የአሜሪካው ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (USAID) ኀላፊዋ ሳማንታ ፓወር የኢትዮጵያ ጉብኝት ውጤታማ እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

228

የአሜሪካው ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (USAID) ኀላፊዋ ሳማንታ ፓወር የኢትዮጵያ ጉብኝት ውጤታማ እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 29/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (USAID) ኀላፊዋ ሳማንታ ፓወር በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ በሥራ ብዛት ምክንያት ከጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር መገናኘት ባለመቻላቸው ከሌሎች አቻ የሚመለከታቸው የሥራ ኀላፊዎች ጋር በመወያየት ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃበይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገልጸዋል። ቃል አቀባዩ ኀላፊዋ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ማግኘት አንደማይችሉ ተነግሯቸው ነው የመጡት ብለዋል። በነበራቸው ቆይታም ከአቻ እና ከሚመለከታቸው ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን ገልጸዋል፡፡

የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ከሳማንታ ፓወር ጋር ባካሄዱት ውይይት የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ የጦርነትን ጉዳት በመረዳት ሰላም እንዲፈጠር በርካታ ተግባራትን ያከናወኑ ቢሆንም ይህ ጥረት ሳይሳካ ቀርቶ አሸባሪው የትህነግ ቡድን የሀገሪቱን መከላከያ በማጥቃት ጦርነቱን እንደጀመረው ማስረዳታቸውን በሰጡት መግለጫ አብራርተዋል፡፡ ሚኒስትሯ ሙፈሪያት መንግሥትም ሳይፈልግ ተገዶ የገባበት ጦርነት መኾኑን ለኃላፊዋ አብራርተውላቸዋል ነው ያሉት።

የአሜሪካው ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (USAID) ኃላፊዋ ሳማንታ ፓወርም የትህነግ ቡድን ተኩስ አቁሙን ማክበር እንዳለበት እና እርዳታ እንዳይደርስ እያስተጓጎለ መኾኑ ተገቢ እንዳልኾነ ገልጸዋል ብለዋል።

የአሜሪካ እና የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ግንኙነት መሻከሩ እንዳሳዘናቸው ጨምረው ገልጸዋል ብለዋል አምባሳደር ዲና። አምባሳደር ዲና በሱዳን በኩል የእረዳታ ኮሪደር ስለማስከፈት ጉዳይ ሳማንታ ፓወር እንዳላነሱም አብራርተዋል።

የአሜሪካው ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (USAID) ኃላፊዋ ሳማንታ ፓወር ሥራቸውን አከናውነው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል። መንግሥት ይህ ጉብኝት ስኬታማ መሆኑን ያምናል ያሉት አምባሳደር ዲና አምባሳደር ዲና በቀጣይ ሳማንታ ዋሽንግተን ሲደርሱ የሚያቀርቡትን ሪፖረት ምን ሊሆን እንደሚችል እንጠብቃለን ነው ያሉት።

ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን – ከአዲስ አበባ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleአሸባሪው ትህነግ በወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ላይ የፈጸመውን ግፍ አስመልክቶ ያካሄደውን የጥናት ውጤት ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ገለጸ፡፡
Next articleየህዳሴው ግድብ ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት ኀይል ለማመንጨት በሚያስችል ደረጃ ላይ ነው፡፡