
“የገጠመን ሰይጣናዊ አሸባሪ ቡድን ነው፤ ሰይጣን የሚኖረው ደግሞ በደም ነውና በጋራ ልንዋጋው ይገባል” የ8ኛ መዓበል ሜካናይዝድ ክፍለጦር ዋና አዛዥ ብርጋዲዬር ጀነራል ናስር አባዲጋ
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 29/11/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሙዚቃና የማርሽንግ ኦርኬስትራ ባንድ በምዕራብ ጎንደር ዞን በመገኘት ሠራዊቱን የሚያነቃቃና ለኅብረተሰብ የሞራል ስንቅ የሚሆኑ ሙዚቃዎችን በማቅረብ ድጋፉን አሳይቷል።
የሙዚቃ ማርሽንግ ባንዱ የህልውና ዘመቻውን በመቀላቀል በገንዳውኃ ከተማ ተገኝቶ ለማኅበረሰቡ፣ ለመከላከያ ሠራዊቱ፣ ለልዩ ኀይሉና ለሚሊሻው ወኔ የሚቀሰቅሱና አንድነትን የሚሰብኩ ሙዚቃዎችን አቅርቧል።
በዝግጅቱ የዞኑ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የጦር መኮንኖች፣ ጀነራሎች ሌሎች የጸጥታ ኀይሎችና የከተማው ማኅበረሰብ ተገኝተዋል።
“እኛ በዓለም የታሪክ መዝገብ የምንታወቀው በአይበገሬነታችንና ሉዓላዊነታችንን ባለማስደፈር ነው” ያሉት የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደሳለኝ ጣሰው ኢትዮጵያ እንደ ትናንት አባቶቻችን ዛሬም በእኛ ደም ክብሯ በደማቅ ተጽፎ ይቀጥላል ብለዋል።
ኢትዮጵያን ሰፈር ላድርጋት ብሎ የተነሳው አሸባሪውን የትህነግ ቡድን ደምስሰን ሀገራዊ አንድነታችን የምናረጋግጥበት ቀን ቅርብ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ኢትዮጵያውያን የሀገራችንን አደራ ተሸክመናልና የተግባር እንጅ የወሬ ጀግኖች ሳንሆን የገጠመነንን ችግር በጋራ ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
በዚህ ፈታኝ ወቅት ምርጫው በሰላም መጠናቀቁና የሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ ውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ የአይበገሬነታችን፣ የጀግንነታችንና የአንድነታችን ማሳያ ነው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አማረ ሰጤ ናቸው። ጦርነቱ ከአሸባሪው ጋር ብቻ ሳይሆን ከባዳዎችም ጋር ነውና አንድነትን ተላብሰን በመቆም በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቁን ድል እናስመዘግባለን ብለዋል።
የ8ኛ መዓበል ሜካናይዝድ ክፍለጦር ዋና አዛዥ ብርጋዲዬር ጀኔራል ናስር አባዲጋ የገጠመን ሰይጣናዊ ጁንታ ነው፤ ሰይጣን ደግሞ የሚኖረው በደም ነውና በጋራ ልንዋጋው ይገባል ብለዋል።
ማርሽንግ ባንዱ የህልውና ዘመቻውን ከተቀላቀለ ዛሬ 13ኛ ቀኑን ያስቆጠረ ሲሆን በማይካድራ፣ በወፍ አርግፍ፣ በምድረገነትና ሌሎች ቦታዎች በመገኘት ደጀንነቱን እንዳሳየ አስታውቋል።
ዘጋቢ፡- ቴዎድሮስ ደሴ – ከገንደው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
