ደግሞ በጋራ መሥራት ተገቢ መኾኑን አንስተዋል፡፡ ምሁራን ኅብረተሰቡን ማንቃት እና ማስተማር አለባቸው፤ የሃይማኖት አባቶችም በየእምነት ተቋሞቻቸው የሚገኙ ምዕመናንን የሽብርተኛውን ትህነግ እና የምዕራባውያንን ሥውር አጀንዳ ማስረዳት አለባቸው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የልጆቿን ወሳኝ ድጋፍ የምትሻው አሁን ነው ያሉት መምህሩ ማኅበረሰቡ በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በሞራል እና በጉልበቱ በማገዝ ዳግም ዓድዋን መድገም አለበት ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየሙሉዓለም የባህል ማዕከል በህልውና ዘመቻው ወቅቱን የሚመጥን ኹነት እያቀረበ ነው።
Next articleበእስራኤል ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትዉልደ ኢትዮጵያዊያን ለህልውና ዘመቻው የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታወቁ፡፡