
የሕወሓት አሸባሪ ቡድን ሥርዓት የሚይዝ ከሆነ መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ ሰብዓዊ ድጋፍ ማቅረብ እንደሚችል ገለጸ።
ባሕር ዳር:ሐምሌ 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ)ለጉብኝት አዲስ አበባ የገቡት የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት ኃላፊ ሳማንታ ፓዎር ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱም ወቅት በትግራይ ክልል በተፈጠረው ሁኔታና የሕወሓት አሸባሪ ቡድን እየፈጠረ ባለው ችግር ዙሪያ ለኀላፊዋ ሰፊ ገለፃና ማብራሪያ እንደተደረገላቸው የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ገልጸዋል።
የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት ኀላፊ ሳማንታ ፓዎር ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው የሕወሓት አሸባሪ ቡድን እየፈፀመ ያለውን ጥፋት በትክክል እንዲረዱ ማስቻሉን ነው የጠቆሙት።
የሕወሓት አሸባሪ ቡድን በሀገር ላይ በፈጠረው የሀገር የህልውና አደጋ መንግሥት ተገዶ ወደ ጦርነት መግባቱንም እንዲረዱ ተደርጓል ብለዋል።
ሆኖም የሕወሓት አሸባሪ ቡድን በሀገሪቱና በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖርና ዜጎች ለችግር እንዲጋለጡ በጥፋት መንገድ መቀጠሉን አስረድተናቸዋል ብለዋል ወይዘሮ ሙፈሪያት።
ለተራድኦ ድርጅት ኀላፊዋ በተደረገላቸው ገለፃ የሕወሓት አሸባሪ ቡድን ሥርዓት የሚይዝ ከሆነ መንግሥት በየትኛውም አማራጭ ለትግራይ ሕዝብ ሰብዓዊ ድጋፍ ማቅረብ እንደሚችል አረጋግጠውላቸዋል።
በትግራይ ክልል ለሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ በአግባቡ እንዳይደርስ አሸባሪ ቡድኑ እያስተጓጎለ መሆኑን ማስረዳታቸውን አመልክተው፤ ቡድኑ ከእኩይ ዓላማው የሚታቀብ ከሆነ መንግሥት ለሕዝቡ ማንኛውንም ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያደርስ አረጋግጠንላቸዋል ነው ያሉት ሚኒስትሯ።
አሸባሪው ሕወሓት በመንግሥት የተሰጡትን የሰላም አማራጮች እና የመንግሥትን የተናጠል ተኩስ አቁም ባለመቀበል በጥፋቱ መቀጠሉን ኀላፊዋ እንዲረዱ ተደርጓል።
ቡድኑ በከፈተው ጦርነት በአማራ እና አፋር ክልሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለው ለከፍተኛ ችግርና እንግልት መዳረጋቸውንም አስረድተናቸዋል ብለዋል።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ለተፈጠሩት ወቅታዊ ችግሮች ከጅምሩ አስካሁን የሕወሓት የሽብር ቡድን ጥፋት መሆኑን ማስረዳት መቻሉን የሰላም ሚኒስትሯ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ሳማንታ ፓዎር በአሁኑ ጊዜ የአሜሪካ መንግሥት እርዳታ ድርጅት የሆነውን ዩ ኤስ ኤ አይ ድ የሚመሩ ሴት ናቸው።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
